No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Tuesday, 14 August 2012

‹‹ሆያ ሆዬ… ያች ድንክ አልጋ…ሆ… አመለኛ›› – ከተመስገን ደሳለኝ




በልጅነት ዕድሜያችን ከሚወደዱ እና ከሚናፋቁ ወራቶች ነሐሴ ዋነኛው ነው። በተለይ ለብላቴናዎች። ለወሩ ተወዳጅነት ምክንያት የሆነው ደግሞ በ‹‹ሆያ ሆዬ›› ጭፈራ የሚከበረው የ‹‹ቡሄ›› ባህል በዚህ ወር መሆኑ ነው። ስለዚህም ከወሩ የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ‹‹ጅራፍ›› እየገመዱ በሚያስጮኹ ማቲዎች መንደሮች ይታመሳሉ። በዚህ አይነት መልኩ እየተዝናኑ ይቆዩና ዕለቱ ሲደርስ ተቧድነው ‹‹ሆያ ሆዬ›› ዕያሉ በየቤቱ ይዞራሉ።
ሆያ ሆዬ

ሆዬ የኔ ጌታ

እዛ ማዶ ሆ፣ ጭስ ይጨሳል
አጋፋሪ ይደግሳል
ያችን ድግስ ውጬ ውጬ
በድንክ አልጋ ተገልብጬ
ያች ድንክ አልጋ አመለኛ
ያለ አንድ ሰው አታስተኛ…
ክፈት በለው በሩን የጌታውን

ጭፈራው ይደምቃል። ሽልማቱ ይጎርፋል። ምስጋናው ይዥጐደጐዳል።
እነሆም በዘንድሮ ‹‹ቡሄ›› ዋዜማ በቤተመንግሥቱ ‹‹ሆዬ ሆዬ›› ደምቋል፣
ያች ድንክ አልጋም ‹‹አመለኛ›› በመሆኗ ብዙዎችን ግራ እያጋባች ነው። ግራ የተጋቡት አልጋውን የሚፈልጉት ብቻ አይደሉም፡፡ ለሚፈልጉት ለመስጠት የቋመጡም ግራ ተጋብተዋል። ለምሳሌ አሜሪካ ዋነኛዋ ነች። ለዚህም መሰለኝ የኃይል ትንቅንቅ የፈጠሩትን በመሸምገል የተጠመደችው። እናም አዲስ አበባ ያሉ ዲፕሎማቶቿ ከዚህ ጉዳይ ውጭ ምንም መስማት የሚፈልጉ አይመስሉም። የፍትህ መዘጋት እና መታገድንም ሊሰሙ አልፈለጉም (እንደ እኔ መረጃ አሜሪካ ኤምባሲ በአሁኑ ወቅት ከሴራው ቀደም ቀደም እያለ መረጃ የሚሰጥ እንደፍትህ አይነት ሚዲያ ባለመኖሩ ላይ ተስማምታለች) ይህ አንድ እውነት ነው።
ወደ አልጋው እንመለስ
ምስኪን ኦህዴድ! ‹‹መሪ›› እየተፈለገለት ነው። ሊቀመንበሩ አለማየሁ ቱምሳ ጤናቸው ከታወከ አመት አልፎታል። ሰሞኑንም በይፋ መልቀቂያ እንዳስገቡ ምንጮቼ ነግረውኛል። በነገራችን ላይ በፌዴራላዊ መንግሥት ብቻ አይደለም መሪ የጠፋው አሮሚያ ክልልም ፕሬዚዳንቷ ታማሚ ሆነው አልጋ ከያዙ ቆይተዋል። በምክትላቸው አብዱልአዚዝ ላይ ህወሓት እና ብአዴን እምነት ማሳደር የቻሉ አይመስሉም። የጁነዲን ሳዶም ጩኸት የበረሃ ጩኸት ከመሆኑ ባለፈ የሚያመለክተው ነገር ቢኖር ኦህዴድ ማፈንገጡን እና ከውድድሩ እየተሸራተተ መሆኑን ብቻ ነው።
ሌላኛው የፖለቲካ ፓርቲ በጥርስ ፍንጭቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራው ደኢህዴን ነው። ደህኢዴን ‹‹ያች ድንክ አልጋ›› ለእኔ ትገባለች ብሎ ጨረታው ላይ ሊሳተፍ አልፈለገም። አብዛኛው የአመራር አባል ‹‹እየሱስ ጌታ ነው›› በሚል ስብከት የተጠመደ ይመስላል። እስከአሁንም በለስ ቀንቶት ሁለት ሚኒስትሮች ‹‹ጌታን እንዲቀበሉ›› አድርጓል። በግሌ እየሱስ ጌታ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ቅሬታዬም ይህ አይደለም፡፡ ያደናገረኝ ሀገር እንመራለን ብለው ስልጣን የያዙ ሰዎች በስራ ሰዓት በዚህ መጠመዳቸው ነው፡፡ እንግዲህ አመንክም አላመንክም በዚህ ዘመን፣ በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ይህም የፖለቲካ ድርጅት ነው እየተባልክ ነው።
ህወሓት እና ብአዴን
ህወሓት እና ብአዴን አሁንም እንደተፋጠጡ ነው። ኧረ ከፍጥጫም ከፍ ብሎ ጠንካራ የብአዴን የአደባባይ ደጋፊዎች ሰፈር እየተደፈረ ነው። በአናቱም ሁነኛ ሰዎቻቸውም እየተደቆሱ ነው። ይህ እየሆነም አሸናፊው ገና አልለየም።
የሆነ ሆኖ በቅርቡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደስራቸው የሚመለሱ መስሎን ነበር። ይህ ሊሆን ስላልቻለ የመንግሥት ስራም እንዳይስተጓጎል በእከሌ ተክተናቸዋል። (ስም ልጥቀስ እንዴ?)›› የሚል ይዘት ያለው መግለጫ እንደምንሰማ ተስፋ አደርጋለሁ።
ልክ እንደአቤ ቶኪቻው፡- በመጨረሻም
አዎ በመጨረሻም ነገ ፍርድ ቤት እቀርባለሁ። ብዙ ድራማዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ። የክሱ ቻርጅ ትላንት ማታ ደርሶኛል። ያለፈው አርብ ቻርጁ ሳይደርሰኝ ጉዳዩ መታየት እንደጀመረ በሬዲዮ ፋና መስማቴን ተናግሬ ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት መልእክት ግልፅ ነው ‹‹የተጠቀሰው አንቀጽ አደገኛ ነው እና እስከሚቀጥለው ቀጠሮ ድረስ ሀገር ለቀህ ውጣ›› የሚል እንደሆነ ማለቴ ነው። ሆኖም ምንም ይፈጠር ምን ሌላ ሀገር የለኝምና ነገ በከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ 16ኛ ወንጀል ችሎት እቀርባለሁ። በትምህርተ ስላቅም ዋስትና እንደሚፈቀድልኝ እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ፡፡
በአጠቃላይ ይህ ሁኔታ ከተከሰተ ጀምሮ ቢሮ በመምጣት እና በተለያዩ መንገዶች አጋርነታችሁን ያሳያችሁኝን አመሰግናለሁ። ከዚህ በኋላ የቀረኝ ነገር እንደሌለ ጠቅሳችሁ ‹‹ሀገር ለቅቄ እንድወጣ›› የመከራችሁኝንም-ለቀና አሳባችሁ ከልብ አመሰግናለሁ። ምንአልባትም ይህ የመጨረሻ ቃሌ ከሆነም ለሀገሬ የምከፍለው ዋጋ ነውና ይሁን ብያለሁ፡፡ …የፍትህ ጠንካራ መንፈስም በባልደረቦቼ መሪነት ጉዞውን ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment