No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Friday, 17 August 2012

የፓትርያርክ ጳውሎስ ገመና ፣ በደሎች ፣ መታሰቢያና ውርሶች


አዲሱ ተስፋዬ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን እስካሁን አምስት ኢትዮጵያውያን ፓትርያርኮች ተሹመው አልፈዋል:: ፓትርያርኮቹ የሚታወሱበት የተለያየ ባህርይና መታወሻan article about Abune paulos EGYPT ETHIOPIA AFRICAN UNION SIDELINES
ነበሯቸው:: ሰኔ 21, 1951 አ.ም የተሾሙት የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ እጅግ ሲበዛ ሊቅ እንደነበሩ ታሪክ ያስታውሰናል [1] :: ቤተ ክርስትያኒቱ የራስዋን ልጆች ፓትርያርክ አድርጋ እንድትሾም ፣ ከፍተኛ ተጋድሎ አካሂደው ቤተክርስትያኗ ነጻነት እንድታገኝ አድርገዋል[2] :: ህዝበ ክርስትያኑም ክርስትናውን እንዲያጸና ብዙ ታግለዋል :: ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅም የሳቸው ውጥን ነው [3] :: እሳቸው ሲያርፉ የተሾሙት ሁለተኛው ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስም የሳቸውን መስመር ተከትለው ለቤተክርስትያኒቱ ከፍተኛ አስተዋጾ አበርክተዋል [4] :: በተለይም ኢኮኖሚም የዳበረ አቅም እንዲኖራት በርካታ መሰረተ ልማቶችን አስገንብተዋል :: “እግዚአብሄር የለም” የሚለውንም የግፈኛው ደርግን አውራዎች በመቃወም ሰማእትነትን ተቀብለዋል [5]:: ሶስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ለእግራቸው እንክዋን ጫማ ለማጥለቅ የሚለመኑ ፣ በጾም ብዛት እንዳይሞቱ የሚሰጋላቸው ፣ አለምን ከነምኞቱ የሰቀሉ እውነተኛ መናኝና የእግዚአብሄር ሰው ነበሩ [6]:: በወቅቱ የነበረው የኢሰፓ መንግስት አዲስ አበባ የሚገኘውን አንድ ቤተ ክርስትያን “ዘግቼ ሙዚየም አደርገዋለሁ ” ብሎ ሲነሳ ” ሬሳዬን ተራምደህ ” በማለት የቤተክርስትያን የቁርጥ ቀን ልጅነታቸውን ያስመሰከሩ ትልቅ የእምነት አባት ነበሩ:: አራተኛው ፓትርያርክ መርቆሬዎስ አገር ለቀው እስካሁን በምድረ አሜሪካን ናቸው:: እሳቸው “ከመንበሬ በግፍ ተሰድጄ ነው የ ወጣሁት” ቢሉም ፤ በርካቶች ግን “መንበራቸው ላይ እስከመጨረሻው ጸንተው የሚመጣውን በመቀበል ታሪክ ፣ ቤተ ክርስትያንና ህዝብ እንዲያስታውሳቸው ቢሆኑ ይመረጥ ነበር“ ብለው ይነቅፉቸዋል:: እጅግ አወዛጋቢ የነበሩት አምስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስም ትናንት ነሀሴ 10/ 2004 አመተ ምህረት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል[7]::

ህልፈታቸውን አስቀድመው የተረዱ የሚመስሉት ፓትርያርክ ጳውሎስ ፤ የዘንድሮውን በአለ ሲመታቸውን( የሹመት በአላቸውን) ያከበሩት በከባድ ዝግጅት ነበር :: በአለ ሲመታቸው ሐምሌ 5/2004  በመጀመርያ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በከፍተኛ ሸብ እረብ የተከበረ ሲሆን ፣ ሐምሌ 16/2004 ደግሞ በሼራተን ሆቴል ድል ባለ ድግስ ተከብሯል :: [8] ቅጥ ያጣውን ድግስ የታዘቡ ወገኖች ” የቁም ተዝካር ” ብለው ተቃውሞ ቢያሰሙም ፣ ያላአግባብ የሚባክነውን ገንዘብና ሀብት ቢቃወሙም ፣ ድግሱ ለሶስተኛ ግዜ በክራውን ሆቴል ተደግሞአል:: በነዚህም ድግሶች ላይ ፓትርያርኩ 20 አመት ሙሉ ያከናውኗቸውን ” የፓትርያርኩን ሀያ ውጤታማ አምታት ስራዎች” የሚዘርዝር ዜና መዋእል አስጽፈውም ለታዳሚዎች ተበትኗል:: ፓትርያክ ጳውሎስ ግን ፣ እውን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ባለውለታ ነበሩን? በምን በምንስ ይታሰባሉ? What was the legacy of patriarch Paulos ?
መንፈሳዊ አምባገነንነት
ፓትርያርክ ጳውሎስ ከሹመታቸው ማግስት ጀምሮ የመጀመርያ ስራቸው የነበረው የቤተክርስትያኒቱን ስልጣን በሙሉ በሳቸው ቁጥጥር ውስጥ ማድረግ ነበር:: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የጥንት ትውፊትና ልማድ መሰረት የቤተ ክርስትያኗ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉዳይ ሀላፊዎች የተለያዩ ነበሩ:: መንፈሳዊው ጉዳይ የሊቃነ ጳጳሳቱና የፓትርያርኩ ሲሆን አስተዳደሩ ደግሞ የሚካሄደው በተክለሃይማኖት መንበር ላይ በተሾሙት እጨጌ ነበር:: [9]( በጥንቱ ልማድ የቤተመንግስቱ ሀላፊ አጼጌ ፣ አጼ ሲባል የቤተ ክህነቱ አስተዳደራዊ ሀላፊ ደግሞ እጨጌ ይባል ነበር) :: አባ ጳውሎስ ግን ይህ አስተዳደራዊ ማእረግ የፓትርያርኩ እንዲሆን ካደረጉ በሗላ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሀይማኖት ተባሉ :: በመቀጠልም የአክሱምን ሊቀ ጵጵስና ለብቻው ለይተው “ሊቀጳጳስ ዘአክሱም”  የሚለውን ደረቡ [10]:: “በመሰረቱ ፓትርያርኩ – ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ( የሊቀ ጳጳሳቱ ሁሉ የበላይ) ሆነው ሳለ እንደገና ወደታች ወርደው የአክሱምን ሊቀ ጳጳስትነት ለምን ፈለጉት?”  የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን ግራ ቢያጋባም መሰረቱ ግን ፖለቲካዊ መሰረት የያዘ እንደነበረ ፣ተንታኞች ምክንያቱን እንዲህ ይገልጻሉ:: “ያ ትውልድ ” እየተባለ በሚነገርለት የ1950ውና 1960ው ትውልድ “ ኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ያላት ሀገር እንጂ ጥንታዊ ሀገር አልነበረችም” የሚል አስተሳሰብ ይዘው በተነሱ ግራ ዘመሞች የተወጋ ነበር:: በነዚህ ግራ ዘመም ሀይሎች እይታ የአክሱም ስልጣኔ አክሱምን ብቻ እንጂ ሌላውን ኢትዮጵያ የሚመለከት አይደለም:: በነሱ ፓለቲካዊ እይታ ፣  አክሱም ላይ ተሹመው የነበሩት የመጀመርያው ያገራችን ጳጳስ አቡነ ፍሬምናጦስም የአክሱም ሊቀጳጳስ እንጂ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ አልነበሩም:: ስለዚህ የአክሱም ሊቀ ጵጵስና ከሌላው የተለየ እንደሆነ ፣ በዚያን ዘመንም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንዳልነበረች የማያሳምን ታሪክ ይዘው ይሞግታሉ :: የዛ ትውልድ አካል የሆኑት የኢትዮጵያው ፓትርያርክ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ የአክሱምን ሊቀ ጵጵስና ለብቻ ለይተው ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም የሚለውን ማእረግ መጠርያቸው ያደረጉት ምክያቱ ያ ከሆነም ወደፊት ታሪክ የሚያየው ይሆናል:: የአባ ጳውሎስ የስልጣን ጉዞ ግን በዚህ አልተገታም:: ሁለት ሺህ ዘመን ባስቆጠረው የቤተ ክርስትያኒቷ ትውፊትና ህግ መሰረት “የሲኖዶሱ የበላይ መንፈስ ቅዱስ ነው ” [11] የሚል ሐዋርያዊ ህግ ቢኖርም አባ ጳውሎስ “የቅዱስ ሲኖዶሱ የበላይ እኔ ፓትርያርኩ ነኝ” የሚል አዲስ ማሻሻያ ይዘው ብቅ አሉ:: በዚህ ወቅት ግን በርካቶች የኢትዮጵያ ሊቃውንትና ጳጳሳት ዝም ብለው አላዩአቸውም [12]:: ይልቁንም የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢ ታዋቂው ምሁር አለቃ አያሌው ታምሩና ሌሎች የቤተክርስትያኒቱ ሊቃውንት ባቀረቡት የመረረ ተቃውሞ ይህ ህግ ሳይጽድቅ ቀረ:: የሚሊኒየሙ በኣልም ሲከበር አባ ጳውሎስ ” የሚሊኒየሙ አባት” የሚለው ማእረግ እንዲደረብላቸው ተደርጓል[13]:: አሁን በቅርቡ ደግሞ “አለም አቀፍ የሰላም አምባሳደር” የሚለው ማእረግና ስያሜ ተመርቆላቸዋል[14]:: አሁን ያለውን የሳቸውን የስም ማእረግ ለመጻፍ ፣ ራሱን የቻለ ገጽ ሳያስፈልገው አልቀረም::
የተከፈለውና የተደፈረው ሲኖዶስ
አባ ጳውሎስ ሌላው የሚታወሱበት አብይት ጉዳይ በሳቸው ዘመንና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሳቸው ምክንያት የተከፈለው የቤተ ክርስትያኒቱ ሲኖዶስ ነው:: በኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የሁለት ሺህ አመት ታሪክ ውስጥ የቤተ ክርስትያኒቱ ሲኖዶስ ሲከፈል ይህ የመጀመርያው ነው:: ዛሬ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ቤተ ክርስትያኒቱ ባለ ሁለት ሲኖዶስ ሆናለች:: በሀገር ውስጥ አባ ጳውሎስ የሚመሩት ሲኖዶስና ፣ በውጭ ደግሞ አባ መርቆርዮስ የሚመሩት ሲኖዶስ[15]:: በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም ሲኖዶሶች ተወጋግዘዋል[16]:: ይሄ ክፍፍልና ብጥብጥ ግን በዚህ አላቆመም:: አባ ጳውሎስ የሚመሩት ያዲስ አበባው ሲኖዶስም ያለመግባባቱ ከባድ ደረጃ ላይ ደርሶ አባ ጳውሎስን የተቃወሙ ጳጳሳት ቤታቸው ተሰብሯል[17]:: እነሱም ተደፍረዋል:: ጉዳዩ ግን በዚህ አላበቃም:: ፓትርያርክ ጳውሎስ ስራተ ቤተ ክርስትያንን በጣሰ ሁኔታ ያስገነቡትን የራሳቸውን ሀውልት እንዲያስነሱ ቅዱስ ሲኖዶሱ ቢወስንባቸውም “እምቢኝ” በማለት ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ያላቸውን ንቅት በማሳየት አምባገንንተቻውን በግልጽ አሳይተዋል[18]:: በዚህም ለሲኖዶስ ውሳኔ ባለመገዛት የመጀመርያው ፓትርያርክ ሆነዋል::
የገዳማቱና አድባራቱ በደል
በአባ ጳውሎስ ሃያ የፕትርክና አመታት ክፉኛ ከተጎዱት የቤተክርስትያን ተቋማት አንዱ ፣ የኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው:: ትልልቅ የሚባሉት ገዳማት ፣ ተመልካችና ረዳት አጥተው ህልውናቸው አጠያያቂ የሆነው በሳቸው ዘመን ነው:: ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ይዞታ የነበረው በኢየሩሳሌም የሚገኘው የኢትዮጵያ ገዳም – ዴር ሱልጣን-  በኮፕቶች ያላሰለሰ ተንኮል የኢትዮጵያ ባላቤትነት ተሸርሽሯል:: በየሩሳሌም ያሉት መነኮሳት የተቻላቸውን ትግል ቢያደርጉም ካባ ጳውሎስ አሰተዳደር የተሰጣቸው ትኩረትና ድጋፍ ግን የወረደ በመሆኑ በተደጋጋሚ ለህዝቡ የደረሱልን ጥሪ ሲያሰሙ ነበር [19]:: ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ትላልቅ ገዳማትም የደረሰባቸው እጣ ተመሳሳይ ነው:: በቅርቡ እንዃን ታላቁ የዋድልድባ ገዳም ሲታረስ መነኮሳቱ ” ገዳማችን ታረሰ ” ብለው ላቀረቡት የድረሱልን ጥሪ ያቡነ ጳውሎስ አስተዳደር የሰጠው መልስ አጅግ አስገራሚ ነበር:: ምንም አንኳን የስኳር ፕሮጀክቱ የጋድሙን መሬት እስከ 16 ኪሎ ሜትር ዘልቆ ግበቶ ገዳሙን እንደሚያውከው የተለያዩ ጥናቶች ( በተለየ የማህበረ ቅዱሳን ሪፖርት [20]) በገልጽ ቢያስቀምጠውም ፣ ያባ ጳውሎስ አመራር ጉዳዩን በቸልታ በመመልከት ገዳሙን አሳልፎ በመስጠት መተባበሩን የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው:: በዚህ አመት ብቻ አራት ታላላቅ የቤተ ክርስትያኒቱ ገዳማት ላይ እሳት መነሳቱ ተዘግቧል:: አሰቦት ላይ በዚህ አመት እሳቱ የተነሳው አራት ግዜ ሲሆን ዝቋላ ሁለት ግዜ ነዷል [21]:; ጎንደር ውስጥም ብቸኛው የመጽሀፈ መነኮሳት የትርጉም ትምህርት ቤት ነዷል:: የቤተክርስትያኒቱ መሰረት የሆኑት ገዳማት መቃጠላቸው ያስቆጫቸው፤ በየገዳሙ ያሉትን የመንኮሳት ጥሪ መሰረት አድርገው ፣ በከፍተኛ መንፈሳው ቅናት እሳቱን ለማጥፋት እየተቃጠሉ ወዳሉት ገዳማት የተመሙትም ምእመናን አባ ጳውሎስ ከሚመሩት ቤተ ክህነት የተሰጣቸው መግለጫ እጅግ አሳዛኝ ነበር:: ገዳምትን ብቻ እየመረጠ የሚያቃጥል እሳት ምክንያቱ እንዲጣራ ምእመናኑ ላቀረቡት ጥያቄ ፣ ያባ ጳውሎስ አስተዳደር የሰጠው መልስ ይሄንን ነበር –” እሳት በመንደርም ይነሳል:: በገዳማት ቢነሳ ምን ያስደንቃል:: ይህንን የምታራግቡት ለራሳችሁ የፖለቲካ ፍጆታ ነው::” [22]በማለት እጅግ የሚገርም መልስ በመስጥት ለገዳማቱ ያላቸውን መቆርቆር አሳይተውናል:: በያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስትያን የሚይታየውም የቤተ ክርስትያንን መብትና ህልውና አሳልፎ የመስጠት ነገር ተነግሮ አያልቅም:: ለዚህም ጥሩ አብነት የሚሆነው የደብረዘይቱ ምስራቀ ጸሀይ ባቦጋያ መድሀኔአለም ቤተ ክርስታያን አንዱ ነው:: ለረጅም ዘመናት የቤተክርስታይኑ የጥምቀተ ባህር ቦታ የነበረው የቤተክርስትቲያኑን የጥምቀተ ባህር ማክበርያ ቦታ ፣ በኮሬፍቱ ሪዞርት ባላቤት ሲወሰድ፣ ምእመናን ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው ነበር:: አስገራሚ በሆነ  መልኩ የአባ ጳውሎስ ቤተ ክህነት ተወካይ ያደረገው ነገር ግን ፤ ባህረ ጥምቀቱ ላይ የነበረውን መስቀል በመቁረጥ ቦታውን ለሆቴሉ አሳልፎ በመስጠት ምእመናኑን አንገት ማስደፋትና እምቢ ያሉትንም በፍርድ ቤት በሀሰት ከሶ ማሳሰር ነበር [23]:: ይሄ የሆነው እዛው ካዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር የምትገኘው ደብረ ዘይት ላይ ነው:: በየዳር አገሩ በመናፍቃንና በአክራሪዎች ቤተ ክርስትያን እንደ ችቦ ስትጋይ ፣ ምእመናን ሲታረዱ ያባ ጳውሎስ ቤተ ክህነት አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ በዝምታ ከማለፍ ውጭ ያደረገው ነገር እንደሌለ ጸሀይ የሞቀው እውነት ነው::
የምእመናን ጠባቂ ማጣትና ውጤቱ
ፓትርያርክ ጳውሎስ ስልጣን ሲይዙ የኢትዮጵያ ህዝብ 50% እና በላይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነበር[24]:: የ1987 የህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ህዝብ ግማሹ የተዋህዶ እምነት ተክታይ ነበር:: የቅርቡ ህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት እንደሚያሳየው የኦርቶዶክስ እምነት ተክታይ ከ50% ወደ 43.5 % ወርዷል[25]:: ይህ በቁጥር ሲሰላ ደግሞ እጅግ በዙ ሚሊዮን ነው:: ቤተ ክርስትያኒቱ ይህን ሁሉ ህዝብ ያጣችበት ዋናው ምክንያት ያባ ጳውሎአ አስታዳደር ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ሌሎች ነገሮች ላይ በማትኮሩና ምእመናኑም እረኛ በማጣታቸው ነው:: ፓትርያርክ ጳውሎስ የሚታወቁትና የሚታወሱት ትልልቅ የስብከተወንጌል መርሀግብሮችን አዘጋጅተው በመክፈት ሳይሆን እጅግ በሚገርም ሁኔታ እንደ ቢዮንሴ ያሉ ዘፋኞችን በመቀበል ነው:: አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የቦብ ማርሊ የልደት በአል ለማክበር የተዘጋጀውንም የዘፈን ድግስ በጸሎት በመክፈት የእምነቱን ተከታዮች ክፉኛ ማሸማቀቃቸውና ማሳፈራቸውም የቅርብ ሩቅ ትዝታ ነው::
ሲጠቃለል
አምስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ጳውሎስ ከሚታወሱብት በጎ ነገር ፣ የሚወቀሱበት ክፉ ነገር የበዛና ቤተ ክርስትያኗን ለከፋ አደጋና ጉስቁልና አሳልፈው የሰጡ አባት ነበሩ:: በኢትዮጵያ ታሪክ የገማ እንቁላልና የሰበሰ ቲማቲም የተወረወረባቸው ብቸኛ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ናቸው:: እንደሳቸውም ከምእመንና ካህናት ተቃውሞ የገጠመው ፓትርያርክ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም:: የፓትርያርክ ጠባቂዎች ቤተ ክርስትያን አውደ ምህረት ላይ ባህታዊ ተኩሰው የገደሉት በአባ ጳውሎስ ዘመን ነው:: ሰላምን ፈልገው ቤተ ክርስትያን ተጠልለው የነበሩ ተማሪዎችንም አሳልፎ በመስጠት አባ ጳውሎስ ይወቀሳሉ:: ከሊቃውንቱም ጋር በነበራቸው ጸብ በሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን የተወገዙ ብቸኛው ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ ናቸው:: አለቃ አያሌው ገዝተውና አውግዘዋቸው እንዳለፉ ይታወሳል:: ቤተ ክርስትያኗም ለሶስት የተከፈለችው( ያዲስ አበባ ሲኖዶስ የውጭ ሲኖዶስ እና ገለልተኛ) በሳቸው ምክንያት ነው:: ተሐድሶ በማለት ቤተክርስትያኒቱን ሊያፈራርስ የተነሳው ሀይልም ቤተ ክርስትኒቷን እንዲህ እያወካት ያለው በሳቸውና አማካሪዎቻቸው ለፈስፋሳ አቛም ምክንያት ነው:: ለብዙ ሺህ አመት የቆየውም የጳጳሳት አለባበስ ከጥቁር ወደ ነጭ የተቀየረውም በሳቸው ዘመን ነው:: በታሪካችን ለመጀመርያ ግዜ ሀውልት ለራሳቸው ያሰሩ ፓትርያርክም እሳቸው ብቻ ናቸው[26]:: ሌላም ሌላም ሌላም
ቢሆንም ግን አባ ጳውሎስ የሚመሰገኑበትም ጉዳይ አለ:: “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅባት”  የሚል አዲስ ድርጅት ፈጥረው ቤተ ክርስትያኒቱን ለሁለት ሊሰነጥቁ የነበሩትን የቅባቶች የቅርብ ግዜ እንቅስቃሴ በመግታት ቤተክርስትያኒቱን ከመከፈል ማዳናቸው ሁሌም ሲያስመሰግናቸው ይኖራል:: ግዜው ካለፈ በኋላም ቢሆን “የተሀድሶ መነኮሳት ህብረት” በማለት የቤተክርስትያኒቷን አስተምህሮ ለመናድ በተነሱ መናፍቃን ላይም የወሰዱት የማውገዝ እርምጃ ቤተ ክርስትያኒቷን ከጥፋት አድኗልና ይታወሱበታል:: ለቤተ ክርስትያን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ እንደ ማህበረ ቅዱሳን ፣ ማህበረ በአለ ወልድ፣ ጽርሀ ጽዮንና የመሳሰሉ ማህበራትን ፈቃድ ያገኙትና እንዲሰሩም የተፈቀደላቸው በሳቸው ዘመንና በጎ ፈቃድ በመሆኑ ምስጋና ይግባቸው::ያሰሩት የመንበረ ፓትርያርክ ህንጻና አሁንም አስጀምረውት የሄዱት የአክሱም ሙዚየም ለቤተክርስትያን ቅርሶች ናቸውና በዚህ በጎ ስራቸውም ይታወሳሉ::በቅርቡ ቤተክርስቲያኒቷ ያሳተመችው ሰማንያ አሀዱ ቤተክርስትያንም በሳቸው ዘመን የሆነ ነውና ይህን በማድረጋቸው የቤተ ክርስታያን ታሪክ ያስታውሳቸዋል::
ግን በአባ ጳውሎስ ምክንያት የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ላይ የደረሰው ጠባሳና ቁስል በቀላሉ የሚጠገን አይደለም:: የተሰበረውን የሚጠግኑ ፣ የቆሰለውን የሚያክሙ መንፈሳዊ አባት እግዚአብሄር ለቤተ ክርስትያናችን ይሰጠን ዘንድ የተዋህዶ ምእመናን ሁላችንም ካሁኑ እንጸልይ:: የቤተ ክርስትያን አምላክ ቸሩ እግዚአብሄር የቤተክርስትያናችንን ትንሳኤ ያሳየን::
አባ ጳውሎስም ወደ እውነተኛው ቦታ ሄደዋል:: ፍርዳቸውንም ሁሉን ከሚያይ ከእውነተኛው ፈራጅ ከቅዱስ እግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላሉ:: ነብሳቸውን ይማር!!!
ወስብሀት ለእግዚአብሔር!
ዋቤ መጻሕፍት

1 ዜና ባስሌዎስ ሊቀጳጳሳት :: ሰኔ 10/ 1951:: ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተምያ ቤት
[2] ዜና ባስሌዎስ ሊቀጳጳሳት :: ሰኔ 10/ 1951:: ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተምያ ቤት
[3] የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን የመጀመርያው ፓትርያርክ :: አዲስ አበባ 1956::ብርሃንና ሰላም ቀዳማዊ ሀይለስላሴ
ማተምያ ቤት ::
[4] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 አ.ም :: አዲስ አበባ 2000
አ.ም::
[5] http://www.dacb.org/stories/ethiopia/tewoflos2.html
[6] የሶስተኛው ፓትርያርክ በኣለ ሲመት:: ነሀሴ 23/ 1968:: ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተምያ ቤት
[7] http://www.bbc.co.uk/news/world-africa-19285459
[8] http://www.dejeselam.org/2012/07/blog-post_26.html
[9] የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን የመጀመርያው ፓትርያርክ :: አዲስ አበባ 1956::ብርሃንና ሰላም ቀዳማዊ ሀይለስላሴ
ማተምያ ቤት ::

[10] የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 አ.ም :: አዲስ አበባ 2000
አ.ም::
[11] ፍትሐ ነገስት :: 1978 :: አዲስ አበባ::
[12] http://www.aleqayalewtamiru.org/
[13] http://www.aleqayalewtamiru.org/
[14] http://www.dejeselam.org/2012/07/blog-post_29.html
[15]www.eotcdc.org/documents/Wegezet.pdf
[16]www.eotcdc.org/documents/Wegezet.pdf
[17] http://www.dejeselam.org/2009/07/blog-post_16.html
[18] http://www.youtube.com/watch?v=mpzFq0gmX0Y
[20] http://eotcmk.org/site/images/stories/pdfs/MK_Walideba_Final_Report1.pdf
[21] http://www.youtube.com/watch?feature=player_embedded&v=oGieo5lQd3s
[22] http://www.dejeselam.org/2012/03/blog-post_3709.html
[23] http://andadirgen.blogspot.com/2012/06/13.html
[24] http://www.google.com/hostednews/afp/article/ALeqM5i-WtiPcdGx83wuVl-kZ8ZT8tQGRg
[25] http://www.google.com/hostednews/afp/article/ALeqM5i-WtiPcdGx83wuVl-kZ8ZT8tQGRg

No comments:

Post a Comment