No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Friday 17 August 2012

አይታክቴው ታማኝ በሲድኒ


አብይ ዮሃንስ አፈወርቅ 
በአውስትራሊያ የኢሳት ርዳታ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በደማቅ ሁኔታ ተጀመረ
       በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ ጠልፎ አማራጭ ሜዲያነቱን ያረጋገጠውን ኢሳትን
ለመርዳት በተለያዩ የአውስትራሊያ ከተሞች የተያዘው የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራም ትላንት እሁድ ኦገስት 12
ቀን 2012 ዓ.ም. እጅግ በደመቀ ሁኔታ በሲድኒ ተጀምሯል።       ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሲድኒ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን
 በጋለ ስሜት ተሞልተው ዝግጅቱን ያደመቁት ሲሆን ተወዳጁ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነም እንደተለመደው
ሁሉ በተባ አንደበቱ ወሳኝ የሆኑ አገርኛ ጉዳዮችን እያነሳ በመረጃ የተደገፉ ትንታኔዎችን አቅርቧል።
       አክቲቪስት ታማኝ በዚህ ፕሮግራም ላይ ለመገኘት የበቃው ከአራት ቀናት በላይ የፈጀ መኝታ

ቢስ እንግልት አሳልፎ ቢሆንም በስሜት ተሞልተው የተጠባበቁት ወገኖቹ ፊት ሲቆም ግን አንዳችም
ድካም ባልታየበት ሙሉ መነቃቃትና ጥንካሬ ፕሮግራሙን ማቅረቡ ታዳሚውን ሁሉ ያስገረመ ጉዳይ
ነበር። ከዋሽንግተን ዲሲ ጉዞውን ባለፈው ሃሙስ የጀመረው ታማኝ ገና ከመነሻው ከአየር ጸባይ
መበላሸት ጋር በተገናኘ የበረራ መሰረዝ ስላጋጠመው በተለያዩ አየር ማረፊያዎች ረዥም ሰአታትንለማሳለፍ
የተገደደ ሲሆን በመጨረሻም ከ20  ሰአታት በላይ ተጉዞ ሲዲኒ በገባ በጥቂት ሰአታት ውስጥ
ነበር ወደ ዝግጅቱ ስፍራ ያመራው፡ አዳራሹን ሞልተው በጉጉት የተጠባበቁት የሲድኒ ኢትዮጵያውያንም
አይታክቴው አክቲቪስት የግል ምቾቱን ንቆ ከመሃላቸው ለመገኘት የከፈለውን ዋጋ አድንቀው የሚገባውን
 ክብር ችረውታል።  በፀሎት በተከፈተው በዚህ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ ስሜት ቀስቃሽ ግጥሞች ሙገሳ በሚገባቸው
ገጣሚያን የቀረቡ ሲሆን ታማኝ በየነ አንድ ሰአት ተኩል ያህል ጊዜ የፈጀ በምስል የተደገፈ መሳጭ
ፕሮግራሙን አቅርቧል። ታማኝ ለምን የመብት ተሟጋች ለመሆን እንደመረጠ ለማመላከት ከተለመደው አቀራረቡ ወጣ
ባለ መልኩ የግል ህይወቱን ገና ከጅማሬው ያስፈተሸ ሲሆን ይህም በፍቅርና በጽኑ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ
ከታደሙት ወገኖቹ ጋር መንፈሳዊ ትሥሥሩን እንዲያጠናክር ልዩ ሃይል ሆኖታል።
       አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ እያዋዛና በአስገራሚ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እያስደገፈ በተለመደው ርቱእ
አንደበት ሲተነትንም በተመስጦ የሚከታተሉት ኢትዮጵያውያንን በስሜት ማዕበል ማንቀሳቀሱ ጎልቶ
ታይቷል። ኢትዮጵያውያኑ የፕሮግራሙ ታዳሚዎች አገር ቤት ባሉ ወገኖቻቸው ላይ እየደረሰ ባለው
መንግስታዊ በደል ሃዘንና ቁጭት ሲንጣቸው ታማኝ በየመሃሉ እያዋዛ ጣል በሚያደርጋቸው ቀልዶቹ
እያሳቀና እያረገበ ጠንካራ ቁምነገሮቹን ማስጨበጥ ችሏል። ተከትሎ በተካሄደው የጨረታ ስነ-ስራት ላይም የሚያስደስት ተሳታፊነትና ፉክክር የታየበት ሲሆን ለኢሳት መርጃ የሚሆን ጠቀም ያለ ገቢም ለማሰባሰብ ተችሏል።
 በእለቱ በተለይም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እህቶችና እናቶች መገኘታቸውን ያወደሰው ታማኝ
በእያንዳንዱ ተሳታፊ አይምሮ ውስጥ « እኔስ በኢትዮጵያዊነቴ ማበርከት የምችለው ምንድነው?» የሚል
ጥያቄ ለማጫር መብቃቱን የተለያዩ ታዳሚዎችን እየዞረ ያነጋገረው የዚህ ሪፖርት አቅራቢ አረጋግጧል።
ካነጋገርኳቸው ኢትዮጵያዊያን አንዱ ‹ፖለቲካ አልወድም› የሚል የኖረ ስሜቱን የገለጸ ሲሆን
«አያገባኝም የሚለው ስሜቴ ግን ዛሬ ጥሎኝ በሯል!» ሲል ተናግሯል። «  ወገንህ ያለአግባብ ሲበደል ‹ለምን?›
ማለት ፤ ፍትህ ሲጓደልብህም መቆጨትና መብትህን መጠየቅ ፖለቲካ ሳይሆን የህልውናና የመብት ጉዳይ መሆኑን ነው ያረጋገጠልኝ» ያለችኝ ሌላዋ ታዳሚም "  ዛሬ ታማኝ በውስጤ ህያው የሆነ ሻማ ነው የለኮሰው"
 በሚል አገላለጽ ዕለቱን አወድሳዋለች። ‹የኔስ ድርሻ ምንድን ነው?› የሚለው ጥያቄ ውስጣቸው እንደቀረ ያመላከቱኝ የተለያዩ ታዳሚዎች ኢሳትን በሚችሉት መንገድ ሁሉ መርዳት ቀዳማይ ተግባራቸው እንደሚሆን ጠቁመውኛል። "ማዕድ ከታማኝ ጋር" በሚል በተያዘው ተጨማሪ የገቢ ማሰባሰቢያ ልዩ ፕሮግራም ላይም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተው ምሽቱን ከታማኝ ጋር አሳልፈዋል። ለቀናት ያለዕረፍት ሲንከራተት የቆየው የመብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነም ከወገኖቹ መሀል መገኘቱ
 ምስጢራዊ ጉልበት ሆኖት ጠረጴዛ እየቀያየረ ከሁሉም የማዕዱ ተቋዳሾች ጋር በጓደኝነት መንፈስ ሲያወጋ ማምሸቱን ያስተዋሉ አንድ ኢትዮጵያዊ "ይህ ሰው በልቡ ያለው ፍቅር ከብረት በላይ አጠንክሮታል" ሲሉ ለዚህ ዘጋቢ ሹክ ብለውታል።
       በሲድኒ ያሉ የኢሳት አፍቃሪዎች ዕለቷን አድምቀዋት እንደዋሉ ሁሉ በሌሎች የአውስትራሊያ
ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ለኢሳት ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ
መሆናቸውን ከየስቴቱ ያሰባሰብናቸው አስተያየቶች ያመላክታሉ።  ይህ በአውስትራሊያ የተለያዩ ከተሞች
የሚካሄደው ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የመክፈቻ ዝግጅቱ የታቀደው የላቀ ቁጥር ያላቸው
 ኢትዮጵያዊያን መኖሪያ በሆነችው በሜልቦርን ቢሆንም በጉዞ መስተጓጎል ሳቢያ የሜልበርኑ ፕሮግራም
ባንድ ሳምንት መራዘሙ ታውቋል። አይታክቴው የመብት ተሟጋች ታማኝ በየነ በመጪዎቹ ሳምንታት
በሌሎች 4  ከተሞች ዝግጅቶቹን የሚያቀርብ እንደመሆኑ  በአገር ውስጥ ጉዞ ብቻ ከ20  ሰዓታት በላይ
የበረራ ቆይታ ይጠብቀዋል። ይህን የሁለት ሳምንት ተልዕኮውን ለመወጣት    ዓለም አቀፍ የደርሶ መልስ
ጉዞውን ጨምሮ በድምሩ ከ60 ሰዓታት በላይ በዓየር ላይ ጉዞ ያሳልፋልም ተብሏል።

No comments:

Post a Comment