ይሄይስ አእምሮ
ሀገራችን የጉድ መንተክተኪያ ጎላ ድስት ከሆነች ቆየች፡፡ ባለሥልጣን ከናካቴው የለንም ወይም ሁሉም በየፊናው
ባለሥልጣን ሆኗል፡፡ ተጠያቂነት የሚባል ነገር ድራሹ ጠፍቷል፡፡ ነገረ ሥራችን ሁሉ የአባትህ አገር ሲወረር አብረህ
ውረር ዓይነት ነው፡፡ ሁሉም ባመቸው አጋጣሚ የቻለውን መቦጨቅና ኢንቬስተር መሆን በተለይ ለወያኔያውያን በጣም
የተንቦረቀቀ መስክ ከሆነ ሰነበተ፡፡ እስኪ ስለ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትንሽ እናውራ፡፡ ከመሪያችን ሁኔታ በተጓዳኝ
ይህም ነገር ሰሞነኛ ነው፡፡ ትንሽ እንቆዝም፡፡
አሠራሩ እንደማንኛውም የመንግሥት ቤት ሁሉ መደዴ እንጂ በሕግና በሥርዓት የሚመራ አይደለም፡፡ ከሞላ ጎደል በሁሉም
የሀገራችን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት እንደነገሠ ሁሉ በዚህ ቤትም ይሄው ችግር ጥርሱን
ባገጠጠ መልኩ እንደተንሠራፋ ከዚያው አካባቢ የሚናፈሱ ወሬዎች ያረጋግጣሉ፤ የሰሞኑ የሎንዶን አሎምፒክም ይህን ጉድ ገሃድ አውጥቶት በዓለም ላይ መሣቂያና መሣለቂያ አድርጎናል፡፡ ዘርፈ ብዙው መረገማችን ዓለምን ከጽንፍ እስከአጽናፍ እያዳረሰና መላውን የመሬት ነዋሪ እያስደመመ ነው፡፡ ሁሉም መሥሪያ ቤት ‹የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ› ብሎ መሪ ድርጅቱን ኢሕአዴግን በነቀዘ አሠራር ከፍ አድርጎ እያስጠራ ነው፡፡ ‹የዕድገታችንና የልማታችን አባት ኢሕአዴግ ሆይ!፤ የብልግናችን መሠረት በመሆንህ ስምህ ለዘላለሙ ከፍ ከፍ ይበል› በሚሉ የሙስና ደቀ መዛሙርት የተጥለቀለቀው የሀገራችን ቢሮክራሲ ከምን ጊዜውም በበለጠ በንቃት እየዘረፈ ነው፡፡(ኦ! ካለፈ ያየሁት የአርትዖት ስህተት – የብልግናችን ሳይሆን የብልጽግናችን ተብሎ ይነበብልኝ)
ትዝ ይላችሁ እንደሆነ በ1983ዓ.ም ግንቦት ወር ውስጥ የደርግ መንግሥት ሄርማን ኮህን በተባለ ወስላታ አሜሪካዊ ዲፕሎማት አደራዳሪነት ሎንዶን ላይ ወያኔና ደርግ የይስሙላ ድርድር አድርገው ነበር፡፡ በዚያ ሳይጀመር የተጠናቀቀ በተባለ ሸውራራ ድርድር ለመሣተፍ ከኢትዮጵያ ወገን 13 የልዑካን ቡድን አባላት ነበር የሄዱት፡፡ ያኔ ይህን ያህል የተደራዳሪ ብዛት መላኩን የሰማን ሰዎች ‹እንዴ! ይሄ ነገር ዱላ ሊገጥሙ ነው ወይንስ ከምር ሊደራደሩ?› ብለን አሸሙረን ነበር፡፡ እውነታችንን ነው፡፡ ሌላ ዓላማ ከሌለው በስተቀር ለአንድ ድርድር 13 ሰው ምን ያደርጋል? እንደጠረጠርነው ተመልሶ ወዳገር የገባው የልዑካን ቡድን ቁጥር ጥቂት ነበር፡፡
በሰሞኑ የሎንደን ኦሎምፒክ ደግሞ ከዚያ የበለጠ አስቂኝ ድራማ አየን፡፡ በቅሌት መዝገብ ስሙ ዘወትር የሚነሣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወደ ውድድሩ ሥፍራ የላካቸው ሰዎች 35 አጃቢና 33 ተወዳዳሪዎች መሆናቸውን ስንሰማ ያልተገረምን የለንም – ከመገረምም አልፈን በሰዎቹ ቂላቂልነት ከትከት ብለን ስቀናል፡፡ የሀገር መጥፋት ማለት እንዲህ በተሟላ መልኩ ሲሆን አያስተማማም – መጸዳጃ ቤት ገብተን የፈረንሣይ ኮሎኝ መዓዛ እንዲሸተን መቼም አንጠብቅም፡፡ ምክንያቱም በወያኔ አገዛዝ ከራስጌ እስከ ግርጌ በሙስና በበሰበሰና በከረፋ ሥርዓት ውስጥ አንዱ ተለይቶ ጻዲቅ እንዲሆን አይጠበቅበትምና – በዚህ ሥርዓት ውስጥ መልካም ልሁን ብትል መጥፎው አንተ ትሆንንና በሽብርተኝነት ወይም በሙስና ቃሊቲ ትወርዳለህ፡፡ በቅሌታም ሥርዓት ያለህ አማራጭ አንድም አብረህና ተባብረህ ቅሌታም መሆን አለዚያም የሰው ቦታ መልቀቅ፤ የሙስናን ዑደታዊ የደም ዝውውር ስለምታደናቅፍ ብልሹ ስብዕና ከሌለህ ወያኔን በ‹ታማኝነት› ማገልገል አትችልም፡፡ ነባሩ ብሂልስ ‹ ተከተል አለቃህን፤ ምታ ነጋሪትህን› አይደል – ባይኖርም አሁን እንበለው ግዴለም፡፡ እንደሄደው ሰው ብዛት ከሆነ የፌዴሬሽኑ ዘበኛና ጽዳትም አዲስ አበባ ላይ የቀረ አይመስልም፡፡ ዱሮ በደጉ ዘመን ‹የስሙኒ ዶሮ የብር ገመድ ይዛ ጠፋች› ይባል ነበር – ዛሬ እመት ኩኩሉ በነጠላ ግዢ 200 ብር ልትገባ፤ ቅቤውም እንደዛው፡፡ አሜሪካዎች ለ115 ገደማ ተወዳዳሪ ስፖርተኛ 12 አመራር፣አሠልጣኝ፣ ሐኪምና አማካሪ ስትልክ የኞቹ ይሉኝታቢሶች በእከከኝ ልከክልህ ተጠቃቅሰው ቅንጣት ሳያፍሩ ለ33 ስፖርተኛ 35 ሰው ላኩ – የክፍለ ዘመናችን ስፖርት ነክ ቀልድ ነው፡፡ እንዲያው ለመሆኑ ሀፍረትና ይሉኝታ ጓዛቸውን ጠቅልለው እንደብዙኃን ከርታታ ወገኖቻችን ከኢትዮዮጵያ ተሰደዱ እንበል? ሀገር ቢኖረን እኮ ይህን ያደረገ/ጉ እንደተመለሱ ዘብጥያ በወረዱ ነበር – ሥርዓታዊ ሀገር ብትኖር ደግሞ ከመነሻውም እንዲህ ባልሆነ – አሁን ግን ባለቤቱን ስለናቁ ከሕዝብ የተሰበሰበውን ዐርባ ስድስት ሚሊዮን ብር ሊነቀንቁ ግም ለግም ተያይዘው ተመሳጠሩ፡፡ እናም ያው በዚአከ ለዚአየ የመጠቃቀም አባዜ ተለክፈው የሕዝብን ገንዘብ እያሟጠጡ ሊዘርፉ ከላይ እስከታች ተስማሙ፡፡ የማይጠየቁ መስሏቸው ከሆነ ትክክል አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሏንም ነገር እየመዘገበ መሆኑን ይረዱት፡፡ ዛሬ እንዲህ በማንአለብኝነት ቢዘባነኑ የሚጠየቁበት ቀን መምጣቱን መርሳት የለባቸውም፡፡ ታሪክ መዝጋቢዎች ይህንንም ሳትረሱ መዝግቡት – አደራ!!
አትሌት እንዴት እንደሚመረጥ ብትሰሙ ደግሞ ምናልባት በሀገራችን ሞቶ መቀበር ታለቅሱ ይሆናል፡፡ ቀዳሚው የመመረጫ መሥፈርት ጎሣና ነገድ ነው፡፡ ቀጥሎ ለባለሥልጣናት ያለ ቀረቤታ ነው፡፡ ቀጥሎም ገንዘብ ነው፡፡ ቀጥሎም ወሲብ ነው – ምን ያሳፍረኛል? ቀጥሎም ዝና ነው – ቀደም ባለ ወቅት በተመዘገበ ስኬት ምክንያት በግለሰብ ላይ የተገነባ አምልኮት – ለዚህም ነው የዛሬ 20 ዓመት በውርስትና ወቅት እንደአቦ ሸማኔ እየተወነጨፈ ወርቅ ወርቁን ሲሞጨልፍ የነበረ የዛሬ ጎልማሣ በስፖርታዊ እርጅናው ተሰልፎ ሲሮጥ የምናየው፤ አሰላፊም ተሰላፊም ይሉኝታ ቢሶች ሆኑ፡፡ በቃኝ ጠፋ፡፡ ‹ይበቃሃል፤ደክመሃል› የሚልም ጠፋ፡፡ ሁሉም እየተመሳጠረ ብቻ ሕዝብን ማሳዘን ሆነ ሥራው፡፡ በነዚህና በመሳሰሉ ምክንያቶች ሀገሪቱ ልታገኘው የነበረው አንድያ የአትሌቲክስ ድል እያሽቆለቆለ መጥቶ ከ68 ሰው ሦስት ወርቅ ብቻ ልናገኝ በቃን፡፡ የመለስን ዘረኛ ሥርዓት በአጠቃላይ ፣ ፌዴሬሽኑን ደግሞ በተለይ እግዜር ይይላቸው፡፡ ብቸኛዋን የሀገራችንን የኩራት ምንጭ በዘርና በጥቅማጥቅም ልክፍት አጥምቀው እንዳይሆን አደረጉት፡፡ ወጣት ተስፈኞችን አፍነውና ሳይወዱ በግዳቸው በተውሶ ዜግነት የባዕድ ሀገር ባንዲራ በኦሎምፒክና በሌሎች የስፖርት መንደሮች እንዲያውለበልቡ ለስደት ዳርገው በቀላሉ ልናገኘው የሚቻለንን ድል አሳጡን፤ ይህን ያደረጉ ሰዎች ከምር ልጅ አይውጣላቸው፡፡ ሀብታቸውን ብል፣ ነፍሳቸውን ሲዖል ይብላው፤ እነዚህን መሰል የሀገር ጥፋት አምባሳደሮች የተወለዱባቸው ቀናት ከቀናት ሁሉ ተለይተው የተረገሙ ይሁኑ – ኢዮባዊ እርግማኔ ይድረስባቸው፡፡ አሁን በውነት ከ90 ሚሊዮን ሕዝብ 100 ቆፍጣና ሯጭ ጠፍቶ ነው? የአንድ ነጥብ ምናምን ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት የሆነችው ትሪንዳድና ቶቤጎ በዓለም ዋንጫ ስትሰለፍ እኛ መቶ ሚሊዮንን የጎሪጥ እያዬ ካለው የሕዝባችን ብዛት 11 ሰው አጥተን ነውን ለአፍሪካ ዋንጫ እንኳን የመጀመሪያ ማጣሪያ ልንደርስ ያልቻልነው? አመራር … አመራር… አመራር… ችግራችን የአመራር ነው፡፡ ችግራችን ኢትዮጵያን ‹የኔ ናት› ብሎ በትክክለኛ የሀገር ፍቅር ስሜት የሚያስተዳድራት ሁነኛ ሰው መጥፋት ነው፡፡ ይህ የእግር እሳት ነው ብዙዎቻችንን እየፈጀን የሚገኘው፡፡ ባለቤት የሌለው አህያ ማንም ሲጭነው ይውላል – የአሁኑን አያድርገውና መንጌ ‹ብታምኑም ባታምኑም…› የምትል አማርኛ ነበረችው – እናም ብታምኑም ባታምኑም የጠፍ አህያ ሆነናል፤ ስለዚህም ሀገሪቱ ባለቤት የሌላት ያህል ጋጠወጡ ወያኔ እንዳሻው እንደቅሪላ እያላጋት ነው፡፡ ይህችን በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ እያቃሰተች የምትገኝ ሀገር ማን ይድረስላት? ማንስ አለሁልሽ ይበላት? ማን የደም ጎርፏን ይጥረግላት? አሁን በሥልጣን ላይ ካሉት ሰዎቻችን አብዛኞቹ አንድን ነገር ለነሱ ከሚያስገኝ ጥቅም አንጻር እንጂ ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት አንጻር ሊመለከቱ አይፈልጉም፡፡ ለዚህ የዳረጋቸው የወያኔ ከፋፍለህ ግዛ የፖለቲካ ሥልት ነው፡፡ ለየትኛው ሰንደቅ ዓላማ – ለየትኛዋ ሀገር – ለየትኛው ብሔራዊ አጀንዳ – ለየትኛው መፋቀርና መፈቃቀድ – ለየትኛው ዘውግ ጥቅምና ፍላጎት – እነዚህ ባለፉት 21 ዓመታት በሀገራችን የተተከሉ ነቀርሣዎች በባለሥልጣናቱም አእምሮ ውስጥ ሆነ በበርካታው ዜጋ ኅሊና ውስጥ ያስቀመጡት የደፈረሰ ነገር በቀላሉ የሚገመት አይደለም፤ ለማጥራትም ጊዜ ይወስዳል፤ ወዮ! ለቀጣዩ መንግሥት፡፡ ብዙ ሥራ አለበት፡፡ ለኔ የፈጠሩልኝን ባንዴራ ለምሳሌ ቀለሙ ይቅላ ይጥቆር አላውቀውም፤ ባህር ዳርና ጎንደር ላይ ግን እሱን ይዘው እንከፍ እንከፍ የሚሉ ሞኛሞኞች አሉ ይባላል – ለዕለት ጉርስ የሚታለሉ ጅሎች ወይም በዓላማ አንድነት የተቆላለፉ መሠሪዎች፡፡ ወያኔዎች ደግሞ በማንኛችንም ውስጥ የሚፈጠርን የማንነት ኪሣራ አጥብቀው ይፈልጉታል፤ ሌት ከቀን የሚደክሙትም ለዚሁ ነው – ሀገሪቱን ያለባለቤት በወለድ አገድ ራሳቸው ይዘው ያሻቸውን ለማድረግ እንዲችሉ – ልክ እንደእስከዛሬውና ልክ እንደአሁኑ፡፡ ስለዚህም እያንዳንዱ ባለሥልጣን ከሲሳዩ እንዴት እንደሚቦጭቅ እንጂ የሚጨነቅለት የሥራ ዲሲፕሊንና ኤቲክስ ብሎ ነገር የለውም፡፡ ሀገር ሲያረጅ የጃርት መፈንጫ ይሆናል ማለት ይህን ጊዜ ነው፡፡
ከሰማሁት ጥቂት ላካፍላችሁ፡፡ አንድ የ10000ሜትር ሯጭ እንደማይሆንለት እየታወቀ አሰለፉት አሉ፡፡ በርሱ ምትክ ቢያንስ በተጠባባቂነት መሄድ የነበረበትን ወጣት አትሌት ንቀው ወይም የተፈለገውን ጉቦ ሳይሰጥ በመቅረቱ ሳይወስዱት ቀሩ፡፡ ያ አትሌት ደግሞ አለመመረጡን ሲረዳ ለግል ውድድር ወደውጭ ይሄድና አንደኛ ወጥቶ ብዙ ዶላሩን ያፍሳል፤ እንኳን በሁለት አልተበደለ፡፡ የሎንደኑ የ10000 ሜትር ሩጫ እንደነገ ሊደረግ እንደዛሬ ያ ልጅ እንዲመጣና ታመመ የተባለውን ‹ሽማግሌ› አትሌት እንዲተካ ቢጠሩት ሊመጣ አልቻለም፡፡ ቀድሞ ያላዘጋጁት ነገር በጭንቅ ወቅት ከወዴት ይገኛል? ተጠባባቂ አትሌት እንደመያዝ ሸቀጥ ነጋዴ የአትሌቲክሱ ፌዴሬሽን ባለሥልጣናት ዘመዶችንና ወዳጆችን አንጋፍፎ የዘመተው ቡድን ‹አስረክቤ መጣሁ› እያለ ወዳገር ሊገባ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ወግ ነው አሉ ሲዳሩ ማልቀስ፡፡ ሆኖም ቢሆን በለስ ለቀናቸው እነጥሩነሽና ቲኪ፣ መሠረትና ሌሎቹም ምሥጋናችን ይድረሳቸው፤ ሞክረው ያልተሳካላቸውም በጥረታቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ብቻ ሣይሆን ችግራችን ከመስቀያው ነውና ለታላቁ የሀገር ነጻነት ተባብረን እንነሣ፡፡ ይህ ትንሹ ነገር የታላቁ ቁስላችን ነፀብራቅ እንጂ በራሱ ሲታይ ትንሽ ነገር ነው – አመላካችነቱ ግን እጅግ ሰፊና ውስብስብ ነው፡፡ ከዚህ የባሰ ግፍና በደል በሀገር ላይ እየደረሰ ስለሆነ ለትልቁ ዓላማችን በኅብረት እንትጋ፡፡ ካለእጅ መንሻና ካለጎሣዊ የደም ትስስር የማትንቀሳቀስ ሀገር ተፈጥራልናለችና ከእስካሁኑ በበለጠ ብዙ ሥር ሳይሰድ የጋራ መፍትሔ እናፈላልግ፡፡ ነካካሁ እንጂ ምንም አልተናገርኩም፡፡ ከዚያው አካባቢ ውስጥ ዐዋቂ ካለ ይበልጥ ይግፋበትና ብዙ ነገር ያሳውቀን፡፡
No comments:
Post a Comment