No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Friday, 12 April 2013

የለንደን ደብረጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሰሞኑ ሁኔታ (ቪዲዮ) አልአዛር ታረቀ



የለንደን ደብረጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በምእመናንና በካህናት መካከል በተነሳ ውዝግብ ስትናጥ ድፍን አንድ ዓመት አለፋት። ይህንን አለመግባባት ለማስወገድና ምእመናን እንደቀድሞዋቸው በሰላምና በፍቅር ጸሎታቸውን አድርሰውና ቤተ ክርስቲያናቸውን ተሳልመው በየቤታቸው እንዲሄዱ ለማድረግ ይረዳ ይሆናል ተብሎ፤ ብዙ ስብሰባዎች ተካሄዱ፤ ብዙ ኮሚቴዎች ተዋቀሩ። ነገር ግን ነገሩ እንደመብረድ ጭራሽ እየባሰበትና እያገረሸበት ሄደ። ቤተ ክርስቲያኗ በሁለት ጎራዎች ተከፈለች። በአንድ በኩል የአገልግሎት ዘመኔን ብጨርስም ከያዝኩት ሥልጣንና ኃላፊነት አልነሳም ብለው የሚሟገቱት የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ግርማ ከበደና ደጋፊዎቻቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአገልግሎት ዘመናቸውን የፈጸሙት የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪና የተለያዩ ኮሚቴዎች ወርደው በአዲስ ኮሚቴዎችና አስተዳዳሪ ይተኩ፤ ከቤተ ክርስቲያኗ ዕድገት ጋር የሚመጥን አዲስ የመተዳደሪያ ደንብም ይተካ የሚሉ ወገኖች።


ነገሩ እየተካረረ ሲሄድ እርስ በእርስ መወነጃጀልና መካሰስ ደረጃ ላይ ተደረሰና አባ ግርማ ለጊዜውም ቢሆን የቤተ ክርስቲያኗ ማህተምና ጽሕፈት ቤት በጃቸው ስለሚገኝ፤ ይቃረኑኛል ብለው ያሰቧቸውን አስራ አምስት ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያኗ እንዳይገቡ የሚያግድ ደብዳቤ ጽፈው በየአድራሻቸው ላኩላቸው። የታገዱት ሰዎች እሁድ ዕለት ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ሲመጡ፤ የአባ ግርማ ጋሻ ጃግሬዎችና ሌሎች ተቀጥረው የመጡ ጠባቂዎች፤ ቅጥር ግቢው መግቢያ ላይ በመቆም፤ ታገዱ የተባሉትን ሰዎች ማስገባት ይከለክላሉ። ያልታገዱና ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ለጸሎት ገብተው የነበሩ ሰዎች ግን፤ ግማሹን ምዕመናንን አግዶ እውጭ አቁሞ ለተመረጡ ሰዎች ብቻ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስጠት አግባብ አለመሆኑ ስለተሰማቸው፤ እውስጥ እንዳሉ ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ። እውጭ ታግደው ቆመው የነበሩት ምዕመናንም ውስጥ የተነሳውን ተቃውሞ ሲሰሙ፤ ጠባቂዎቹን ጥሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ተቃውሟቸውን አብረው ማሰማት በመጀመራቸው የቤተ ክርስቲያኑ አገልግሎት ተቋርጦ አባ ግርማ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብተው መሸጉ። በመጨረሻ ከስምንት ሰዓት በላይ ከፈጀ የአባ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ውዝግብ በኋላ አባ ግርማ በፖሊሶች አማካይነት ከመቅደስ ወጥተው የቤተ ክርስቲያኗን ቁልፍ በቦታው ከነበሩት ካህናት መካከል ለአንዱ አስረክበው ከግቢው እንዲወጡ ይደረጋሉ። ምዕመናኑ ቁልፉን ከተረከቡት ካህንና ከሌሎች አባላት ጋር ማክሰኞ ዕለት እዚያው ቤተ ክርስቲያን ተገናኝተው ስብሰባ ተደርጎ ችግሩን በውይይት ለመፍታት ስምምነት ላይ ተደርሶ ሕዝቡ ወደ የቤቱ ይሄዳል።

ማክሰኞ ዕለት ከመቶ የበለጡ ምዕመናን እጅግ በሚሰቀጥጥ ብርድ ቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ተሰብስበው ቁልፍ የያዘውን ካህን ሲጠብቁ፤ ለስብሰባ ለመምጣት የተስማሙት አባላትም ቁልፉን የያዘው ካህንም ሳይመጡ ቀሩ። በዚህ መልኩ አባ እና ደጋፊዎቻቸው ተቃዋሚዎቻቸውን በብርድ ቀጥተው ደስታን አገኙ። በሳምንቱ እሁድም ቤተ ክርስቲያኗ ሳትከፈት ቀረች። ምዕመናን በቦታው በተገኙ ካህናትና አስተማሪዎች ቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ ጸሎት አድርገውና የወንጌል ትምህርት ተቀብለው ተለያዩ። አባ ግርማና ቁልፉን የተረከበው ካህን ግን በዕለቱ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ብቅ ባይሉም፤ ‘መዘምራን’ ብለው የሚጠሯቸውን ደጋፊዎቻቸውን ልከው ነበር። የአባ ደጋፊዎች በዕለቱ በቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ለብቻቸው ተነጥለው በአንድ ወገን እንዳሉ፤ ከሕዝቡ ጋር ሆነው በማስተማር ላይ የነበሩት ካህን ወደ እነሱ ጠጋ ብለው አብረው ለማስተማር ቢሞክሩም ከእነሱ ጋር ሆነን መማር አንፈልግም ብለው ከማፈንገጣቸውም በላይ፤ አባ ግርማ ሳይኖሩ ለማስተማር የመጡትን ካህናት ለምን እንደሳቸው መንጋውን በትነው አልቀሩም ብለው በቁጭት ሲያብጠለጥሏቸው ነበር። ይህ ሁኔታ በሳምንቱም ተደግሞ ቤተ ክርስቲያኗ እንደተዘጋች፤ ምዕመናኑ ግን ቤተ ክርስቲያናቸው ቅጥር ግቢ ድረስ መጥተው፤ እንደተለመደው በሁለት ጎራ ተከፍለው የአባ ግርማ ደጋፊዎች በአንድ በኩል ሌሎች በሌላ በኩል ሆነው እየተገለማመጡና በክፉ ዓይን እየተያዩ፤ የአባ ደጋፊዎች የአባ ደጋፊ በሆነ ካህን የአባ ተቃራኒ ደግሞ በሌላ ካህን አማካይነት ጸሎታቸውን አድርሰው ሄደዋል። በዚህም ዕለት የአባ ደጋፊዎች የሆኑ ‘መዘምራን’ በሌላው ጎራ የተሰለፈውን ቡድን ያስተማሩትን ካህን እንደተለመደው ሲዘልፏቸው ነበር።
የሰሞኑ የለንደን ደብረጽዮን ማርያም ምዕመናን ሁኔታ አጠር ባለ መልኩ ሲታይ ይህንን የሚመስል ነበር። እና ምንድነው መደረግ ያለበት? መፍትሔውስ ምንድነው?እንደዚህ ዓይነቱ በሁለት ጎራ መከፈልስ ምን አመጣው? የሚሉት ጥያቄዎች በሁሉም አእምሮ የሚመላለስ ጥያቄ ነው። ብዙ ጊዜ ሕብረተ ሰባችን ነገሮችን ግልጥ አድርጎ መናገር ይፈራል። ሰዎችን ላለማስቀየም ስንል አይተን እንዳላየ፤ ሰምተን እንዳልሰማ መሆንን እንመርጣለን። የአንድን ግለሰብ ስሕተት ገልጾ እንዲያሻሽል ከመንገር ይልቅ፤ እንዴት ብዬ እነግረዋለሁ? ብነግረውና ቢቀየመኝስ? ብለን ሸፋፍነን እንተዋለን። ግን ስለድክመቱና ስሕተቱ ለሌሎች እናወራለን። በለንደን ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ያጋጠመን ችግር ከላይ የገለጽኩት ልምዳችን ነጸብራቅ ይመስለኛል። ስለዚህ ይህንን አጉል ይሉኝታና ተብታቢ ባሕል እርግፍ አድርገን እንተውና እርስ በእርሳችን በግልጽ ተነጋግረን፤ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋትና ምዕመናኑን ለመበታተን የተነሱትን ሰዎች ዓላማና ስሕተት በግልጽ ሁሉም እንዲያውቀው አፍረጥርጠን መናገር ይጠበቅብናል። ሕዝቡ ሁኔታውን ካወቀና ከተረዳ በኋላ ባገኘው መረጃ ላይ በመንተራስ የራሱን ውሳኔ ለመውሰድ ይችላል። ያለበለዚያ ግን እንዲሁ እንደተናቆርን መኖራችን ነው። ይህም በመሆኑ እኔ በግሌ ይህችን ግልጽ ደብዳቤ ለአባ ግርማ ከበደ መላክ እወዳለሁ።
ግልጽ ደብዳቤ ለአባ ግርማ ከበደ
የለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ለእርስዎ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ስለሆነ እተወዋለሁ። ያለመግባባቱ ከውስጥ ለውስጥReese Adbarat Saint Mary of Debre Tsion Ethiopian Orthodox Church መጎሻሸም አልፎ አደባባይ ስለወጣ በሬድዮም፤ በምስልም ሁኔታውን ሁላችንም እየተከታተልነው ነው። እስከአሁን በራዲዮ ከሰማኋቸውና በምስል ካየኋቸው የእርስዎ ደጋፊዎች ኢንተርቪው እንደተረዳሁት፤ ክርክሩም ሆነ ሙግቱ በሙሉ በሃሰት ላይ የተመሠረተ ነው። እንኳን ሌላ ቀርቶ፤ የቤተ ክርስቲያኗ ማህተም ታትሞበት፤ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ፤ እርስዎ ራስዎ ባሉበት ለሕዝብ የተሰራጨውን የመተዳደሪያ ደንብ ረቂቅ፤ አንድ ከእርስዎ የወገኑ ካህን ‘ሰነዱ ሕጋዊ አይደለም፤ በድንገት የተሰራጨ ነው፤ ጸሃፊው በቤተሰብ ጉዳይ ምክንያት አዲስ አበባ ሄዶ ስለነበር ነው’ የሚሉ፤ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው፤ አሳፋሪ ምክንያቶች ዕውነቱ እያነቃቸውና አፋቸው እየተሳሰረ ለመደርደር ሲሞክሩ ታይተዋልል። ከፍ ብዬ እንደገለጽኩት ጉዳዩ አሁን የአደባባይ እንጂ የማጀት አይደለም። ዛሬ የተናገርኩትን የሰማኝ አንድ ሰው ብቻ ስለሆነ ነገ መለወጥ እችላለሁ ከሚባልበት ደረጃ አልፏል። ስለዚህ እውነቱን መናገር ከእርስዎም ሆነ እርስዎ ልከዋቸው ከሚቀርቡ ሰዎች እንደሚጠበቅ ማወቅ አለብዎት። ዕውነት መናገር ደግሞ የማንኛውም ክርስቲያን ባሕሪ ሲሆን በተለይ የኃይማኖት አባቶች ለሌላውም አርአያ በሚሆን መልኩ ዕውነተኛ ነገርን ይዘው እስከመሰዋት ድረስ መሄድ ይጠበቅባቸዋል።
አንድ አንጋፋ ፖለቲከኛ ስለቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ውሸታምነት ሲናገሩ፤’መለሰ ሌላው ቀርቶ በትክክለኛ ስሙ እንኳን የማይጠራና በውሸት ስም የሚጠራ መሪ ስለሆነ ምንም ቢናገር የሚታመን ሰው መሆን የለበትም’ ያሉትን ዘወትር አስታውሰዋለሁ። ይህንን በምን አነሳሁት መሰለዎት? የለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ውዝግብ በተመለከተ አንዳንድ ጽሁፎች በድረ ገጾች ላይ ሰሞኑን ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምሩ፤ ዋናው ተዋናይ እርስዎ አባ ግርማ ከበደ መሆንዎ በተደጋጋሚ እየተወሳ ነው። ታዲያ አንዳንድ ጽሁፎች ላይ እንደተጠቆመው ዕውነተኛ ስምዎ ግርማ ከበደ ሳይሆን ሌላ እንደሆነ ነው ያነበብነው። ይህንን የሚናገሩት ደግሞ አሁን የተጣሏቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ቀድሞ የሚያውቁዎት ጭምር ናቸው። ሰው መቼም ስሙን በሕጋዊ መንገድ መለወጥ መብቱ ስለሆነ፡ ለምን ስምዎን ለወጡ ብሎ መተቸቱ አግባብ አይሆንም። ግን እስቲ ‘እረኛው ነኝ’ ‘አባቱ ነኝ’ ብለው ለሚሉት ሕዝበ ክርስቲያን ዕውነተኛ ስምዎ ማን እንደሆነ፤ ለምንስ እንደለወጡት፤ በሕጋዊ መንገድ ይሁን አይሁን ገልጸው ይንገሩትና ይወቀው። የሚደብቁትና የፈጸሙት ወንጀል ኖሮ ነው? ወይስ እንደማንኛውም ዓለማዊ ሰው ወደ እንግሊዝ ሃገር ሲሰደዱ በሌላ ሰው ስም ነው የመጡት? በሕጋዊ መንገድ ለውጠውት ከሆነ ሃሜቱ አይመለከትዎትም። ግን በጓዳ በር ከሆነ ስምዎን የለወጡት፤ ዕውነተኛ ስምዎን እንኳን የሚደብቁ ግለሰብ በመሆንዎ ታማኝነትዎን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። ደግሞ ከለወጡትስ አይቀር ምናለበት ነበር እንደመነኩሴነትዎ በስመ ክርስትናዎ ቢለውጡት? ካላጡት ስም ‘ግርማ ከበደ’ ለምን እንዳሉት ይገርመኛል!
አባ! እኔ ገና ስምዎን ስሰማ ያስደነገጠኝ ነገር ቢኖር፤ ‘ምን ሲሉ ይህንን ስም መረጡት?’ ብዬ ነው። ለምን እንደሆነ በአጭሩ ልግለጽልዎት። የወጣትነት ዘመናችንን በኢትዮጵያ የአብዮትና የቀይ ሽብር ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ ያሳለፍን ሁሉ ይህንን ስም የምንዘነጋው አይመስለኝም። በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም በአራት ኪሎና በቅድስት ማርያም አካባቢ ብዙ ወጣቶችንና ሠራተኞችን በጋለ ካውያ በማቃጠል፤ በኤሌክትሪክ ሽቦ አንቆ በመግደልና በግርፋት በማሰቃየት የታወቀውን ግርማ ከበደ የሚባለውን የቀበሌ ሊቀመንበር ነበር ያስታወሰኝ። ግርማ ከበደ በቀበሌው ውስጥ በሰዎች ላይ የሚያደርሰው ስቃይና ሰቆቃ እጅግ ከመጠን ያለፈ አሰቃቂ በመሆኑ፤ እንኳንስ ተቃዋሚዎቹን፤ ራሱን ሥራውን ሲያከናውንለት የነበረውን ደርግን ስላሰቀቀው፤ በመጨረሻ ላይ “አረመኔው ግርማ ከበደ” የሚባል ቅጽል ስም ተሰጥቶት በደርግ ተይዞ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሕዝብ በተሰበሰበበት በጥይት ተደብድቦ እንዲገደል የተደረገ ካድሬ ነበር። በአረመኔው ግርማ ከበደ ላይ የመጨረሻውን የሕዝብ ቁጣ ያስነሳበት፤ ዳሮ ነጋሽ የተባለችውን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ትሠራ የነበረች፤ የዘጠኝ ወር እርጉዝ፤ ጸረ አብዮተኛ ናት በሚል ምክንያት አስሮ በጋለ የኤሌክትሪክ ካውያ እያቃጠለ ሲያሰቃያት ጽንሱ ሆዷ ውስጥ ሞቶ የእርሷም ሕይወት በማለፉ ነበር። እና አባ በዕውነት እንደሚነገረው ስምዎ ሌላ ከሆነ ምኑ ደስ ብሎዎት ነው በዚህ ሰው ስም የተኩት? ወይንስ በአንዳንድ ዕምነቶች እንደሚወራው አንድ ሰው ከሞተ በኋላ እንደገና ይወለዳል እንደሚባለው ግርማ ከበደ እንደገና ተወልዶ ይሆን?
አረመኔው ግርማ ከበደ የአብዮት ጠባቂዎቹን እየላከ የቀበሌውን ነዋሪዎች እያዋረደ፤ እንደሚያስረውና እንደሚያንገላታው ሁሉ፤ እርስዎም “መዘምራን” ብለው የሰበሰቧቸውን መረን ኮረዳዎች እየላኩ፤ የተከበሩ አረጋውያንን የሚያሰድቡና የሚያዋርዱ፤ የመስቀል ምስል ቆባቸው ላይና ቀሚሳቸው ላይ በግዙፍ የተሳለበት ልብስ ለብሰው፤ አምላክን እንዲያመሰግኑና ለስሙ እንዲዘምሩ የተመረጡ፤ ተብለው አውደ ምህረት ላይ ቆመው፤ ልክ ጉልት ገበያ ላይ እንደተጣሉ ቀሬዎች አንገታቸውን እየሰበቁ የሚሳደቡ ቦዘኔዎችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያሰማሩና ይህንንም ሲፈጽሙ የማይገስጹ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆንዎ፤ በማንኛውም መስፈርት ለቦታው የማይመጥኑ ነዎት ብሎ ሕዝብ ሁሉ ፈርዶብዎታል።
እነዚህ ‘መዘምራን’ብለው ያሰማሯቸው ወጣቶች፤ በራስዎ ህሊና ሲገምቱት አፋቸውና ልባቸው የቱን ያህል ያልተገናኘ መሆኑን አያዩምን? ወይንስ እርስዎን በመደገፍ ሌላን ማዋረድና መዝለፍ ትክክል ነው ብለው ነው ያስተማሩዋቸው? አብዛኛዎቹ ስድባቸውንና ዘለፋቸውን ከመጀመራቸው በፊት እንደ መግቢያ የሚጠቀሙበት ‘ይሄ እኮ የእግዚአብሄር ቤት ነው’ የሚለውን አባባል ነው። አባ ግርማ! ብዙዎቻችን ቪድዮ ክሊፑን አይተናል እርስዎም እዚያው ቆመው ነበርና፤ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት? ዕውን ያንን ቤት እንደ ቤተ እግዚአብሄር ያከበሩት ያ ሁሉ ስድብና ዘለፋ ሲወርድባቸው፤ ከተቀመጡበት እንኳን ሳይነሱ፤ እጃቸውን አጣምረው፤ በትዕግስት ያዳመጡትና መልስ እንኳን ያልሰጡት አዛውንቶች ናቸው? ወይንስ አንገታቸውን እየነቀነቁና ወገባቸውን እየሰበቁ ተሰዳቢዎቹ አዛውንቶች ድረስ እየሄዱ እንደ ወፈፌ ድምጻቸው እስኪዘጋ ድረስ ሲሳደቡ የነበሩ ኮረዳዎች ናቸው? ዕውነተኛ ከሆኑ መልሱን ያውቁታል።
ነገሩን ለማጠቃለል ዙሪያዎትን የተከበቡት ጃስ ሲሏቸው ዘልለው ለመናከስ ባኮቦኮቡ፤ ነገሮችን ለማመዛዘንና ለማስተዋል መብሰል በተሳናቸው፤ ሃሳብን በሃሳብ ከመዋጋት ይልቅ ‘አገጭህን አወልቅልሃለሁ’ በሚሉ ጋጠ ወጥ ጎረምሶችና፤ ምላሰኛ ኮረዳዎች መሆኑን አልተረዱም? ወይስ እሥልጣን ላይ ለመቆየት እስከረዱኝ ድረስ በማንስ ብከበብ ምንቸገረኝ ብለው ነው የተቀመጡት? ከእርስዎ ከመነኩሴው በላይ ባላውቅም፤ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ሥርዓት የሚማሩበት፤ አዛውንቶች በዕድሜያቸው የሚከበሩበት፤ ዕውነት የሚነገርባት ቦታ እንጂ፤ የተሳዳቢዎች መጠራቀሚያ፤ የአዛውንቶች መሰደቢያና የሃሰት ማሰራጫ ቦታ መሆን ነበረባት? ቤተ ክርስቲያኗ የሁላችን እንጂ የግልዎ እንዳልሆነችም መገንዘብ እንዴት እንደተሳነዎት ያሳዝናል። ከተግባርዎ እንደሚታየው እንኳንስ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት ለተራ ምዕመንነት የሚበቃ የሞራል ደረጃ ላይ አይደለምና ያሉት፤ እንደ ግል መደብርዎ ቆልፈው የሄዱትን ቤተ ክርስቲያን በአስቸኳይ ከፍተው ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀው ለጥቂት ጊዜ ዞር ቢሉ የተሻለ ከበሬታ ያገኛሉ። ከዚህ ባሻገር ሌላ ደባ ቢሰሩ ግን ዕውነቱ መገለጹ ስለማይቀር፤ በዚያን ጊዜ በውርደት ተባርረው በኃፍረት እንደሚኖሩ ይወቁት። እስቲ እስከአሁን የደረሰብዎትን ውርደት እንኳን ጥቂቶቹን ዘወር ብለው ለማጤን ይሞክሩ፤
-በኢትዮጵያ ኮሙኒቲ እራት ግብዣ ላይ ተገኝተው እንደ አባት ገበታውን ባርከው ማስጀመር ሲገባዎት ሕዝቡ መምጣትዎትን በመቃወሙ እንደማንኛውም እንግዳ ተራ ጠብቀው ራት እንዲያነሱ ተደረጉ፤
-በአንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ መታሰቢያ ዝግጅት ላይ መገኘትዎን ተጋባዡ ሕዝብ በመቃወሙ፤ ልክ በኢትዮጵያ ኮሙኒቲ እንደደረሰብዎት ሁሉ እንደ አባትነትዎ ሥነ ሥርዓቱን በቡራኬ መክፈትና መዝጋት ሲገባዎ ያንን ዕድል ተነፈጉ፤
-ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መቀደስ የለባቸውም የሚል ተቃውሞ ተነስቶብዎት እመቅደስ ውስጥ ተደብቀው ስንት ሰዓት ሙሉ ቆይተው ቁልፍ አስረክበው በፖሊስ ታጅበው በስርቆሽ በር እንዲወጡ ተደረጉ፤
-አንድን ምዕመን መስቀል ለማሳለም አውጥተው ሲቀርቡ ‘እኔ አንተ የያዝከውን መስቀል አልሳለምም’ ተብለው በሰው ፊት ተዋረዱ፤
ይሄ እንግዲህ በጥቂቱ ለመጥቀስ ነው እንጂ የቀረውን ደግሞ ራስዎ ያውቁታል። እርስዎ መነኩሴ እንጂ የፖለቲካ ሹመኛ አይደሉም። መነኮሰ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተዘንግቶዎት ከሆነ ልብ ይግዙና ለማስታወስ ይሞክሩ። እንደ አለባበስዎ በተግባርዎም መነኩሴ ከሆኑ፤ ዓለማዊ ሹመት፤ ሥልጣን፤ የገንዘብ ማካበትና የጋለሞታዎች አጀብ አይጠቅምዎትም። በዕውን የእግዚአብሄር አገልጋይ ከሆኑ በአባትነት ከሚያስተዳድሩት ሕዝብ መካከል እንኳን በመቶዎች የሚቆጠሩ ይውረዱ እያሉዎትና የተመረጡበት የአገልግሎት ዘመን አክትሞ ይቅርና፤ ጥቂቶች እንኳን ከቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት ይነሱ ቢሉዎት፤ ‘እኔ ስለመረጣችሁኝ ላገልግላችሁ ብዬ ነው እንጂ ዓለማዊ ሹመት ለእኔ ምኔ ነው?’ ብለው እግዚአብሄርን ማገልገል እንደመቀጠል፤ ‘ነፍስ እንዋደቃለን እንጂ ከዚህ ቦታ አልወርድም!’ ብለው መፎከርዎ ተሰምቷል። አሁን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነፍስ መዋደቅን ምን አመጣው? ለዚህ ለዓለማዊ ሹመት ሲሉ ሰው ሊገድሉ ነው? ወይንስ በጋሻ ጃግሬዎችዎ አማካይነት ሊያስገድሉ ነው?
አባ! ባሉበት ሃገር እንኳንስ የሃይማኖት መሪ የፖለቲካ መሪም ዘመኑን ሲጨርስ ይወርዳል። እዚያ ጥለነው የመጣነው ሃገር ላይ ብቻ ነው ‘ነፍስ እንዋደቃለን እንጂ ማን ያወርደኛል?’ የሚባለውና፤ ይህንን ጠባይዎን እዚያው ያድርጉት። የእስከ አሁኑ ውርደት ይበቃዎታልና ይበልጥ ሳይዋረዱ በሠላም ቦታውን ይልቀቁ። ዙሪያዎትን የከበቡዎት አንድ ቀን የምድር አዋቂ ዘንድ ሌላ ቀን ቤተ ክርስቲያን የሚሉ ጋለሞታዎችና ድረ ገቦች፤ ያፈረሱ ዲያቆናት፤ ፖሊስ ሲመጣ አንገቱን የሚደፋና ፖሊስ ዘወር ሲል ደግሞ ልደባደብ እያለ የሚጋበዝ አውቆ አበድ፤ በተደጋጋሚ የለንደንን የማርያም ቤተ ክርስቲያን ለማዘጋት ሞክሮ ያልተሳካለትና አሁንም እርስዎ ጉያ ውስጥ ተደብቆ ያንኑ ተልዕኮውን ለማሳከት የሚቅነዘነዝ ደብተራ እና አንገታቸውን እየሰበቁና ወገባቸውን እየያዙ አውደ ምህረትን አርክሰው ተራ ስድብ የሚሳደቡ መረን የተለቀቁ ‘መዘምራን’ ለውድቀትዎ መነሻና ማፋጠኛ ይሆኑዎት እንደሆን ነው እንጂ የሚጠቅሙዎት አይደሉም። ግን ሰሞኑን በአንድ ከኢትዮጵያ ለማስተማር በመጣ መምህር ላይ እርስዎና አጋርዎችዎ የፈጸሙትን ደባና ተንኮል የሰማና የተመለከተ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፤ ‘እነዚህን መዘምራንስ በምን ማስፈራሪያ እየተጠቀሙ ይሆን እንደዚህ ጃስ! ሲሏቸው አዛውንትና ካህን ሳይለዩ ለማዋረድ የሚነሱት?’ ብሎ ያዝንላቸዋል እንጂ የሚፈርደው በእርስዎና በግብረ አበሮችዎ ላይ መሆኑን አይጠራጠሩ።
አባ ግርማ፤ እንኳን ደስ ያለዎ! ለጊዜውም ቢሆን በእርስዎ ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን የውዝግብ ቤት ሆናለች፤ እርስ በርሳችን ተከፋፍለናል፤ በገንዘባችን የገዛነውን ቤተ ክርስቲያን ቆልፈው ተደብቀው በለንደን ብርድ አረጋውያንና ሕጻናት ተቀጥተዋል። የተከበሩና ቤተ ክርስቲያኗን ከአስርና ከሃያ ዓመት ያላነሰ ያገለገሉና አሁን ላለችበት ደረጃ ያበቁ አባቶች፤ ትናንት በጓዳ በር ባስገቧቸው የእርስዎ መልእክተኞች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰድበዋል ተዋርደዋል፤ አንድ የነበረውን ሕዝብ አናክሰው እንዳይተማመን አድርገዋል። ወደዱም ጠሉም ከዚህ ሁሉ በደል በኋላ በለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቦታ አይኖርዎትም። መሄድዎ አይቀሬ ነው። ሲሄዱም ፍቅር መስርተው በመሄድ ፋንታ መርዝ ረጭተው በመሄድዎ ዘወትር በክፉ ሲታወሱ ይኖራሉ። ልክ የስም ሞክሼዎትን ‘አረመኔው ግርማ ከበደን’ ዘወትር በክፉ ግብሩ እንደምናስታውሰው እርስዎንም በከፋፋይነትዎ፤ በጸረ ፍቅርነትዎና ቤተ ክርስቲያናችንን በዓቢይ ጾም ቆልፈው ሕዝቡን በማጉላላትዎ ምንጊዜም እናስታውስዎታለን።
ያም ሁሉ ሆኖ ግን፤ እርስዎም ከአሁኑ ለከፋ ውርደት ሳይዳረጉ፤ ሕዝቡንም የባሰ ሳያቃቅሩና ሳያጣሉ፤ የዘጉትን ቤተ ክርስቲያን ከፍተው ሕዝቡ የቀሩትን የጾም ቀናት በቤተ ክርስቲያኑ እንዲሰባሰብ አድርገው፤ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀውና እርስ በእርሱም እንዲታረቅ መክረው፤ ሥራውን በሠላም አስረክበው ዘወር ቢሉ ትልቅ አስተዋይነት ነውና፤ እንደ ዓለማዊ ሰው እልኸኛነትዎን ትተው እንደ መንፈሳዊ አባት የሠላም መንገድ እንዲከተሉ፤ እኔ ዓለማዊው ሰው የተገላቢጦሽ እርስዎን መንፈሳዊውን አባት በዚች ግልጽ ደብዳቤዬ እመክርዎታለሁ።
source:-

No comments:

Post a Comment