No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Thursday 9 August 2012

የጠፋ ሰው ዳገት ላይ ሲገኝ…!!የሽግግሩ ሰው!!…

ዳንኤል ገዛኽኝ ከዳንኤል ገዛኽኝ
አቤት ጊዜው እንዴት ይሮጣል ? በጣም ይሮጣል። ስለጊዜው መሮጥ የማወሳው ወደሁዋላ ሰባት አመት ተመልሼ ትውስታዬን የሁዋልዮሽ ሳጠነጥን ነው። አስታውሳለሁ ምርጫ 97/2005 እየተቃረበ ነው ቢያንስ ቢያንስ የስምንት ወር ያህል ጊዜ ይቀረው ነበረ። ከ እለቶች በአንዱ እኔ እና ጉዋደኛዬ መሃል ፒያሳ ከማህሙድ ሙዚቃ ቤት አካባቢ ወደ ቼንትሮ ፓስትሪ ጎራ ብለን ቡና ለመጠጣት እያዘገምን ሳለን…ጉዋቅደኛዬ ባየው ነገር ተገርሞ… “ይሄንን መኪና ትመለከተዋለህ ?…” በማለት ይጠይቀኛል…እኔም መኪናውን ተመልክቼ አዎ አዎ አየሁት አልኩት። በ እርግጥ የተለየ ነገር ለጊዜው ባላስተውልም እሱ ግን ሆን ብሎ የመኪና ሞዴሎችን ማድነቅ ዋጋውን መከታተል ያዘወትር ነበር እና እና ምንድነው ? አልኩት መልሼ ጥያቄውንም በጥያቄ። “ይሄ መኪና ማንም ሃብታም እጅ አልገባም…እርግጥ የ እኛ ሃገር ሃብታሞች አደጉ የሚባሉት ሃገሮች ውስጥ የሚገኙ ሃብታሞች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚይዙት መኪና በተጋነነ መልኩ ውድ መኪና በመያዝ ቢታወቁም ይሄ መኪና ግን ለጊዜው ሃገራችን ያለው በአንድ ግለሰብ እጅ ብቻ ነው…” ማን ነው እሱ በማለት ብቻ ጊዜ ሳላጠፋ የመኪናውን አይነት ለማየት መለስ አልኩኝ። መኪናው ክራውን ኮሌጅ ትይዩ ማህሙድ ሙዚቃ ቤት ፊትለፊት ነበረ እና የቆመው በደንብ አየሁት። እውነትም ምን አልባት በፊልም ካልሆነ ያንን አይነት መኪና ከዚያ ቀደም ብዬ እንዳላየሁ አረጋገጥኩ። ጂ.ኤም.ሲ የሚሉ የ እንግሊዘኛ ፊደሎች ከፊትለፊቱ በቀይ ይታዩበታል። ድፍን ያለ ጥቁር መኪና ነው ሁሉ ነገሩ ጥቁር መኪና ሲበዛ የቅንጦት መኪና እንደሆነ አያጠራጥርም። መኪናውን ዙሪያውን በደንብ ካየን በሁዋላ ከጉዋደኛዬ ጋር ሲኒማ አምፒር ፊትለፊት ከሚገኘው ቼንትሮ በረንዳ ላይ አረፍ አልን እና ቡናችንን እንዳዘዝን ጉዋደኛዬን… እና ታዲያ መኪናው የማን ነው ? አልኩት። “የዶክተር ፍሰሃ ነዋ…” ሲለኝ…ዶክተር ፍሰሃ ዩኒቲ ኮሌጅ ? አልኩት መልሼ… “አዎ ልክ ነህ” አለ እና
አረጋገጠልኝ። ታዲያ ዶክተር ፍሰሃ በ እርግጥ የተሳካላቸው ሃብታም ናቸው ይህንን መኪና ለመግዛትም ያን ያህል የሚቸገሩ ሰው አይደሉም ምንድነው አንተን ያስገረመህ ብዬ አልኩት ነልሼ። “የተለየ አስገራሚ ነገር ባይኖርም ሰውየው ግን የዘመኑ ሰው ናቸው ይባላሉ” ሲል ጥርጣሬውን ሰነዘረ ጉዋደኛዬ። እኔም ለማከል ያህል እሱማ ጥርጣሬውን ግልጽ የሚያደርግ ታሪክ አለ አልኩት ጉዋደኛዬን። “ምን አይነት ታሪክ ?” ሲል ጥያቄ ሰነዘረ። ጉዋደኛዬ እኔ ስለማነሳው ጉዳይ የሚያውቀው ባለመኖሩ ትረካዬን ቀጠልኩኝ። አስታውሳለሁ ከሚያዝያ 1993 በሃገራችን አቆጣጠር መሆኑ ነው ከስምንት ወራት በፊት አንድ የሚዲያ ተቁዋም ሊመሰረት ዶክተር ፍሰሃ ትልቅ ሽርጉድ ይጀምራሉ። አንደኛው ሬድዮ ሁለተኛው ደግሞ ሳምንቱን ሙሉ በየቀኑ በህትመት ላይ የሚውል ጋዜጣ ነው። ሬድዮው ዩኒቲ ድምጽ የሚባል ሲሆን በአሁኑ ሰአት በወያኔ በመለስ ዜናዊ ሚስት በአዜብ መስፍን ስፖንሰር አድራጊነት የሚታተመው ኢትዮ-ቻናል ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ሳምሶን ማሞ አጋፋሪነት የሚመራ ሬድዮ ነበረ ዩኒቲ ድምጽ በ ኤፍ.ኤም 97.1 ስርጭት ላይ የአየር ሰአት በመከራየት የሚተላለፍ ሬድዮ ነው። ባለቤትነቱ የ ዶክተሩ ነው። ወደጋዜጣው ስመለስ ታዲያ እለታዊ አዲስ የሚል ስም ያለው ሲሆን ጋዜጣው እንደመንግስታዊው አዲስ ዘመን ቁመቱ ረጅም ሲሆን ጎኑ ደግሞ ከ ዘመን አነስ ይላል። የጋዜጣው አመሰራረት በራሱ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ያሉት ሲሆን ውሎ አድሮ ግን እውነታውን በተለይ የሚዲያ ሰዎች ለመገንዘብ ችለናል። እለታዊ አዲስ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ሽርጉድ በሚባልበት ወቅት አንድ መግለጫ ቢጤ ተዘጋጀ እና በዚያ ሚዲያ ውስጥ ለመስራት ፎርማሊቲ ያሙዋሉቱ በተለይ የሚሰማቸውን እንዲጠይቁ መድረኩ ተመቻቸ። የሆነው ሆኖ እኔም ታዲያ በዚያ ውስጥ ለመስራት ከገቡቱ ውስጥ ባልሆንም ግን በጊዜው ከስፍራው ላይ የመገኘት እድል አጋጥሞኝ ነበረ። እና በወቅቱ የታደሙት ጋዜጠኛዎች በአብዛኛው ማለት ይቻላል እንቶ ፈንቶ ጥያቄ ሲያግተለትሉ ዛሬም ድረስ የማልረሳው በሚጽፋቸው ፖለቲካ ቀመስ ፊቸሮቹ ብዙዎቻችን የነጻው ፕረስ ጋዜጠኛዎች የምንወደው እና የምናከብረው ጋዜጠኛ ተድባበ ጥላሁን እድል ሲያገኝ ለዶክተር ፍሰሃ በጣም ፈታኝ ጥያቄ ያቀርብላቸዋል። አስታውሳለሁ ቃል በቃል አይረሳኝም የተድባበ ጥያቄ። በቅድሚያ የዶክተሩን ገለጻ በግርድፉ ላስታውስ። “እኛ ይህንን የጋዜጣ የሚዲያ ስራ ስንጀምር ሃሳባችን የመናገር ነጻነት እንዲስፋፋ እና መረጃን ለህዝቡ ለማድረስ ካለን ጉጉት እንጂ ጋዜጣ ሸጠን ትርፍ ለማግኘት አይደለም…” የሚል አንድምታ ነበረው ሃሳባቸው። ይሁን እና ተድባበ በዚህ ንግግራቸው ላይ ምሳሌ በመጥቀስ ተናግሮ ጥያቄውን አስከተለ። “ከዚህ ቀደም አሉ የሚባሉ ታዋቂ የቢዝነስ ሰዎች ልክ እርስዎ እንዳሉት ባለሙሉ ቀለም ጋዜጣ ለመጀመር አቅደው አሉ የሚባሉ ሙያተኛዎች ቀጥረው ስራ ይጀምራሉ። ሃሳባቸው የነበረው ጋዜጣውን መሸጥ እና ማትረፍ አልነበረም። እዚህ ሃገር ደግሞ የህትመት እና የወረቀት ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ ሳቢያ የተባለውን ያህል ለመሄድ አስቸጋሪ መሆኑ የታወቀ ነው። በዚህ የተነሳ የጠቀስኩዋቸው ሰዎች በኪሳራ ምክንያት ስራውን በማቆም ጋዜጣውም ከህትመት ውጪ ሆነ። እርስዎስ በዚህ በኩል ምን ያህል ተዘጋጅተዋል ? ይህ እንደማይሆንስ ለጋዜጠኛው ማለትም በዚህ ጋዜጣ ላይ ተቀጥሮ ለሚሰራው ጋዜጠኛ ምን ዋስትና አለ ?…” በማለት ይጠይቃቸዋል። ዶክተሩ መልስ ከመስጠታቸው በፊት ሳቅ አሉ እና ንግግራቸውን ጀመሩ። “ይሄ ፈጽሞ እናንተን ሊያሳስባችሁ አይገባም እኛ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰፊው አስበንበታል ስለዚህ በገንዘብ በኩል ኪሳራ መጥቶ ጋዜጣው ይዘጋል የሚል ስጋት እንዳይገባችሁ…ስለዚህ ስራችሁን ብቻ በነጻነት ስሩ የናንተ ሃላፊነት ይሄ ነው…” በማለት በሰፊው አተቱ። እለታዊ አዲስ ጋዜጣን በመንግስት ጋዜጣ በተለይም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና በ ኢትዮጲያ ሬድዮ ከአስራ አምስት አመታት በላይ ያገለገሉ ጉምቱ ጋዜጠኛዎች ዶክተሩ ያቀረቡቱ የደሞዝ በረከት አጉዋጉቶዋቸው ስራቸውን ለቀው ተቀላቀሉ። ከነጻው ፕሬስም በርካታ ጋዜጠኛዎች ወደ እለታዊ አዲስ ጎረፉ። በቀላሉ አጠቃላይ ወደ አንድ መቶ ሃምሳ በሚደርሱ ጋዜጠኛዎች እና ልዩ ልዩ ሰራተኛዎች ጋዜጣው ስራውን ጀምሮ ለስምንት ወራቶች ዘለቀ። ጋዜጣው ለስምንት ወራቶች ሲዘልቅ በርካታ ፖለቲካዊ ሃገራዊ…ማህበራዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በስፋት እየዳሰሰ በየ እለቱ ያለማቁዋረጥ በህትመት አየር ላይ ቀጠለ። የሆነው ሆኖ ሚያዝያ 1993 ላይ ግን ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ/ህውሃት ለሁለት ተሰነጠቀ። በትግል ወቅት ሳሉ ከተከፈሉበት ታሪክ የሚለጥቀው ህውሃት ህንፍሽፍሽ ሁለት ተከሰተ። የ እለታዊ አዲስም ጋዜጠኛዎች በወቅቱ የሃገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት ከፍ ያደረገውን የክፍፍሉን ጉዳይ በፊት ገጹ ይዞ ለንባብ ይበቃል። በጉዳዩ ደማቸው የፈላው ዶክተር ፍሰሃም የ እለታዊ አዲስ ሃላፊዎችን እያንዳንዱ የጋዜጣው ሰራተኛ ስራ እንዲያቆም ያሳስባሉ። በዚህ አላበቁም ማስታወቂያ በመለጠፍ ጋዜጣው እንደማይታተም የሚጠቁም ማስጠንቀቂያ ይለጠፋል። እናም ጋዜጠኛዎቹ የጋዜጣው የበላይ ሃላፊዎች በመሆን ዶክተሩን ለማናገር እና ሁኔታውን ለመወያየት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ይቀር እና ሁሌም በጋዜጠኛው ጉዳይ የበኩሉን ሁሉ በማድረግ የሚታገለው ኢነጋማ በጋዜጣው ሃላፊዎች ስታፍ ቢሮ በብሄራዊ ሆቴል መግለጫ በማዘጋጀት ለአለም የፕሬስ ተቁዋማት ጥሪ በማቅረብ አንድ መቶ ሃምሳ ጋዜጠኛዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ያለቅድመ ሁኔታ አደጋ ላይ በጣለ ሁኔታ ዶክተሩ የፈጸሙት ተግባር ተገቢ አለመሆኑን እና ለጋዜጠኛዎቹ የስራ መፈለጊያ ደሞዝ እንዲከፍሉ ለዶክተሩ ጥሪ ያቀርባል። ዶክተር ፍሰሃ ግን ያንን ሁሉ ጋዜጠኛ በትነው በዝምታቸው ይጸናሉ። በዚያ አልቆመም ዩኒቲ ድምጽ የሚባለውንም ሬድዮ ይዘጉታል። የሆነው ሆኖ ግን ነገሩ ሌላ ነበረ። ዩኒቲ ኮሌጅ ያንን የሚዲያ ተቁዋም ሲመሰርት ከጋዜጣው እና ከጋዜጠኛዎቹ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላት የዋሽንግተን ፖስት የአዲስ አበባ ዘጋቢ የሪፖርተሩ የአቶ አማረ አረጋዊ ቅምጥ ልበላት ውሽማ ጄኒፈር ፓርመሊ በሂልተን ሆቴል ሙሉ ወጪዋ እየተሸፈነ የ እለታዊ አዲስ ጋዜጣ አማካሪ ተብላ ተቀምጣለች። በወቅቱ ከታማኝ ምንጮች የሚገኙ መረጃዎች የሚያመለክቱት እውነት ታዲያ ለሴትየዋ በመቶሺዎች የሚቀጠር ዶላራት ወጪ ይደረግላት ነበር። ይሄ ገንዘብ ታዲያ በዚያ ፕሬስ ላይ እንዲውል ለጋዜጠኛውም በቂ ደሞዝ እንዲከፈል ከነዋሽንግተን ፖስት ስፖንሰር የተደረገ ነበረ። አስገራሚው ነገር ታዲያ እቺ የዋሽንግተን ፖስት የአዲስ አበባ ዘጋቢ ከዚህ ቀደም ኢነጋማ የ 100 ሃገራትን ድምጽ አግኝቶ በቴይፔ የፍሪደም አዋርድ ሲሸለም የኢትዮጲያ ነጻ ፕረስ ጋዜጠኛዎችን በማብጠልጠል ሽልማቱ ለፕሬሱ ሳይሆን ለአማረ አረጋዊ እንደሚገባ ከፎርቹኑ ታምራት ወልደጊዮርጊስ ጋር ሽንጥዋን ገትራ የተከራከረች የኢትዮጲያ ፕረስ ጠላት ነች። ግን ደግሞ በሌላ በኩል በፕሬሱ ስም በዶክተሩ አጋፋሪነት የመጣን ሚሊዮን ዶላሮችን የተቀራመተች አስፋሪ ሰው ናት። የዚህ ሁሉ ጉዳይ አጋፋሪ ደግሞ ዶክተሩ ናቸው። መቼም ሰው ደካማ ጎኑ ሲነሳ ጠንካራ ጎኑንም ማንሳት የግድ ነው እና ሰውየው ዶክተሩን ማለቴ ነው በአነስተኛ የቁዋንቁዋ ትምርት ቤት የጀመሩትን እንቅስቃሴ ወደ ኮሌጅ በሁዋላም ወደ ዩኒቨርስቲ በማሳደግ የትምርት ጥራቱ የተጠበቀ እና ትውልድን የሚቀርጽ ሆኖ እንዲወጣ በማድረጉ በኩል የተሳካላቸው ሰው ናቸው። ቢሆንም…ቢሆንም ግን ፕረስ ከመሰረቱ በሁዋላ የህውሃት መከፋፈል ተዘገበ ብለው ፕረሱን ዘግተው ጋዜጠኛውን መበተናቸው እስካሁንም ያልረሳነው አሳዛኝ አሳፋሪም ስራቸው ነው። ለምንስ ይሆን አብ ሲነካ ወልድ ይነካ በሚያሰኝ ብሂል የ 1993 ሚያዝያ ወር የወያኔ ክፍፍል መዘገብ ንዴታቸውን አንሮት ያንን ሁሉ ጋዜጠኛ የበተኑት ? ለምን ይሆን ? እንግዲህ ዶክተር ፍሰሃ በቅርቡ የሽግግር ምክር ቤት አቁዋቁመዋል። ምስረታውንም እውን አድርገው ምርጫም አካሂደዋል። በሰጡት መግለጫ ከአንደበታቸውም እንደሰማነው የመንግስት ባለሰልጣናት በተለይ አዜብ መስፍን አላሰራ ብላቸው ሃገር ለቀው በመውጣት ለኢትዮጲያ ሰላም ዲሞክራሲ እንዲመጣ እንደሚታገሉ አሳስበዋል። ይህ የሆነው በ እርግጥ ዛሬ ነው። የሆነው ሆኖ ግን በ 1997 ከምርጫው በሁዋላም ሆነ በምርጫው ወቅት ሃገራችን ላይ ያሁሉ ጭፍጨፋ እና ዘግናኝ ተግባር ሲፈጸም ዶክተር ፍሰሃ የት ነበሩ ? በዚህ አያበቃም። ከስልሳ ሚሊዮን ብር በሚልቅ ገንዘብ ዩኒቨርስቲያቸውን ለ ሼክ መሃመድ ሁሴን አላሙዲን ሸጠው ካገር ሲወጡ ምክንያት ብለው ያቀረቡት እረፍት እፈልጋለሁ የሚል ነበረ። ያም ሆነ ይህ ሁሉም ከሆነ በሁዋላ አሁንም ስለ ዶክተር ፍሰሃ እሸቱ እምነት የሌላቸው ኢትዮጲያውያን የፖለቲካ ታዛቢያን እና ዜጎች በርካታ ናቸው። ይህ የሚሆነውም ከሰውየው ቆየት ያለ የጀርባ ታሪክ አንጻር ነው። ተንታኞች እና እውነተኛ ኢትዮጲያውያን ጥርጣሬያቸው ሰፊ ነው። ሰውየውን በሁለት ጎራ ይመለከቱዋቸዋል። አንደኛው ከውጪው አለም አንድ ትልቅ ቡድን ጋር እናም ይህ ቡድን መለስ ዜናዊ ቀደም ብሎ በበሽታቸው ሳቢያ እዚህች አለም ላይ የሚኖረው እድሜ ውሱን መሆኑን እና መሞቱም እርግጥ መሆኑን ከህክምና ባለሞያዎች መረጃ በማግኘታቸው ሳቢያ እኚህን ዶክተር ለሽግግር ስር አት እንደመለመሉዋቸው…ሌላው ደግሞ ሰውየው አልሸሹም ዞር አሉ አስመሳይ ስር አት ለመምስረት እንደቁዋመጡ ይናገራሉ እውነታው ግን የቱ ይሆን ? ሲደርስ የሚታወቅ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን በርካታ ኢትዮጲያውያን ደግሞ በወሳኝ ወቅት ለ ኢትዮጲያ የደረሱ ወሳኝ ሰው ናቸው በማለት ነው ዶክተሩ ይዘው የተነሱትን የፖለቲካ አቅጣጫ በማወደስ የሚናገሩላቸው። እንዳውም ጥሩ የፖለቲካ አማራጭ ያለው ቡድን በጠፋበት በዚህ ኢትዮጲያ መንታ መንገድ ላይ በሆነችበት ጊዜ ሰው ሲጠፋ ዳገት ላይ የተገኙ ኢትዮጲያዊ አዲስ የፖለቲካ ሰው ናቸው ሲሉ ያሞካሹዋቸል። እውነት እኚህ በስንት ፈታኝ ወቅት ጠፍተው ከርመው ዛሬ ደግሞ በከፋው ወቅት ላይ የተገኙ የፖለቲካ ሰው ይሆኑ ? ከሆነ እሰየሁ። ካልሆኑ ግን እንጃ የዚያን ጊዜ አበቃሁ። ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኽኝ በኢትዮጲያ ነጻው ፕሬስ በጋዜጠኝነት ያገለገለ ሲሆን በቅርቡ ሲዋን የተሰኘ መጽሃፍ ለህትመት አብቅቶዋል።

No comments:

Post a Comment