እንደ መብረቅ ብልጭ ብሎ የሚጠፋው፣ እንደ ጸበል ጻዲቅም በአምስት አመት አንድ ጊዜ የሚታየውና የሚታስበው
የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ሞቅታ የሚፈጥረው የሞቅታ ፖለቲካ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ወቅታዊና አወዛጋቢ ሁኔታዎች በተያያዘ ያለአመሉ ባልተጠበቀ ጊዜና ሁኔታ ሲጋጋል እየተስተዋለ ነው። በእርግጥ ክስተቱ (የሰው ልጅ በሥጋ መታመም ሆነ በሞት ከዚህ ዓለም
መለየት) ከልማዳዊ የሰው ልጆች የኑሮ ዘዬ የዘለለ የተለየ ታሪካዊም ሆነ ሥነ ተፈጥሮአዊ አንድምታ የለውም ሊኖረውም አይችልም።
አንድ ሰው ሰው ሆኖ ተወልዶ ለመኖር እስከቻለና እስከበቃ ድረስ ደስታም ሆነ ሐዘን ጤናም ሆነ ሕመም እንዲሁም ብርታትና ድካም
በየጊዜያቸው ማየቱና ማስተናገዱ የማይቀር ነው። በአጭሩ የሰው ልጅ ይወለዳል ይሞታልም።
የሰው ልጅ ጥላ ዘርግቶ የፀሐይ ንዳድ የሰማይም ዝናብ መከላከል ቢቻለውም ከመቃብር ሃይል ሊያስመልጠው ሊያተርፈውና
ሊታደገው የሚችል ጡንቻም ሆነ የአእምሮ ልቀት ግን የለውም። ሥልጣን፣ ውበት፣ እውቀትም ሆነ ሀብት እስከ መቃብር ከመቃብርም
በታች ናቸው። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም መቃብር/ሞትና ፍቅር ማንንም አይገፉም የሚባለው። ጥጉ የሞት ጠላትም ሆነ ወዳጅ
የለውም። ሞት ከጸሐይ በታች ለከተመ ፍጥረት ሁሉ እንግዳ ነው። ለነጩም ለጥቁርም ለድሃው ለሀብታሙም ለባለ ሥልጣኑም ሆነ
ለተራ ዜጋ ለመሃይሙም ሆነ ፊደል ለቆጠረ ሞት ዕጣ ፈንታው ነው።
የማይሞት ያልተፈጠረ በሌላ አገላለጽ ወደ ህልውና ያልመጣ ብቻ ነው። ከዚህ ውብ የሆነ የሕይወት ዑደት
የሚያመልጥ/ሊመልጥ የሚቻለውም አንድም የለም። የተወለደ ሁሉ በአንድም በሌላም ኮንትራቱን/ቆይታውን ጨርሶ በእልፍ ዓይነት
መንገድ መሄዱ የማይቀር ነው። ስለሆነም የጽሑፉ ይዘትም ሆነ የጸሐፊው አስተያየት የሰው ልጅ ተሟግቶ ሊረታው ከማይቻለው ከሥጋ
በሽታና ከሞት ጋር መሳፈጥ ሳይሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከብዙሐኑ ዕይታና እውቀት መሰወር ተከትሎ በተለይ በውጪው ዓለም የምንገኝ
ዜጎች መካከል የፈጠረውን ሞቅታ ጩኸቱ እርስ በርሳችን መደማመን እስኪያቅተንና እስኪሳነን ድረስ አቅጣጫውንም ስቶ የከፋ አዘቅት
ውስጥ እንዳይከተን በመስጋት ወቅቱ እያራገባቸው ከሚገኙ ልብ ያላልናቸው ለጊዜው ሦስት ዓበይት ነጥቦች ያተኮረ ለመመካከር ተጻፈ።
አንድም ሞቅታ አዳልጦ ይጥላል ነውና።
ውድ አንባቢ! ቢላ የሰው ልጅ የዕለት ኑሮውን ማለትም ምግቡን በመስራት ረገድም ሆነ ራሱን ከበላተኛ አውሬ ለመከላከል
ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ሁሉ የገዛ ወንድሙን ነፍስ ለመጣልም ሆነ የወገኑን ደም ለማፍሰስም ሊያገለግል/ሊሚጠቀምበትም
እንደሚችል ይስቱታል የሚል እምነት የለኝም። ታድያ በሰው ልጅ ሕይወት ዙሪያ ያሉት ማንኛውን ተፈጥሮም ሆነ የአእምሮ ውጤት
ሁሉ እንደ አጠቃቀማችን ሊያጠፉንም ሊያለሙንም እንደሚችሉ ከተረዳን ዘንዳ ጥፋት ምርጫ እስካላደረግን ድረስ ደጉንና መልካሙን
ብቻ ሳይሆን በራሱ አደጋ የሚመስለው ነገር ሳይቀር ወደ ልማት፣ ለመልካም ነገርም ሁሉ መገልገያና መጠቀሚያ ማድረግና ማዋል
የመቀየርም ድርሻ የእኛ ሊሆን እንደሚችል በማመን ሰፊ ሐተታ ውስጥ ሳልገባ በዋናነት ወደ ተነሳሁበት ላዝግም።
ላለፉት በርካታ ዓመታት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት በስራ ገበታቸው ለበርካታ ቀናት አለመገኘትና
መጉደል ለሥርዓቱ ማብቂያ አስተዋጽኦ አለው ተብሎ ከታመነ አይቀር ከፍ ስል ቀለል ባለ ምሳሌአዊ አነጋገር ለመግለጽ እንደተሞከረ
መንገዱ ሁለት አቅጣጫዎች መያዙ የማይቀር ነው። ይኸውም ተደማምጠንና ተጠባብቀን ሁሉን ያማካለ የትግል መስመር ዘርግተን
የተፋለምነው እንደሆነ በአጭሩ ምድሪቱ ወደሚያስፈልጋት ሕዝቡም ማየት ወደሚናፍቀው ምዕራፍ እንደ አንድ ማሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ
ወደ ቀጥዩ ምዕራፍ ሊያሸጋግረን ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ አበው "የቸኮለ ጅብ ቀንድ ይነክሳል" እንዲሉ ገና ለገና ምኑ ሳይያዝ ጭልጥ
ያለ እንቅልፍ ወስዶን በሕልምና በቅዠት ዓለም ውስጥ ገብተን ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎልን በዝግታ ስንራመድ፣ ከዓለም መንግሥታት ተርታ
ተሰልፈን ስናውካካና ስንጨባበጥ … ብቻ በዚህ ሁሉ ማኸል (በህልሙ ማኸል ለማለት ነው) የማንቅያ ደወል በሚደውሉ ወገኖች ላይ እንደ
አንስት አንበሳ ጨበርበር የምንል ከሆነ (በድረ ገጽ ባለ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በመፍጠር ሊነበቡ የሚገባቸው ጽሑፎች ሳይውሉ ሳያድሩ ከስፍራቸው
ማስነሳትና መንቀልን ይጨምራል) ደግሞ ምድሪቱ ወደከፋ የትርምስና የእልቂጥ ቀጠና መግባትዋ የማይቀር ነው። ይህ ሊሆን እንደሚችል
ከወዲሁ ከግምት ያለፈ መሬት የረገጠ እውነታ ለመተንበይ ደግሞ በልዩ ቋንቋ መናገርም ሆነ መጻፍ አይሻውም። ምን ነው? ቢሉ ሰላም
ስለተመኝዋት የምትገኝ የስለት ዕቃ ሳትሆን ለመልካምና ለበጎ ነገር ሁሉ ራስህን በማስገዛት፣ የምትመጣ የመስዋዕት ፍሬ የከበረች ዕንቁም
ናትና።
እንግዲህ አንድ ሰው ስለ ፍትሕ አፉ መልቶ ሲናገር/መናገሩ ያልቀረ ፍትሐዊ የሆነ አስተሳሰብና አመለካከት ከራሱ ከተናጋሪው
ይጠበቃልና ስለ ፍትሕ ገንዘቡን እውቀቱንና ነፍሱን ለመስጠት እየተዘጋጀ ያለውን ትውልድ ትግሉን መስመር እንዲይዝና ቱንቡውንም
ጠብቆ መንገዱን እንዲጠበጥብ ከዚህ ባሻገርም ዋጋ የሚከፍልበትን ትግል ዒላማውን በሚገባ ይመታ ዘንድ ቀጠለው በሚዘረዘሩ ወቅታዊ
ነጥቦች ላይ መስማማት መተማመንና የጋራ የሆነ ዕልባት መድረስ ይጠበቅበታል። ነጥቦቹ ምንም እንኳን ጥቂትና ቀላሎችም ቢመስሉ
ተገቢ ትኩረት ሰጥተን ተግባራዊ ያደረግናቸው እንደሆነ ግን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቁ አንድ ሆነን በአንድ ልብና በአንድ
ሐሳብ ለአንድ ዓላማ እንዳንቆም አሽክላዎች የሆኑብን ችግሮችንና ዕንቅፋቶችን መቅረፍና ማስወገዳቸው ብቻ ሳይሆን የጥቂቶች ጥቅም
ማዕከል ያደረገ አንባገነናዊ አገዛዝ ከሥሩ ለመጣልም የጎላ ሚና እንደሚጫወቱ ነው። ዝርዝር ነጥቦቹ -
አንደኛ. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምሮ ሌሎች በዙሪያቸው የሚገኙ አንዳንድ አውራ ሽማሙንቶች ምንም በልደት በሀገሬትዋ
ሰሜናዊ ክፍል ከሚገኘው ሕዝብ "የተገኙ" ቢሆኑም ግለሰቦቹ በምንም ዓይነት መልኩ የተጠቀሰውን ክልል/ሕዝብ/ብሔር እንደማይወክሉ
ልናሰምርበት ይገባል። በኃጢአታቸውና በነውራቸውም የሚጠየቅ ሌላ ወገን እስከሌለ ድረስም ግለሰቦቹ አራትና አምስት ሚልዮን ከሚሆን
ሕዝብ ነጥለን ማየት ይጠበቅብናል። ስማቸውና እኩይ ምግባራቸው በተወሳ ቁጥርም ካስፈለገ የወላጅ አባቶቻቸው ስም ይጨመርበት
እንጂ በዕለተ ፍርድ፣ የዘርዋትንም በሚያጭዱበት ወቅት መራራ ፍሬአቸውን የሚጋራ ሕዝብ አይኖርም። በዚህ አጋጣሚ የትግራይ ሕዝብ
በአጉሊ መነጽር የሚታይበት አሰራርና አካሄድ የሚሰሩትንም ዜናዎች አስቸኳይ እርምት ይደረግባቸው ዘንድ እጠይቃለሁ።
በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምሮ ሌሎች ጥቂት የማይባሉ በሥልጣን ላይ የሚገኙ ግለሰቦች አብዛኞቹ በከፊልም ሆነ በመላ
የኤርትራ ደም ያላቸው/የኤርትራ ተወላጆች ናቸው ሲባል ነበር/ነው ሲነገር የምንሰማው ተጽፎም የምናነበው። ታድያ ከኤርትራ ጋር አብሮ ለመስራት
ያላፈረ ቡድን እነዚህ ግለሰቦች "በኤርትራዊነታቸው" የሚያፍርባቸው ከዚህ አልፎ "በኤርትራዊነታቸው" የሚከሰሱበት ምክንያትስ ምንድ ነው?
ጨወታው ሰዎቹ የኤርትራ ተወላጆች አይደሉም ማለት ይሆን? ወይስ የኤርትራ መንግሥት ለፍጥረቱ የሚጠላው ሕዝብ በኤርትራ ስም መጠላቱ
ይሆን? መቼም ኤርትራ ማለት ትግራይ ነው ትግራይ ማለት ደግሞ ኤርትራ ማለት ነው የሚል ባለ አእምሮ እንደማይኖር በማመን ነው።
ሁለተኛ. ለሃያ አንድ ዓመታት በትረ ሥልጣኑን ጨብጦ እየገዛ የሚገኘውን ለምዕራባውያን ዕጥፍ ዝርግት ብሎ ሲያበቃ ለዜጎቹ
ክብር የሌለው የባንዳዎች ስብስብ መንግሥት ዕድሜውን ለማሳጠር በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም በሚደረገው የመረረ ሰላማዊ
ትግልና ምክክር የትግራይ ሕዝብ ልዩ አጀንዳ ተይዞለት መወያያ የሚሆንበት ምክንያት ትግሉን በዋናነት ከሚያጨናግፉ ዓበይት ነጥቦች
መካከል አንዱ ነውና አሁንም ይህን የተሳሳተ እምነት በአስቸኳይ እርምት እንዲደረግበት ጥርዬን ለማቅረብ እወዳለሁ። አንዱን የጭዋይቱ
ሌላውን የባራይቱ እንደ መፈረጅ ዓይነት በሚደረገው ትግል ትርፉ ኪሳራና ኪሳራ እንጂ አመርቂ ውጤት ሊያስመዘግብ አይችልም። በተለይ
ከተለያዩ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች ጋር የሚደረጉ ቃለ ምልልሶች በአንድ ሕዝብ ላይ አነጣጥረው ስለሚሰነዘሩ ጥያቄዎች ጥያቄው
ቀደም ብሎ በሚገባ ታስቦቦት በስሌት የሚቀርበው ያክል በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊ ልብ ያለው ሰላም ወዳድ ዜጋ ልብ እንደሚሰብሩ
እንደሚያደሙና ሰሚ ጆሮም እንዲሁ እንደሚኮረኩሩ ውሎ አድሮም የተገለጠ ችግር ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አቤት ለማለት እወዳለሁ።
ሦስተኛ. በኢትዮጵያ ምድር በጥቅም የተሳሰረ የጥቂት ግለሰቦች አንባገነናዊ አሰራር/ሥርዓት እንጅ የአንድ ብሔር/ክልል/ጎሳ
የበላይነት ብሎ ነገር እንደሌለም አበክረን ልንተማመን ይገባል። "የትግራይ ገዢ መደብ" ብሎ ቋንቋ የለም! አለ ብሎ የሚያምን ግለሰብም
ሆነ ድርጅት ቢኖር ግን የዚህ አካል ጥያቄ የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ ሳይሆን ጠበንጃ የሚታጠቀው ለሌላ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ማንንም
የማይበጅ ለብ ያለ አስተሳሰብና ጎደሎ ፖለቲካዊ አካሄድ ደግሞ ከዚህ ቀደም ግልጽ በሆነ ቋንቋ በተከታታይ ለመግለጽ እንደተሞከረ
ያጠፋፋናል እንጅ ዓለም ወደ ደረሰችበት የስልጣኔ መንገድ አይቀላቅለንም።
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E- mail yetd gnayalehe@gmail.com
United States of America
August 09, 2012
No comments:
Post a Comment