No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Monday, 6 August 2012

ሙገሳችን ምክንያታዊ ይሁን

ከይኸነው አንተሁነኝ
ነሐሴ 5 2012
መቼም እንዳለመታደል ሆኖ ሀገራችንም ሆነች እኛ ህዝቦቿ የምንጠራው በመልካም ኮሆነ ሰነባብቷል። እንዲያውም ብዙ ሰዎች እንደሚናገሩት "የመንታ እናት ተንጋላ ትሙት" እንዲሉ እዚህም እዚያም እያሉ የሀገራችንን በጎ ስም ለማስጠራትና እንዳትዘነጋ ለማድረግ የሚጥሩ ጥቂት ሯጮቻችን ባይኖሩማ ኖሮ ሁሉ ነገር ጨለማ በሆነ ነበር (እነሱም ላይ የሚደርሰው ዘርን መሰረት ያደረገ መድሎ ሳይዘነጋ ማለቴ ነው)። ይደንቃል አንደኛው ሲሰፋ ሌላኛው ስቀድ የሚያድርበት ሀገር። የህዝብን ምኞት "መንግስት" ሲያኮላሽ የሚያነጋበት ምድር። እስኪ በማን ሀገር ነው የሀገር መሪው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለድፍን አርባምስት ቀናት በአስተማማኝ፣ በግልጽና በማስረጃ በተደገፈ ምልኩ ለህዝቡ የማይነገረው። ታዲያ እንዲህ ያለው መጥፎ ታሪክ በወያኔዎች ከምትገዛዋ ኢትዮጵያችን በቀር የት ሊገኝ ይችላል? እንዲህ ያለው ድርጊት እንደ ዘረኛው መለስ ዜናዊ ያሉ የአምባገነን አምባገነኖች የሚከውኑት የነሱ ብቸኛ መለያ ባህሪ ይመስለኛል።
እንዲያው ነገር ጠልፎኝ ሰለወያኔ ባህሪ ትንሽ አልኩ እንጂ አነሳሴ እንኳ ስለ በታኙ መለስ ዜናዊና ወያኔ ጭፍን ደጋፊዎች "ጭፍን ጋላቢዎች ማለት ይሻል ይሆናል" ጥቂት ለማለት ነበር። ማነው ስሙ ይኸ አወ "ሰለሞን ቅንድቡ" በሚያስተላልፈው ነፃነት ራዲዮ ፕሮግራም ወይም በሚሚ ስብሃቱ ዛሚ የውሸት ራዲዮ ይመስለኛል፤ ታዋቂው ጋዜጠኛ አበበ ገላው መለስ ዜናዊን ቀልቡን ከገፈፈው በሗላ በየዌብሳይቱ የሚወጣው ያላማራቸው ጭፍን "ጋዜጠኞች" እና ደጋፊዎች በጌታቸው እንትን መፎከር የጀመሩት። "የኛ ጌታ መለስ ዜናዊ ታንክ ተደግፎ መጽሃፍ ሲያነብ የነበር ጀግና እንዴት ለአበበ ገላው ጩኸት ይደነብራል " ይሉናል። ነገሩ ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን ሆነና ዛሬ አይበሉን እንጅ።

እነዚህ ጭፍን ጋላቢዎች እንደሚሉት በታኙን መለስ ዜናዊን ለሀገራችን ያልነበረና ያልታየ እድገት ያመጣ አድርገው ይስሉታል። ከጎጠኛው መለስ በፊት የነበሩ የሀገራችን መሪዎች ምን አይነት ኢትዮጵያን እንደተረከቡና በጊዜው ከድህነት በተጨማሪ መሃይምነትንና የእርስ በርስ እና ከጎረቤት ሀገር ጋር የሚደረጉ የማያባሩ ጦርነቶችን አብረው እንደተረከቡና የሀገርን ሉአላዊነት ሳያስደፍሩ እንደኖሩ ላፍታ እንኳ ማስታወስ አይፈልጉም። እጅግ በጣም ቢያንስ እንኳ፤ እንደ ጎጠኛው መለስ እና ወያኔ የሀገርን ድንበር ቆርሰው እየመረቁ በመስጠትና በመሸጥ የሚታሙ አይደሉም። ከዚህ በተጨማሪ ለበታኙ የወያኔ የይስሙላ መንግስት በገፍ እየፈሰሰ ያለው በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር እርዳታ በነዚህ የቀድሞ የሀገራችን መሪዎች ወቅት የሚታሰብ አልነበረም። ያም ሆኖ በወቅቱ ህዝባችን ካሁኑ እጅግ በተሻለ ሁኔታ ይኖር ነበር። ሀገራችንም ሆነች እኛ በዓለም ፊት ካሁኑ እጅግ በጣም በተሻለ መልኩ ክብር ነበረን።
እነዚህ ጭፍን ደጋፊዎች እያዩ ያሉት እየተገነባ ያለውን መንገድ እና ህንጻዎችን ከሆነ ገሚሱም ወደፊት በልጆቻችን ወይም በልጅ ልጆቻችን የምንከፍለው በምስኪኑ ህዝባችን ስም በብድር በተገኘ ገንዘብ እየተገነባ ያለ እንጅ ጎጠኛው መለስ ወይም ወያኔ ህዝብን አስተባብረው በመስራት ያመጡት እድገት አለመሆኑን ማስተዋል ይገባል።
ሀገር አስገንጣዩ መለስና ወያኔ ሀገራችንን መግዛት ከጀመሩ ጀምሮ ካገኙትና እያገኙት ካለው የእርዳታ ሃብት አንጻርም በሀገራችን እየተገነባ ያለው ኢምንት እንደሆነ እነዚህ ጭፍን ደጋፊዎች ማስተዋል ተስኗቸዋል ወይም አይፈልጉም። ካልሆነም ዩ ኤን ዲ ፒ ከዚህ በፊት ወደ ሀገራችን ከገባው የእርዳት ገንዘብ የሚበዛው ተመልሶ በተለያዩ የወያኔ ባለስልጣናት ስም በውጭ ባንኮች መቀመጡን አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት በግርድፉ ዳሰስ ማድረግ ብቻ እውነቱን ለማየት ይበቃቸዋል። በእርግጥ ፍላጎቱ አይኖርም እንጅ።
ለአንዲት ሀገር የእድገት መሰረት ሀገሪቷ ያሏት የተፈጥሮ ሀብቶች ናቸው። ከነዚህም ሃብቶቿ ዋነኛው ሰው ነው። ይህ ሰው ባለው አቅም በመረባረብና ሌሎች ሀብቶቿን ለአገልግሎት ዝግጁ ወደ ሆነ ሀይል በመቀየር እና ለገበያ በማቅረብ ገቢ የሚያስገኝላት እና ችግሯን የሚፈታላት የአንዲት ሀገር ትልቅ ሃብት ነው። ስለዚህም መገንባት ካለበት በቅድሚያ ሊገነባ የሚገባው ይህ ያንዲት ሀገር እንቁ ሃብት እንጅ መንገድና ህንጻ አልነበረም። በታኙ መለስ ዜናዊና ወያኔ ግን እያደረጉ ያሉት ይህን ገንቢ የሀገር ሀብት በስበብ አስባቡ መግደል፣ ማሰርና ማሰደድ ነው።
ሌላው የከፋፋዩ መለስ ዜናዊ ጭፍን ደጋፊዎች የሚያነሱት፤ ሰውየው ኢትዮጵያን ያፍሪካ መሪ አድርጓል፤ በተለይ የምስራቅ አፍሪካ ደግሞ የሰላም አባት ናቸው ይላሉ። እንዴው ለመሆኑ በምንድን ነው መሪ የሆነው በድህነት፣ በርሃብ፣ በስደት፣ የእርዳታ እጆቻችንን በመዘርጋት፣ ሰብአዊ መብትንና ዲሞክራሲን በማፈን፣ የጋዜጠኞችን መብት በመርገጥ፣ አስር ቤቶችን በመገንባትና መብቱን የጠየቀውን ሁሉ በማጎር ወይስ ተገቢውን ጥራት የጠበቀ ትምህርት ለልጆቻችን በማቅረብ? በ2012 በወጣው የዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥራት መመዘኛ የኢትዮጵያው ታላቁ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች 31ኛ ሲወጣ ምንግስት አልባ የነበረችው ሶማሊያ ትልቁ ዩኒቨርሲቲ 35ኛ መውጣቱን እነዚህ ጭፍን ደጋፊዎች ያውቁ ይሆን? ይህ እድገት ከሆነ ማለቴ ነው። የአፍሪካን በተለይም የምስራቅ አፍሪካን አካባቢ ሰላም በመጠበቅ በኩልስ ቢሆን እነሱ የፈለጉትን እንዲጮሁላቸውና እንዲያደርጉላቸው ምእራባዊያን የሚያስወሩትን በመከተል ነው ወይስ በምድር ላይ ያለውን ሀቅ በመንተራስ? እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረትን አጠፋለሁ ብሎ ሶማሊያ የገባው የወያኔ ጦር የህዝብ ለህዝብ ጠላትነትን ከማሳደጉም በላይ አልሻባብን ፈጥሮ አካባቢውን ለማያባራ ትርምስ አላጋለጠም። በሁለቱ ሱዳኖች መካከልስ የሚጫወተው የገንጣዩ መለስ ዜናዊና ወያኔ ሚና በእርግጥ የሰላም አባት ያስብላል? ጭፍን ደጋፊዎች ቢያንስ አሁን እንኳ አይናችሁን መክፈት ያለባችሁ ይመስለኛል። ወደ አንድ አቅጣጫ ያጋደለና ሚዛናዊነት የጎደለው ግምገማ ለትችት ያጋልጣልና የአምባገነኑ የመለስ ዜናዊና የወያኔ ጭፍን ደጋፊዎች በሀገራችን ያለውን ከልክ ያለፈ ጎጠኝነት፣ አኩልነት እርሙ የሆነ ስርአት፣ ርሀቡን፣ ስደቱን፣ ስራ አጥነቱን፣ ኢፍትሃዊ የሀብት ክፍፍሉንና ሀገራችንም ሆነች ህዝባችን የደረስንበትን የውርደት ደረጃ ለማስተዋል ሞክሩ እንዳቅማችሁም ሚዛናዊ ዘገባ ለማቅረብ ጥረት አድርጉ እላለሁ። አበቃሁ።

No comments:

Post a Comment