No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Friday, 10 August 2012

መካከለኛ ልቦለድ፤ “የአውቶቢሶቹ ወግ”


ከአቤ ቶኴቻው
ዛሬ አርብ ነው። የሙስሊም ወዳጆቻችን ሰላማዊ ተቃውሞ ዛሬም ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ተቃውሞ “ፍፁም አመፅ አልባ ተቃውሞ” የሚባለውን የነ ማህተመ ጋንዲን ስልት የያዘ ነው። ባለፈው ጊዜም በየመን በተደረገው ተቃውሞ ላይ የሰላማዊ ተቃውሞው አስተባባሪ እንስት በፖሊስ እና በተቋማት ላይ ድንጋይ የሚወረውሩ የተቃውሞው አባላትን የምትቀጣበት የራሷ የሆነ “ፖሊስ” አዘጋጅታ እንደነበር ሲዘገብ ሰምተናል። ይህ ፍፁም ሰላማዊ ተቃውሞ ቢያንስ ቢያንስ ታሪክ በበጎ ሲያነሳው የሚኖር ነውና እጅግ የሚበረታታ ነው። ይቺን ያህል ከተንደረደርኩ፤ ከሶስት ሳምንት በመርካቶ አካባቢ በፊት የሆነውን የሚያስታውስ አጭርም ረጅምም ያልሆነ መካከለኛ ልቦለድ እንደሚከተለው ይቀርባል።
ዕተቱ አርብ ነው። ጀምበር የክረምቱን ዳመና እንደምንም አሸንፋ ለመውጣት እየታገለች ነው። ደመናው ደግሞ “የለም ተራው የእኔ ነው አትወጪም” ብሎ እየተከራከረ ይገኛል። ፀሐይቷ እንደምንም በፈገግታዋ አታላ ለመታየት ጥረት ማድረግ ጀመረች። ይሄን ግዜ ደመናም በፈገግታዋ ልቡ ተሸነፈ እና ዝም አላት። ሊነጋ ነው። አንበሳ ጋራዥ በርካታ የአውቶቢስ ሾፌሮች ማልደው ደርሰው አውቶብሶቻቸውን እያስጮሁ ነው። በርካታ አውቶቢሶች በጠዋቱ የተለመደ ስራቸው ላይ ሲሰማሩ ጉዳት የደረሰባቸው እና
ከጥቅም ውጭ የሆኑ በርካታ አውቶብሶች ግን እዛው ግቢ ቀሩ። ያለ ምንም ጉዳት እና እንከን ወደ አምስት የሚጠጉ አውቶብሶችም ለምን ወደ ስራ እንደማይሰማሩ ግራ ግብቷቸው ቁልጭ ቁልጭ እያሉ ቆመዋል። ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ በቅርቡ ስራ የጀመሩ ቻይና ሰራሽ መከላከያ አዳሽ የሆኑ አዳዲስ አውቶብሶች ናቸው። “ቢሸፍቱ ባስ” ይባላሉ። አነዚህ አዲስ አውቶብሶች ስራውን በጣም እየወደዱት መጥተዋል። በክረምቱ ሰዉ እቅፍቅፍ ብሎ ሲጓጓዝ አንዳንድ ግዜ የሚታየውን ትርኢት እየታዘቡ መደመሙ ብርቅ ሆኖባቸዋል። እናም ሁሌም ጎህ ቀዶ ሹፌሩ እያስጋለበ ወደ ስራ ሲወስዳቸው በደስታ ነበር የሚነዱት። አሮጌዎቹ አውቶብሶች ደግሞ ነገሩ በሙሉ ትክት ስልችት ብሏቸዋል እና እረፍት ማድረጉን ወደውታል። ከአዲሶቹ አውቶብስ አንዱ ጠየቀ፤ “እኔ የምለው ዛሬ ሰዎቹ ስራ አይወስዱንም እንዴ…!? ሁሉም ወጥቶ እኮ እኛ ብቻ እንደጉዳተኛ ተገትረን ቀረን!” አለ። እርጅና የተጫጫነው አውቶብስ መለሰለት፤ “የኔ ጌታ እናንተ ገና ገና ጀማሪ ናችሁ ምንም አልደከማችሁም እኛ እንረፍበት! ደህና የረሱንን ሰዎች አታስታውስብን” አለው። “አልሰማችሁም እንዴ!?” አለ ሌላው አሮጌ አውቶብስ። “ምን!?” “ዛሬ የሶላት ሰዓት ሲደርስ አንዋር መስጊድ ልንሄድ እኮ ነው!” አስራ ሰድስት ቁጥር ሆና ለበርካታ ጊዜ ከመርካቶ ሽሮሜዳ የሰራች አሮጊት አውቶቢስ ከልምዷ በመነሳት፤ “ምን እናደርጋለን…!? ዛሬ እኮ አርብ ነው። በሶላት ሰዓት መንገዱ ዝግ አይደለም እንዴ!?” አለች “ታድያ ዋና የተፈለግነው ለምን ሆነና…” አለ መረጃውን ያመጣው አንጋፋ አውቶቢስ። አዲሶቹ አውቶቢሶች ግራ ገብቷቸዋል። አንደኛውም “አቦ ምንድነው የምታወሩት ግልፅ አድርጉልና…!” ሲል ተነጫነጨ። “ይሄውላችሁ ትላንት ለጋሽ ሾፌርዬ ከበላይ አካላት አንድ መመሪያ ሲሰጠው ሰምቻለሁ።” “ምን…?” ሁሉም አውቶብሶች በአንድ ድምፅ ጠየቁት። “ተረጋጉ… እንጂ ምንድነው ለወሬ እንዲህ መጣደፍ…!” አለና ሳቅ አለ… ከዛም “ወደው አይስቁ!” ብሎ ተረተ! “እባክህ ንገረን ሞተራችንን አታጩኸው…!” አለ ሌላኛው። (ሆዳችንን አታጩኸው ሲባል ሰምቶ) “አንዋር መስጊድ ተቃውሞ አለ ስለዚህ እኛ ወደዛ እንድንሄድ ሲታዘዝ ሰምቻለሁ” አላቸው ተከዝ ብሎ። አዲሱ አውቶብስ እየተጣደፈ “እንዴ… እኛ አድማ መበተኛ ነን እንዴ!?” አለ ጭንቅ ብሎት። “አድማ መበተኛው ከእኛ በኋላ ነው የሚመጣው። እኛ የተፈለግነው ተቃዋሚዎቹ ድንጋይ ወርውረውብን ስንሰበር በቪዲዮ ለመቀረፅ ነው!” ብሎ እንቅጩን ነገራቸው። አዳዲሶች አውቶብሶች ክው አሉ። አንደኛውም፤ “ገና ከተገጣጠምን ስድስት ወር እንኳ ሳይሞላን በለጋ እድሜያችን ለምን እንዲህ ወዳለው አደገኛ ቦታ ይወስዱናል!?” ብሎ የየዋህ ጥያቄ ጠየቀ። ይሄኔ አስራ ሰድስት ቁጥር “እድልህ ነው ወዳጄ!” ስትል በማፅናናት እና በማሽሟጠጥ መካከል ያለ ንግግር ተናገረች። እንዲህ እየተወያዩ ሰዓቱ ደረሰ። ሾፌሮቻቸው ገቡ። እናም አሰልፈው ወሰዷቸው። ነገሩን ያላወቁ መስለው ሲሰለፉ ከፊት የሚሆነውን አውቶብስ እያዩ እየተሳሳቁ እና እየተሳቀቁ ነበር። በሆዳቸውም የቀጠቀጣቸው እና የገጣጠማቸውን ፈጣሪያቸውን እየጠሩ “ጉድህን አላየህ የሰራህኝ ልሰበር መሆኑን ብታውቅ ያንን ሁሉ ልፋት ባለፋህ ኖሮ… ወዮ ለእጆችህ እኔን በማሳመር ለደከሙ፣ ወዮ ለጥበብህ እኔን አውቶብስ ይሆናል ብለው ለተጠበበብኝ…ወዮ ለእርዳታው ገንዘብ ለህዝብ ማመላለሻ ይሆናል ተብሎ ለተሰጠው” እያሉ እያንጎራጎሩ ነበር። ከጊዮርጊስ አደባባይ ትንሽ ዝቅ ብለው ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ ሲደርሱ በርካታ ህዝበ ሙስሊም አስፋልቱን ሙልት አድርጎ ተመለከቱ። “የታደለ ሮጦ ሪከርድ ይሰብራል እኛ ራሳችን ለማሰበር እንሮጣለን!” ስትል አስራ ስድስት ቁጥር አጉረመረመች። ከኋላዋ ያለው አዲስ “ቢሸፍቱ ባስ” “አይዞሽ እንግዲ ቻል አድርጊው…!” አላት ቅድም ያሽሟጠጠችውን ብድሩን ለመወጣት። “እኔስ ምንም ብሆን የጥንት የጠዋት ነኝ! ይብላኝ ላንተ ሲነኩህ ፍርክስ ለምትለው የቻይና እቃ” ስትል በብሽቀት ተናገረች። አዲሱ አውቶብስም አክብሮ ዝም… አላት። ወደ ህዝቡ ውስጥ ገቡ። ከአሁን አሁን እንሰበራለን ብለው እየተሸማቀቁ በሹፌሮቻቸው አስገዳጅነት ለመሰበር እየሄዱ መሆኑን ሲያስቡ፤ “ሰው በሆንን እና ይህንን ተቃውሞ ተቀላቀልን ለነፃነታችን በጮኽን” ሲሉ ተመኙ። “መርፌ መጣያ እንኳ በሌበት” የመርካቶ መንገድ ለፀሎት እና ተቃውሞ በተሰበሰበው ህዝብ መሀል ተሰልፈው ቢገቡም እንኳንስ ድንጋይ ክፉ ቃል እንኳን የሚሰነዝር ሰው አላጋጠማቸውም። አውቶብሶቹ ርስ በርግ ግራ በተጋባ ስሜት ተያዩ በየራዲዮኖቻቸው “አክራሪ አሸባሪ…” ሲባሉ የነበሩ ሙስሊሞች መሀከል ነው የቆሙት። ነገር ግን አንድም ኮሽታ አይሰማም። “አሸባሪነት ማለት ፍፁም ሰላም። ፍፁም ፀጥታ ማለት ነው ለካስ…!” ሲል አዲሱ አውቶብስ ለአስራ ስድስት ቁጥር በሽኩሹክታ ነገራት። እርሷም “እውነት ብለሃል!” አለችና “ተመልከት” ብላ በርቀት ሲሰበሩ ሊቀርፃቸው የተጠመደ ካሜራ አሳየችው። ሁሉም እየተጠቋቈሙ ወደ ካሜራው ተመለከቱ። ነገር ግን አንድም ሊሰብራቸው ያሰበም… የሞከረም ሰው አለመኖሩን ሲመለከቱ ያሰማሯቸው ሰዎች ቅስም ሲሰበር ታያቸው። መደምደሚያ ልቦለዱ በዚህ አበቃ! ልቦለድ የሆነ ኑሮ ከሚያኖር መንግስት ይሰውረን!

No comments:

Post a Comment