No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Wednesday 8 August 2012

ባርያ ቢሸፍት ከጌታው ጓሮ ነጭ አምላኰች አቤቱታ,,,


Aug/2012
ምንም እንኳን የባርያ ስርዓትን የምቃወምና የማወግዝ ብሆንም በዚህ ስርዓት ወቅት በነበረው ግንኙነት የተማረረ አንድ ባሪያ ጭቆናው አንገፍግፎት በጌታው ላይ ተነስቶ የመሸፈቱን ወሬ እንደሰማሁት ሌላውም የሰማው ይመስለኛል።
ታዲያ ያ የባርነት ሰንሰለትን ለመበጠስ የሸፈተ ባሪያ ዕድሜ ልኩን ከጌታው ግቢ ወጥቶ ስለማያውቅ፣ለሱ የመጀመሪያም የመጨረሻም የሚያውቀው ዓለም ሌት ተቀን እየኮተኮተና እያጸዳ ሲሰራ የኖረበት ሰፊ ጓሮ ብቻ ነበር።አመጽ ባሰበበትና በሸፈተበትም ወቅት ለመሰወር ፣ምሽግና ከለላ አድርጎ የመረጠው በዛው በጌታው ግቢ ውስጥ ከሚገኘው ቁጥቋጦ ውስጥ ሆነ።ውሎ ሳያድር እርቆ ሳይሄድ ምህረት ጠየቀና መልሶ ከኖረበት ገረገራ ውስጥ ገባ።ሸፍቶ ነጻ ላይወጣ፣ከጌታው ጋር አጉል ቅያሜ ፈጥሮ ሰንሰለቱን አጠበቀ ይባላል።
ይህን ታሪክ ያነሳሁት ላለምንም አይደለም።ባለፈው እሁድ ከቤተክርስቲያን መልስ እቤቴ አረፍ ብዬ በዕለቱ የሚተላለፈውን የአካባቢዬን ራዲዮ የአማርኛ ፕሮግራም ሳዳምጥ ጉዳዩ ተነስቶ የተሰነዘረው ሃሳብና ትችት የግል አስተያየቴን እንድሰጥበት ስለቀሰቀሰኝ ነው።

ጉዳዩ ሰሞኑን በኢትዮጵያውያኖች የተቃዋሚ ጎራ ከተሰለፈው ተቃዋሚ ነኝ ባይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ስም የተቋቋመው አደናጋሪ ድርጅት በመፈጸም ላይ ያለው አድራጎት ከዚያ ከባርነት ሰንሰለት ካልተላቀቀው በጌታው ላይ አምጾ በጌታው ግቢ ውስጥ ሲንከባለል የተገኘውን ባሪያ ታሪክ መስሎ ስለታየኝ አድራጎቱን ለሌሎቹ ለማሳየት የመጻፍ ልምዱና ድፍረቱ ባይኖረኝም የግድ ብእሬን ለማንሳት ተገድጃለሁ።
በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የወያኔን ስርዓት ያሰፈኑት፣የአገዛዝ ዕድሜውን ለማራዘም የገንዘብ፣የፖለቲካ፣የዲፕሎማሲና የመሣሪያ እርዳታ እየሰጡ አይዞህ በርታ እያሉ የሚንከባከቡት፣ተቃዋሚ ሲገደል፣ሲቆስል፣ሲታሰር፣ሲሰደድ ምንም ሳይሰማቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው እንደውም በአሸባሪነት እያወገዙ ለግፈኛው ስርዓት ያልተቆጠበ የሞራል ድጋፍ በመስጠት ላይ ያሉት የውጭ አገር መንግሥታትና ድርጅቶች ለመሆናቸው እንኳንስ በከተማ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ቀርቶ በየገዳማቱ የሚኖረውም ባሕታዊ ቢሆን አይዘነጋውም።
ታዲያ በዚህ ቁልጭ ብሎ በሚታይ የወዳጅና የጠላት ሰልፍ ውስጥ ለትግል ቀርቤአለሁ የሚለው የሽግግር ምክር ቤት ለነጮች መንግሥታት የሚያደርገው ልመናና፣ደጅጥናት በድርጅቱ መሪዎች ላይ ሕዝቡ የነበረውን ጥርጣሬ እንዲያጠናክረው እረድቶታል።
የድርጅቱ መስራች የሆነው ግለሰብ ከስድስት ወራት በፊት በአደባባይ ብቅ ብሎ አካኪ ዘራፍ ሲል አብዛኛው የወያኔ ተላላኪ በማለት ወከባ ገጥሞት ነበር።በአንዳንዶቹ ቀና ወገኖች የዋህነትና በአንዳንድ በልዩ ልዩ ሱስ የተለከፉ “ገንዘቡን እንብላው” በሚሉ ብልጣብልጦች በከፈቱለት ቀዳዳ ገባና ድርጅት ፈጥሮ አንድ ጊዜ የሽግግር መንግስት ሌላ ጊዜ የሽግግር ምክር ቤት እያለ የተምታታ መግለጫውን ማዥጎድጎድ ጀመረ።
አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እታገላለሁና እባካችሁ ከኔ የበለጠ ፈረስ ሊኖራችሁ ስለማይችል ተቀብላችሁኝ ፣ከወያኔ ጎን አሰልፋችሁ ጋልቡኝ ፣ከእጃችሁ ሊወጣ የተቃረበውን የጌትነት ቦታ ሕዝቡ እንዳይነጥቃችሁ መሳሪያ ሆኜ ላገለግላችሁ የተዘጋጀሁ መሆኔን አምናችሁ ተቀበሉኝ እመኑኝ እወቁኝ እያለ ለአሜሪካ፣ለጣሊያን፣ለአውስትራሊያና ለሌሎቹም አገር መንግስታት ልመናና ደጅ ጥናቱን ተያይዞታል።
ይህ ድርጅት የኢትዮጵያን ሕዝብ እውቅናና ድጋፍ ሳይጠይቅና ሳያገኝ ተንደርድሮ የደበደበው የነጮቹን መንግስታት በር ነው።
በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ላይ ውሃ ለማፍሰስና አሳልፎ ለመስጠት ከወያኔ ጋር ተደራድሮ ድሪቶ መንግስት ለማቋቋም የቋመጠ በመሆኑ መወገዝና መጋለጥ አለበት።
የዚሁ ድርጅት መሪ የሆነው ግለሰብ 21 ዓመት ሙሉ የወያኔ ተባባሪ ነጋዴ ሆኖ መኖሩ ሲከነክነን ከወያኔ ጎራ ፈልሶ ወደ ሕዝባዊው ጎራ የተቀላቀለ መስሎ የሰበከበት ምላሱ ሳይደርቅ በይሉኝታ ቢስነት በነጮች ቡራኬ የወያኔ ስርአት አዳኝ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነትና እኩልነት ፣ለዲሞክራሲ ስርአት መስፈን የሚታገለው ኢትዮጵያዊ ይህን እስስትና ባንዳ ድርጅት ከትግሉ ጎራ ሊያሶግደው ይገባል።በየዋህነት በሽግግር ምክር ቤቱ የተቀላቀሉት አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በስተጀርባቸው ሳያውቁት የነጮች አገልጋይ ለማድረግ የተተለመውን አሻጥር ተቃውመው
እራሳቸውን ማግለልና ከእውነተኛ የተቃውሞ ጎራ እንዲቀላቀሉ የበኩሌን ወገናዊ ምክር አቀርብላቸዋለሁ፤ለባርነት ስርዓት ገጸበረከት ልትሆኑ ነውና አይናችሁን ክፈቱ እላቸዋለሁ።
የኢትዮጵያ ጉዳይ ኢትዮጵያኑን ብቻ የሚመለከት ነው።የዲፕሎማሲ ወይም የፖለቲካ ስልት በሚል የማጭበርበሪያ ቃላት የኢትዮጵያን ሕዝብ ውሳኔና መብት ለነጮች አሳልፎ መስጠት ባርነትን አምኖ መቀበል ፣በራስ አለመተማመን ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ ያገሩና የመብቱ የወሳኝነት ባለቤትነት ለመሆን ከበቃ፣የተቃዋሚው ጎራ ከጠነከረ፣ ነጮቹ በራሳቸው አነሳሽነት ሳይጠየቁ ይመጣሉ። ምንጊዜም አይተነው ጊዜ ወደሚያዋጣው የሚል አካሄድ ስላላቸው ከጠንካራው ጎን ለመሰለፍ አይናቸውን አያሹም።በዚያም ጊዜ የሚኖረው ግንኙነት የጌታና የባሪያ ሳይሆን በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ይሆናል።
ያንን ክብርና እድል ለማሳጣት ነው አሁን የሽግግር ምክርቤቱና አንዳንድ የወያኔ አውታንቲ ድርጅቶች ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት።በሽግግር ምክር ቤቱ ውስጥና በሌሎቹ ተቃዋሚ ነን ባይ ድርጅቶች የአመራር ቦታ ላይ የተቀመጡት ግለሰቦች ከኢትዮጵያ የቅርብ ዋና ጠላት ከሆነው ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የጠበቀ ግንኑነት ያላቸውና አስመራ ከተማ ወጣ ገባ የሚሉ ከሃድያን ናቸው።
የሽግግር ምክር ቤቱም ሆነ ሌሎቹ በድርጅታዊ መብት ሽፋን የፈለጉትን እንዲያደርጉ መፍቀድና መልቀቅ ተገቢ አይደለም።የሚሰሩትና የሚንቀሳቀሱት በኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ዙሪያ እንጂ በግል የንግድ ድርጅት ዙሪያ አይደለም።ስለሆነም የኢትዮጵያን ሕዝብ ጉዳይ እጅ መንሻና የስልጣን መወጣጫ መሰላል ሊያደርጉት አይገባም። የሚፈጥሩት ግንኙነት የድርጅት መብት ነው ተብሎ የሚታይ ከሆነማ ወያኔም የሚፈጽመው ጥፋት፣አልካይዳ የተባለው አለም አቀፍ የሽብር ተቋም የሚፈጽመው ግድያ በድርጅታዊ መብት ስር ታይቶ መከበር አለበት ማለት ነው።
የሽግግር ምክርቤቱን መስራች ግለሰብ ዶ/ር ፍስሃ እሸቱን የመሳሰሉትን ሰርጎ ገቦች ቦታና እድል የሰጣቸው የተቃዋሚው ጎራ የጠነከረ አንድነትና ጠንካራ አመራር ባለመኖሩ ስለሆነ “ባለቤት የሌለው ቤት በቁንጫ ይወረራል” ነውና አወናባጆች የሚፈልጉትን ለማድረግ የሚችሉበትን ዕድልና ጊዜ ሊፈጥር ችሏል።አሁንም የተቃዋሚው ጎራ መዝረክረክና ቁርጠኛ አለመሆን ለሌላ ትርምስና የወያኔ እጆች ማረፊያ አመቺ ሊሆን ይችላል። የሚያዋጣው በትግሉ የተፈተኑ ፣የሚታመኑ ድርጅቶች አንድ ሆነው አመራር መስጠት ሲችሉ ነው።
መስዋእትነትንም ባለመፍራት በአገር ውስጥ ከሚገኙት ሃቀኛ የተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ትግሉን ለመምራት በአካል ከቦታው ማለትም በአገር ቤት ውስጥ መገኘት ይኖርባቸዋል።ትግል በርቀት ወይም በሪሞት የሚቀነባበር ጉዳይ አይደለም። ይህ ጊዜ የማይሰጠው ከመሪ የሚጠበቅ አስቸኳይ እርምጃ ነው።ይህን ለማድረግ ካልቻሉና ድፍረቱ ከሌላቸው ተቃዋሚ ድርጅቶች ነን ብለው የሚለፍፉበትን አፋቸውን ዘግተው ከመድረኩ ገለል ሊሉ ይገባል።ሕዝቡ እራሱ በራሱ ለችግሩ መፍትሄ ያገኝለታል።”ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል” የሚለውን አባባል ሊያስታውሱት ይገባል።
ዳግማዊ ይሁዳን እናጋልጥ፣የዘመኑ ባንዳዎችን እናሶግድ
በዛብህ ጥቃቱ

No comments:

Post a Comment