No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Sunday, 7 April 2013

‹‹አንዳንድ መገናኛ ብዙኀን ለቀቅ አድርጉን የመንግሥት ባለሥልጣናትንም አትጨቅጭቋቸው›› ሼክ መሐመድ አል አሙዲ


    ከዚች አገር አንድ ሚሊ ሳንቲም አልወሰድኩም ብለዋል

•    ሪፖርተር እንዳይዘግብ ተከልክሏል
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ አል አሙዲ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኅን ኩባንያዎችና ድርጅቶች የሚሠሩትን በመከታተል አሉታዊ ነገሮችን እንደሚዘግቡ በመጠቆም፣ የመንግሥትን ባለሥልጣናትን እንዳይጨቀጭቋቸው አስታወቁ፡፡
ሼኩ ይህንን ዓይነቱን አስተያየት ያቀረቡት ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የገዟቸውን የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ የጐጀብ እርሻ ልማትና የቡና ማደራጃና ማከማቻ ድርጅት የርክክብ ፊርማ በሆቴላቸው ሸራተን አዲስ መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም. በፈጸሙበት ወቀት ነው፡፡
‹‹አንዳንድ የመገናኛ ብዙኅን እባካችሁ ለቀቅ አድርጉን እንሥራበት፡፡ አሁን ጊዜው የሥራ ነው እንጂ የአሉባልታ አይደለም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትንም አትጨቅጭቋቸው፡፡ ውጤቱን የሚያውቁት እነሱ ናቸው፡፡ ለእናንተ በሬ እንኳ ዝግ ነው፡፡ እባካችሁ በአገር ልማት ላይ እወቁበት፡፡ ነገር ፍለጋ፣  ቁስቆሳና አሉባልታ አያዋጣም፤ አገራችንን እንገንባ፤›› በማለት ማሳሰቢያ ይሁን ግሳፄ መሰል መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ቀደም ብሎ ለመገናኛ ብዙኅን ባስተላለፈው ጥሪ፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሆኑትን ሦስቱን የልማት ድርጅቶች በጨረታ ያሸነፉት፣ የሚድሮክ ሊቀመንበርና ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የርክክብ ፊርማ ሲያደርጉ በሥፍራው ተገኝቶ እንዲዘግብ ሪፖርተርንም ጠርቶት ነበር፡፡ በጽሕፈት ቤቱ ጥሪ መሠረት የሪፖርተር ጋዜጣ ዘጋቢና ፎቶግራፈር በሸራተን አዲስ የተገኙ ቢሆንም፣ ፎቶግራፈሩን የሚድሮክ የሕዝብ ግንኙነት ተቀጣሪ ታደለ አሰፋ የተባለ ግለሰብ ‹‹ሪፖርተር ከሚድሮክ ጋር ተስማምቶ እስከሚሠራ ድረስ ከእኛ ጋር እንዲሠራ አንፈቅድለትም፤›› በማለት በሆቴሉ ጥበቃዎች አማካይነት አስወጥቶታል፡፡
ከኤጀንሲው ጋር የርክክብ ፊርማ ሥነ ሥርዓቱን ያከናወኑት የሚድሮክ ሊቀመንበር የመገናኛ ብዙኅኑን በመገሰጽ አርፈው እንዲቀመጡ ከመወትወታቸውም በላይ የሕዝብ ግንኙነት ተቀጣሪ መሆኑ የተገለጸው ግለሰብ ደግሞ፣ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ወደ ግለሰብ ድርጅትነት ሲቀየር፣ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ በመንግሥት በኩል የተጠራን የመገናኛ ብዙኅን በጥበቃ እንዲወጣ ማድረጉ ለምን እንደሆነ ግልጽ አልሆነም፡፡ ይህ ድርጊቱ በሕገወጥ መንገድ ፕሬስን ለማፈን ከሚሯሯጡ ወገኖች ጋር ለመሰለፍ የሚያደርገው ሙከራ መሆኑን ድርጊቱን የታዘቡ ጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አፈና ከፕሬስና ከመረጃ ነፃነት ሕጉ አንፃር ተጠያቂነት የሚፈጥር በመሆኑ፣ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ የግድ መሆኑን የሕግ ባለሙያዎችም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት ተቀጣሪው የሪፖርተርን ዘጋቢ ለማስወጣት የፊርማ ሥነ ሥርዓቱን ለመታደም በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ሲያፈላልግ፣ የፊርማ ሥነ ሥርዓት መፈጸሚያው ሰዓት ደርሶ የርክክብ ሥርዓቱ በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረ መስቀልና በሚድሮክ ሊቀመንበር ሼክ አል አሙዲ ተፈጽሟል፡፡
ከፊርማ ሥርዓቱ በኋላ ሦስቱም ድርጅቶች ማለትም የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ የጐጀብ እርሻ ልማትና የቡና ማደራጃና ማከማቻ ድርጅት፣ በጥሩ አቋም ላይ መሆናቸውን የገለጹት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ሚድሮክን አድንቀዋል፡፡ አቶ በየነ እንደገለጹት፣ ሚድሮክ ለሦስቱም ኩባንያዎች ከፍተኛ የጨረታ ዋጋ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ተወዳዳሪዎቹን አሸንፏል፡፡ ሚድሮክ ከኤጀንሲው በርካታ ድርጅቶችን በመግዛት ጥሩ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለው፣ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙትን ሦስቱን ድርጅቶች ለሚድሮክ ሲሸጡ፣ ባሉበት እንዲቀጥሉ ሳይሆን ተጨማሪ ኢንቨስትመንት በማካሄድ የተሻለ ምርታማ ለማድረግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
‹‹ቋሚዎቹን ትተን ጊዜያዊ ሠራተኞችን ብንወስድ ከአምስት ሺሕ በላይ ናቸው፤›› ያሉት አቶ በየነ፣ ድርጅቶቹም ሆኑ ሠራተኞቹ በጥሩ እጅ ላይ መውደቃቸውንና አገሪቱም የበለጠ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ከሚገኝበት ደረጃ የሚያደርስ በማግኘቷ ደስተኛ መሆናቸውንና የሼክ መሐመድን ጥረትም እንደሚያደንቁ አስታውቀዋል፡፡
ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ሲቋቋም የመጀመርያው ፈር ቀዳጅ ገዥ ድርጅት ሚድሮክ እንደነበር ያስታወሱት ሼክ መሐመድ፣ ከኤጀንሲው የወሰዷቸው ድርጅቶች በሙሉ እያደጉ እንጂ ቁልቁል የሄደ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ሠራተኞችን በሚመለከትም፣ በገዟቸው ድርጅቶች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች በጡረታና በሞት ካልሆነ በስተቀር ሁሉንም ሠራተኞች በማስተማርና በማሠልጠን አቅፎ ከማሠራት ውጭ አንድም ሠራተኛ እንዳላበረሩ ገልጸዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኅን ዘገባ ያሳሰባቸው የመሰሉት ሼክ መሐመድ፣ ‹‹ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ነገር ቢኖር በመጀመርያ እኛ ካምፓኒ አይደለንም፤ የሰው ብር አልሰበሰብንም፤ የመንግሥትንም ብር አልወሰድንም፡፡ የራሳችንን ብር ባለን አቅም እያመጣን ነው ድርጅቶችን የምንገዛው፤›› ብለዋል፡፡ ኤጀንሲው ‹‹ተጫረቱ›› ብሎ ሜዳውንና ፈረሱን ለውድድር ሲያዘጋጅ እንደሚወዳደሩ የገለጹት ሼኩ፣ በሁሉም ጨረታዎች ላይ ሳይሆን መርጠው ስለሚወዳደሩ አሸናፊ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
ከ20 ዓመታት በፊት ጀምሮ በእርሻ ኢንዱስትሪ ለመግባት ፍላጐት እንደነበራቸው የተናገሩት ሼኩ፣ አሁን ዕድሉ በመገኘቱ ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ እርሻ ማድረጋቸውን፣ የአገሪቱን ልማት ወደፊት ለመውሰድና ለማሳደግ የውጭ አገር ኤክስፐርቶችን በማምጣት ጠንክረው ለመሥራት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡
እርሻ በጣም አድካሚና ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ መሆኑን የገለጹት ሼክ መሐመድ፣ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረጉት ኢንቨስትመንት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ቢሆንም፣ አንድ ሚሊ ሳንቲም ወደ ውጭ አለመውሰዳቸውንና አሁንም ለሚያካሂዱት አዳዲስ ኢንቨስትመንት ከውጭ እያመጡ እንደሚገዙ ተናግረዋል፡፡
ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ እንደታገሳቸውና የታገሳቸውም ‹‹መክፈሉ አይቀርም›› በሚል መሆኑን የተናገሩት ሼኩ፣ እንደሚከፍላቸው ስላመናቸው አመስግነዋል፡፡ የሚድሮክ እህት ኩባንያ በሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥር የሚተዳደረት የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ በ860 ሚሊዮን ብር ከመንግሥት መገዛቱንና በቀጣይ አምስት ዓመታት በተጨማሪ 432 ሚሊዮን ብር የድርጅቱን አቅም እንደሚያሳድግ ተገልጿል፡፡ የጐጀብ እርሻ ልማትም በ35.1 ሚሊዮን ብር መገዛቱንና በተጨማሪ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀ ባለ 500 ሔክታር የሙዝ እርሻ ለማካሄድ 15 ሚሊዮን ዶላር መመደቡም ተጠቁሟል፡፡ ለቡና ማደራጃና ማከማቻ ድርጅት 80.5 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ኢንቨስት ለማድረግ መታቀዱም ተወስቷል፡፡ ሆራይዘን ሲቋቋም 250 ሺሕ ሔክታር መሬት ከደቡብ፣ ከቤኒሻንጉልና ከጋምቤላ ክልሎች ተረክቦ አዲስ እርሻ ለማቋቋም፣ የሻይና የዘይት ምርቶችን ለማምረት የማሌዢያ አማካሪ ድርጅት በማስመጣት ማስጠናቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የሼክ አል አሙዲ ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ከባለኮከብ ሆቴሎቹ በመንግሥት ከ632 ሚሊዮን ብር በላይ የግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ እንደሚፈለግባቸው በቅርቡ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አማካይነት የዕዳ ጥያቄው መቅረቡን ዝርዝር ሐረታ ማቅረባችን አይዘነጋም፡፡
Source:-Ethiopian reporter

No comments:

Post a Comment