No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Sunday, 7 April 2013

በማሳጅ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ የወሲብ ንግዶች ተበራክተዋል



ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ማን እንደሆነ አይታወቅምClick to show "sensual massage" result 10
በአዲስ አበባ ከተማ ከሥነ ምግባር ውጭ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ሲባል በማሳጅ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ፀያፍና ኢሞራላዊ ድርጊቶች የማኅበረሰቡን እሴት የሚያጠፉና የውበት ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ዝቅ የሚያደርጉ በመሆኑ ድርጊቱን ለማስቆም መንግሥት ዕርምጃ እንዲወስድ፣ የኢትዮጵያ ሥነ ውበት ሥራ ማኅበር ጥያቄ አቀረበ፡፡
ማኅበሩ ይህንን ጥያቄ ያቀረበው መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባደረገው ስብሰባ ነው፡፡
“ሙያው በዱርዬዎች ተጠልፏል” የሚሉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ዘሚ የኑስ፣ ሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት እንሰጣለን የሚሉ ማሳጅ ቤቶች እዚህም እዚያም እየተከፈቱና ድርጊቱም ወረራ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ ጥቂት ድርጅቶች የሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት በሚሰጡበት ከተማ ውስጥ ሙሉ ቀንና ሌሊት የሚሠሩ ማሳጅ ቤቶች ቁጥር በየዕለቱ መጨመር አሳሳቢ ነው ብለው፣ ወጣት ሴቶችን እያጠመደና የማኅበረሰቡን ደኅንነት እያናጋ ያለው የማሳጅ ቤቶች ውስጥ ነውር ተግባር ሥር እየሰደደ ለመሆኑ አመላካች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝምና ጤና ቢሮዎች፣ የአዲስ አበባ የሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ማዕከልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ ነገር ግን በማሳጅ ቤቶች ውስጥ በሙያው ስም እየተደረገ ያለውን ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ሕገወጥ ድርጊት ተከታትሎ የማስቆም ኃላፊነት ያለበት የመንግሥት አካል ማን እንደሆነ በግልጽ ሊቀመጥ አለመቻሉ ተወስቷል፡፡
ማሳጅ ቤቶች ሰዎች ለመነቃቃት፣ ሰውነታቸውን ዘና ለማድረግና ከውጥረት ስሜት ውስጥ ለመውጣት የሚኬድባቸው የፈውስ ቤቶች መሆን ሲገባቸው የወሲብ ተመራጭ ቦታዎች እንደተደረጉ፣ ይህ ከምዕራቡ ዓለም የመጣ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ባህል ከተማዋን እንደወረራት የሚያሳይ ጥናቱን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በያዝነው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡
የውበት ሥራ ማሠልጠኛዎች እንዲሁም የጤና ጥበቃና የፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮች እንደሚሉት፣ በሙያው ስም ከመስመር የወጡ ነገሮች ሥር በመስደዳቸው በማሳጅ ሥራ የሠለጠኑና የብቃት ማረጋገጫ ያላቸው ወንድ ባለሙያዎች በበርካታ ማሳጅ ቤቶች “ወንድ አንቀጥርም” በመባላቸው፣ አቤቱታቸውን ይመለከታቸዋል ላሉዋቸው የመንግሥት ተቋማት አቅርበዋል፡፡ አቤቱታው ከጤና ቢሮ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከዚያም ተመልሶ ወደ ጤና ቢሮ በመጨረሻም ፍትሕ ሚኒስቴር ድረስ ደርሷል ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በቀጥታ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ባለመታወቁ በማሳጅ ስም በየመንደሩ ለሚከፈቱ “የሴተኛ አዳሪ ቤቶች” መስፋፋት በር መክፈቱ በተሳታፊዎች ተገልጿል፡፡
በማሳጅ ቤቶችና በማሠልጠኛዎች በባለሙያ ቅጥርና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንዲህ ዓይነቱን ነውር ለመከላከል በግል የሚያደርጉት ጥረት እንዳለ ሆኖ፣ ከሙያው ጋር ግንኙነት የሌላቸው ነገር ግን ገንዘብ መሰብሰብ የፈለጉ ግለሰቦች በየቦታው ማሳጅ ቤቶች የሚከፍቱበት፣ በአንድ ወይም በሁለት ሳምንት ሥልጠና የማሳጅ ባለሙያ የሚኮንበት፣ ይባስ ብሎ ምንም ዓይነት ሥልጠና ላልወሰዱ ሰዎች በገንዘብ ሠርተፊኬት ተገዝቶ ማሳጅ ቤት የሚከፈትበት ሁኔታ ሲፈጠር እንኳ፣ ዕርምጃ መውሰድ የሚገባው  የመንግሥት አካል ይኼ ነው ተብሎ ሊታወቅ አለመቻሉ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡
“ማኅበሩ ይህንን ችግር በተመለከተ አንድ ነገር እናድርግ ብሎ መጥራቱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሩ እንዲህ ሥር ሰድዶ እየታየ መጠራትና መሰብሰብ ያለብን በአንድ የመንግሥት አካል ነበር፤” ያሉት የአሜን እንግዳ ማረፊያና ማሳጅ ቤት ባለቤት አቶ ወንድወሰን ጌታቸው ናቸው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት የማሳጅ ቤቶችን የሥራ ፈቃድና ግብር መሰል ጉዳዮች የሚያገባው የመንግሥት አካል ሲኖር፣ በማሳጅ ቤቶች ውስጥ በሙያው ስም የሚፈጸሙ ፀያፍና ሕገወጥ ድርጊቶችን የሚቆጣጠር ተቋም አለመኖሩ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ “አሁንም ከዚህ ስብሰባ በኋላም የሚመለከተው የመንግሥት አካል አልታወቀም፡፡ ጤና ቢሮ፣ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ሌሎቹም የበኩላቸውን እንዲህ እናደርጋለን ቢሉም በቀጥታ የሚመለከተው አካል አልተለየም፡፡ ለማሳጅ ቤቶች የሥራ ፈቃድና ለባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ እየተሰጠ ባለበት ሁኔታ በሙያው ስም የሚሠራ ሕገወጥ ድርጊትን የሚቆጣጠር አካል እንዴት አይኖርም?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ይህንን ድርጊት መንግሥት በአስቸኳይ እንዲያስቆም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው አካል መታወቅ እንዳለበት በተሰብሳቢዎቹ ተወስቷል፡፡
Source:-Reporter

No comments:

Post a Comment