ከደቂቃዎች በፊት የኤሊያስ ወንድሙን የኢሣት ቃለ ምልልስ እየተከታተልኩ ነበር፡፡ ያን ቃለ መጠይቅ እንዳገባደድኩ ኤልያስ የሚመራው የፀሐይ አሣታሚ ድርጅት እስካሁን ካሣተማቸው 60 ያህል መጻሕፍት ለየትኞቹ ይበልጥ ክብደት እንደሚሰጥ ሲጠየቅ ከጠቆማቸው ሥራዎች መካከል በሁለተኛነት የጠቀሰው የቀድሞውን መሪ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያምን(ባሉበት ሰላምታዬ ይድረሳቸው) ‹ትግላችን› የሚል መጽሐፍ ነበርና ጀማምሬው ሳበቃ ሁሉንም ሳላነብ ዴስክቶፕ ላይ ያኖርኩት ይሄው መጽሐፍ ትዝ አለኝ፡፡ ከጅምሩ እንደገና ላነበው ፈቀድኩናም ወደንባብ ክፍል አመራሁ፡፡ ግን እውነት ልናገርና ሸከከኝ፤ ዱሮውንም ሸክኮኝ ነበር ሳልጨርስ የተውኩት፡፡ እናገራለሁ፡፡
ኤሊያስ ወንድሙ ባቋቋመው አሣታሚ ድርጅት በኩል እየሠራው ያለው ነገር እጅግ በጣም የሚደነቅና እንደርሱው አገላለጽ የፈራረሰን የሀገር ድልድይ ለመጠገንና የተጓደለውን ለማሟላት የሚረዳ ምርጥ ሥራ መሆኑን ሳልጠቁም ማለፍ አልወድም፡፡ ይህን የልጅ ዐዋቂ ግሩም ዜጋ ከዐይን ጠብቆልን በጀመረው መንገድ ወደፊት ዘልቆ ብዙ እንዲሠራና ለነጻነት ቀንም ፈጣሪ እንዲያደርስልን ቢያንስ በጸሎታችን አንለየው፡፡ ከእርሱ ጋር ሆነው ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ የሚለፉ ምሁራንና ለሀገር ተቆርቋሪ ወገኖችም እንዲሁ ዕድሜውንና ተርፎ የሚቀር በረከቱን እንዲያድልልን ፈጣሪን እንለምነው፡፡ ልብ ለሌላቸው ብኩንና እንደጋሪ ፈረስ ልቦናቸው ለታወረ አስተሳሰባቸውም ከሆድ እስከአፋቸው ብቻ የተቀነበበ ቂመኛና በቀለኛ ወንድምና እህቶቻችንንም እግዚአብሔር በፀጋው እንዲጎበኛቸውና ከተተበተቡበት የተንኮለኝነትና የመሠሪነት ልክፍት እንዲሁም የሥልጣንና የንዋይ ፍቅር እንዲያላቅቅልን አንድዬን አጥብቀን እንለምነው – የሚሣነው ነገር የለምና፡፡ እነሱ ካሉ የምናልመው ነጻነትና እኩልነት ብሎም ዴሞክራሲ ህልም እንደሆነ ይቀራልና ከነዚህ ማፈሪያ ዜጎች ባፋጣኝ እንዲገላግለን አሁንም በርትተን እንጸልይ፡፡ የበግ ለምድ ለብሰው በመካከላችን እኛን መስለው ከሚመላለሱ የሁለት ዓለም ሰዎችና ለይቶላቸው ጠላት ሆነው ከጠላቶቻችን ጋር ከተሠለፉ በመልክ እኛን በተግባር ግን በሀገርና ወገን አፍራሽነት ከተሠማሩ ኅሊናቢስ ዜጎች የሚመደቡ ሸፍጠኛ ዜጎች ለአንዴና ለመጨረሻ ይገላግለን፤ ጸሎታችን ይሥመር፡፡
ኤሊያስ ሲናገር ከሰማሁትና የአሜሪካን መንግሥት ከምሥጢርነት ደረጃ አውርዶ ካሰራጫቸው ኢትዮጵያ ነክ የቀድሞ ምሥጢሮች መካከል ቀልቤን የገዛውን አንድ ነገር እዚህ ልጠቁም፡፤ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ ሀገራቸው ልትጠቃ የምትችልባቸውን አራት የደኅንነት ሥጋቶች በመጠቆም የአሜሪካንን ዕርዳታ ተማጥነው ነበር አሉ፡፡ እነዚያ እንደትንቢት የተነገሩ ሥጋቶችም 1ኛ፣ የሶማሊያ ወረራ 2ኛ፣ የሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስታዊ መንግሥት ዐይኖቹን ወደ ኢትዮጵያ ማማተርና ሀገሪቱን በኮሚኒዝም ፍልስፍና ማጥመቅ 3ኛ፣ የኤርትራ መገንጠል 4ኛ፣ በኢትዮጵያ የእስልምና ሃይማኖት መስፋፋትና እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት የዐረብ ሀገራት የጠነሰሱት ሤራ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን የሚያወሱ ነበሩ፡፡ የአሜሪካን መንግሥት ግን እነዚህን የንጉሡን የሥጋት አቅጣጫዎችና የዕርዳታ ጥያቄ በማናናቅ አሽበልብለው ሸኟቸው፡፡ ይሁንና ‹ቂጣም ከሆነ ይጠፋል፤ ሽልም ከሆነ ይገፋል› እንዲሉ እንደኤሊያስ አነጋገርና እንደ ታዘብነውም በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ሥጋቶች በግልጽ ታዩ፡፡ ሶማሊያም ወረረችን፤ ዕድሜ ለነመንግሥቱ ኃ/ማርያምና ለአሜሪካን ዳተኝነት ራሺያም ደረቋን ሶማሊያን ትታ እርጥቧን ኢትዮጵያን ያዘችና በድርቅ መታቻት፣ አሁንም ዕድሜ ለነመንግሥቱና ለሻዕቢያ-ወያኔ ኤርትራም ተገነጠለች፡፡ የሆነው ሁሉ ሆኖ ኢትዮጵያ ጨረቃ ላይ ቀረች፡፡
ኤልያስ ሸፋፍኖት ያለፈው አልተፈጸመም የተባለው ንግርት ግን በከፊል እየተፈጸመ እንደሆነ አንዳንዶች ይስማማሉ፡፡ ብዙ መጨነቅ አያስፈልግም ውድ ወገኖች! (ራሴው ተጨነቅሁ ልበል?)፡፡ በጣም ኢምንት የሆነች የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ወስደን ማየት እንችላለን፡፡ ሳዑዲ ዐረቢያ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን መሥራት ቀርቶ ከእስልምና ውጪ ሌላ ሃይማኖት የመከተል መብት የተረገጠ ነው፡፡ እንዲያውም የሃይማኖት ዲኑ (ዋናው ሼህ) በቅርቡ ባስተላለፉት ዐዋጅ ክርስቲያኖችንና አይሁዶችን እንዲሁም የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችን ከነቤተ አምልኮቶቻቸው ከዐረቡ ዓለም ማጥፋት እንደሚገባ በጥብቅ አሳስበዋል – ‹ በእስልምና ሃይማኖት ተቻችሎ መኖር የዕርም ያህል ነው እንዴ?› እስኪባሉና ዓለም ቀርቶ የገዛ ንጉሣቸው ቅሬታ እስኪያድርበት ድረስ በሃይማኖታዊ ሆደባሻነታቸው ይህን ያህል ርቀው ሄደዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ይህች ሀገር በኢትዮጵያ ስንትና ስንት መስጂዶችን እንዳሠራችና እያሠራች እንደሆነ ሕዝበ ሙስሊምንም ለማበራከት በብዙ ሰደቃ ድሃን እንደምታማልል ያጡ የነጡ ዜጎችን በነዳጅ ገቢዋ እየረዘቀች ከነባር የሃይማኖት ጎዳናቸው እንደምታናጥብ፣ መምሬ ገብረማርያም ሳይቀር ጥምጣሙን እያሽቀነጠረ ሃጂ አብደላ እንደሚሆን … እናውቃለን፤ ይሁን ይህም ለበጎ ነው፤ የሚያዋጣውን የሚያውቅም ባለቤቱ ብቻ ነው – ሲያሻው ጳጳሱም ኢማም ይሁን፤ ምርጫውን ማከበር ይገባል እንጂ በለምን ተለወጥክ አላስፈላጊ አታካራ ውስጥ መግባት ቀኖናዊም ፍትሃዊም አይደለም፡፡ በመሠረቱ ሁኔታው ከሌላ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት ከሌለው በስተቀር ገንዘብና ቁርዓን መቀበልም ሆነ መስጠት ወንጀል አይደለም እንጂ በቅርቡ ከሳዑዲ ኤምባሲ ገንዘብና መጻሕፍት ይዘው ሲወጡ የተያዙ ዜጎች እንዳሉ ሰምተናል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመላው ከማስለምና ሀገሪቱን እስላማዊ መንግሥት ለማድረግ ከሚደረግ ግልጽና ሕቡዕ እንቅስቃሴ አኳያ የዚህ ጽሑፍ አቀናባሪ ሌላም ከዚህ የበለጡ የውጭ ተፅዕኖዎችን እንደሚያውቅ ማስገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ይሁንና እንኳን ከፎከረ ከወረወረም የሚያድን የሁሉም ሃይማኖቶች ራስ ሊሆን የተገባው – በየቋንቋችን እንዳመቸን የምንጠራው አንድ ፈጣሪ አለና ሀገራችንን ከአራተኛው ትንቢት እንደሚታደጋት ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ የአራተኛው ትንቢት ችግሩ ሃይማኖቱ ሳይሆን አልቃኢዳን፣ ታሊባንንና አልሻባብን በመሰሉ አክራሪ የሚባሉ ወገኖች ዘንድ በአሁኑ ወቅት የሚቀነቀነውና በአንዳንድ የሙስሊሙ ዓለም ውስጥም ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሳይቀር ባዕድ የሆነ የግል ነጻነትን የሚገድብ ሕግ በሁሉም እምነት ተከታይ በግዳጅ መጣላቸውን በማሰብ እንደሆነ ልብ ማለት ይገባል፡፡ ለምሳሌ በታሊባኖች አመራር ሴት ልጅ ቁርዓን ከመቅራት በዘለለ ዘመናዊ ትምህርት አትማርም፤ ከትዳር ውጪ ወሲብ ብትፈጽም በድንጋይ ተወግራ ትሞታለች፤ሃይማት መለወት በሠይፍ አንገትን ያስቆርጣል፣…. ይህን በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ሕግ ብናደርገው አዲዮስ ቺቺንያ! አዲዮስ ካዛንቺስና ሃያ ሁለት ማዞሪያ፣አዲዮስ ሥላሤ ካቴድራል፣ አዲዮስ አክሱም ጽዮን ወላሊበላ፣…፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ከነዚህ አንጻር እንጂ ሙስሊም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፕሬዚደንት አይሁን አይደለም፡፡ አስፈላጊ ከሆነና የሁሉም ሕዝብ ነጻ ምርጫ ከሆነ ፓርላማውን መቶ በመቶ ሙስሊም ይያዘው – ነገር ግን የሁሉንም እምነትና ባህል የሚያከብርና ነጻነትን በሃይማኖት ሽፋን የማይሸራርፍ ይሁን፡፡ ከዚህ የበለጠ ወይ ያነሰ ፍላጎትም ሆነ የተደበቀ አጀንዳ የለኝም፡፡ ወደሌላ ነገር የሚያንሻፍፍ ሰው ቢኖር ጌታ ይገስጸው፡፡ [ያቤቶክቻው የቅንፍ ጨዋታ ደስ ትለኛለች፡፡ አንድ የዚታ ሹፌር በጎጃም መስመር ሲነዳ መንገዱን አልለቅለት ብላ ላስቸገረችው አንዷ ሴት ‹ከአንቺስ አህያይቷ ትሻላለች› ይላታል አሉ፡፡ እሷም የዋዛ አልነበረችምና ‹የሚጥምሁን የሚያውቁት እርስዎው ነዎት!› አለችውና ባላፊ አግዳሚው አሳቀችበት ይባላል፡፡ ግዴላችሁም አሁን ባይኖራችሁ ከወደፊተኛው ዘመን ተበድራችሁም ቢሆን ጥቂት ፈገግ በሉ - ፈገግታ የሕይወት አንደኛው ቅመም ነውና፡፡]
እዚህ ላይ ሳልጠቅስ ማለፍ የማልወደው ነገር አለኝ፤ ምንም እንኳን ክርስትናና ከዚያም የቀደመው የጣዖታት አምልኮና ከነአካቴውም ሃይማኖት የለሽነት ቀዳሚነት ቢኖራቸውም ኢትዮጵያ የሁሉም ሃይማቶኖች ሀገር መሆኗ የሚካድ አይደለም፡፡ ባለፉ ዘመናት ስህተቶች ተሠርተው ሊሆን ይችላል – አልተሠሩምም አይባልም፡፡ ነገር ግን እነዚያን በማረም መንግሥትንና ሀገርን ለጋራ፣ እምነትንና ባህልን ለግል በማድረግ በሰላም መኖር ይገባናል እንጂ በውጪ ጣልቃ ገብነት የአብሮነታችንን ገመዶች ሊበጣጥሱ የሚችሉ መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ማናችንም ብንሆን ማድረግ አይገባንም፡፡ ክፉ መንግሥት ያልፋል፤ ክፉ ማኅበረሰብኣዊ ቁስል ግን መዳኑ ባይቅርም እንኳን የሚተወው ጠባሳ በቀላሉ የሚረሣ አይሆንምና በዘመንኛ ንፋስ እየተወሰዱ ወገን በወገን ላይ ጉዳት ላለማድረስ መጠንቀቅ ከብልህ ዜጋ ይጠበቃል፡፡ በተረቱ ‹አገባሻለሁ ያለ ላያገባሽ፣ ከባልሽ ሆድ አትባባሻ› ይባላልና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠቅመው የቀድሞው ጨዋነቱና ሀገራዊ የሃይማትኖና የባህል ትውፊቱ ነውና ከየትኛውም አቅጣጫ በሚሰነዘር ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ሳይናወጥ ተከባብሮ መኖር ለሁሉም ይበጃል፤ በጥፋት መንገድ መጓዝ የሚጎዳው ብዙዎችን ነው፤ የሚጠቅመው ግን የጫሩት እሳት የማይነካቸውን በሞቀ ቤታቸው እዬኖሩ የጥፋት ሠራዊታቸውን ጃዝ ብለው የሚያሠማሩ እጅግ ጥቂቶችን ነው፡፡ በየትኛውም የሃይማኖት መስመር ይሁን ከጤናማ መንገድ የወጣ ማናቸውም ዘመን አመጣሽ እምቡር እምቡር ማንንም አይጠቅምም – የሚያከርር ሁሉ የሚያከርረው የነገር ሲባጎ ከርሮ ከርሮ ሲያበቃ ራሱን ነው የሚያንቀው – በቆፈሩት ጉድጓድ መግባት የቀደመ እንጂ የዛሬ ዘመን ፍልስፍና አይደለም፡፡ የሚድነውን የሚያውቅ እንደሆነ አንድ ፈጣሪ ብቻ ነው፤ ሰው ማድረግ ያለበት ያዋጣኛል ብሎ የሚያምንበትን ሃይማኖት ካለማንም ተፅዕኖ በመከተል የሌሎችን ምርጫ ግን በማክበር በሰላምና በፍቅር መኖር ነው፡፡ ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ዓይነቱ አካሄድ በየትኛውም መሥፈርት የማያዋጣና ለከፍተኛ ሥጋዊና መንፈሳዊ ኪሣራ የሚዳርግ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህን መሰሉን የሽብርና የትርምስ ዐዋጅ የሚያራግቡ መንግሥታዊም ይሁኑ ተቋማዊ ቡድኖችንና ግለሰቦችን ሤራ በማጋለጥ ሕዝቡ ለጋራ ኑባሬው መትጋት እንዳለበት ማሳሰብ ማንቃትም ይገባል፡፡ በጣም ባጭሩ የነፍስ ድኅነት የሚገኘው ሃይማኖትን በማጦዝና ሌሎችን መቆሚያ መቀመጫ በማሳጣት ሳይሆን በተረጋጋ መንፈስ አቅላችንን በማቶበት፣ቀልባችንን በመሰብሰብ፣ ውስጠ ውሳጤንም በአርምሞ በመመርመር ከማንኛውም የክፋት መንገድ ርቆ የፈጣሪን ረድኤት በመሻት ብቻ ነው፡፡ በቃ፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ቱማታና የጨረባ ተዝካር ዓይነት አካሄድ የሌቦችና የአጭበርባሪ እረኞች ሥራ ነው፡፡ እነሱም ያውቁታል፡፡ ስለሚጠቅማቸው ግን ይከተሉታል፡፡ እኛ ግን ወደየኅሊናችን እንመለስ – ብዙም ሳይመሽ ታዲያ፡፡
ወደኤሊያስ ልመለስ፡፡ በጀመረው ሂደት ችግሮች እንደሚያጋጥሙት ሳይታለም የተፈታ እንደመሆኑ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እየተደቀኑበት ባሉ ችግሮች እኔም በበኩሌ አዝኛለሁ፡፡ ከችግሮቹ መካከል የኛ የኢትዮጵያውን የጭፍን ጉዞና ‹እነሱ›ና እኛ በሚል ጎራ የመለያየታችን አባዜ ያመጣው የቅድመ አእምሮ ፍረጃና ፍርደ ገምድልነት (bias and prejudice)መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ‹የነሱን ካሣተምህ የኛ አይደለህም› እና ‹የኛን ካሣተምህ የነሱ ልትሆን አትችልምና እነሱን ጠልተህ ተዋቸው› ዓይነቱ የደናቁርት አስተሳሰብ እጅግ እንዳወከው ኤልያስ ገልጾኣል፤ ትክክልም ነው – እኛ እንደጨጓራ ሲያጥቡን የማንጠራ የዘመናት ጭቅቅት በላያችን ተከምሮ እያየን በዚያ የማንማርና የማንሻሻል አድሮ ቃሪያዎች በመሆናችን እኛ ንቁዎች በነበርንበት የጥንት ዘመን እንቅልፋም የነበሩ የዓለም ዜጎች የትና የት በደረሱበት በ21ኛው መቶ ክፍል ዘመን ላይም ተቀምጠን እንደዘመነ መሣፍንት በጎጥና በሸንተረር በሃይማኖትና በደም ‹ጥራት› ውሾችን ይመስል በአልባሌ ነገር የምንናከስ በዚያምና በሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች የተነሣ መቅኖ አጥተን ተበታትነን የቀረን ምንዱባን የመሆናችን መንስዔ የዚሁ ጠማማ ተፈጥሯችን መዘዝ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት በቡድንና በጎራ እየተለያዩ የመነታረክ አባዜ ከቀጠለ ገና የምናየው መከራ ተዝቆ የሚያልቅ አይሆንም፡፡ ፈጣሪ ይጠብቀን እንጂ ተሰግስገውብን ያሉ መዥገሮችና ሞጀሌዎች እንደእስካሁኑ በግልጥና በሥውር የከይሲ ሥራቸውን ከቀጠሉ ብዙ የምንከፍለው ዕዳ አለብን፡፡ በመሠረቱ የጠብ ደቦ የለውም፤ ‹የጠላሁትን ጥላ› ብሎ ትዕዛዝም የለም፤ ባይሆን ‹የሚጠላህን ውደደው› የሚል እንጂ፡፡ የምን መዓት ነው የወረደብን? ነፍስ ያወቀ ሰው እንዴት የምጠላውን ተደርበህ ጥላልኝ ይላል? በምናቧ እናግባሸ እናግባሽ ለሚሏት ጎረምሶች መልስ እንዲሆናት ‹መኖር አይችሉም ወይ የማንም ሳይሆኑ› ብላ ያቀነቀነችው ማን ነበረች?
ኤሊያስ እንደገለጸው ይህን መጽሐፍ አንድ ሃባ ገዝቶ እስካን በማድረግ በኢንተርኔት መልቀቅ ለምሳሌ ከተራ ምቀኝነት በስተቀር ሌላ ፍቺ ሊሰጠው አይችልም – በነገራችን ላይ እኔም ያለኝ መጽሐፍ እሱው ነው – ቆይ፣ ለፍርድ አትቸኩል ታዲያ፡፡ በበጎ አድራጎት ራሮት እንዳላገኘሁት አውቃለሁ፡፡ ሰው ነው በሶፍት ኮፒ የሰጠኝ፤ ምሥጢሩንም በወቅቱ ሰምቻለሁ፤ መቀበል እንዳልነበረብኝ ይገባኛል፡፡ ነገር ግን የመግዛት አቅምና ፍላጎትም አልነበረኝምና ለወረት ያህል ጓደኞች ወስደህ እየው ሲሉኝ ወሰድኩ – በዚህ አጋጣሚ ንስሃየን ላውርድ፡፡ ወደፊት ግን የአንድ መጽሐፍ ዋጋ -ጊዜው ሲደርስ- ለሚገባው አካል ለመክፈል ቃል እገባለሁ፤ ይህ ገንዘብ አንጀት የሚያርስ ሆኖ ሳይሆን የማተብ ጉዳይና የንስሐ ጣጣ ያለበት በመሆኑ ነው አሁን በድረገፅ ፊት የምናዘዝ፡፡
ያን ሥራ የሠሩትና ተሳስተው ያሳሳቱን ሰዎች ግን ከዚህ መጥፎ ድርጊታቸው ሊታቀቡ በእውነት ተጸጽተውም ከተመሳሳይ የዕቡያን ተግባር ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ አይጠቀሙበትም፡፡ እንደተባለው ተቃውሞኣቸውን በጽሑፍና በሌሎች መንገዶች ቢገልጹ እነሱም ከትዝብት እኛም ከወንጀልና ከኅሊና ፀፀት አሣታሚውም ከኪሣራ ልንድን በቻልን ነበር፡፡ አንድ ጥፋት መዘዙና የሚያነካካው ሰው ብዛት ብዙ ነውና ሁላችን ጥፋተኞች ነን – በአንድ ወይ በሌላ መንገድ፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር መጸጸትና ጥፋትን ላለመድገም መቁረጥ ወደትክክለኛ ሰውነት ይመልሳል – በውነቱ መሳሳት ሰውኛ በመሆኑ ብዙ አያስደንቅም፡፡ ችግሩ የስህተትን መንገድ ይሁነኝ ብሎ ሙጭጭ ማለትና እስከመጨረሻው በዚያ ለመጽናት ፈቃደኛ ሆኖ ቆርበውበት መገኘት ነው፡፡
ወደዋናው ጉዳይ ልግባና ስለነዚህ ዓይነት መጻሕፍት የሚሰማኝን ልበል፡፡ የአንባቢያንን ጊዜና ትኩረት ላለመሻማት ባላስረዝም ደስ ባለኝ፡፡
በሰዎች ላይ የተደረገ የባሕርይ ጥናት ስለሰዎች ባሕርያት ከዕድሜና ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የሚታየውን መለዋወጥ እንዴት እንደሚገልጸው ብዙም አላውቅም፡፡ አንድ መሠረታዊ እውነት ግን አለ፡፡ ያም ሰዎች በዕድሜና በሁኔታዎች መለዋወጥ ምክንያት ትናንት ከሚያደርጉት ነገር በተወሰነ ደረጃ ወይም ሙሉ በሙሉ በኋለኛው ዕድሜያቸው እንደሚቆጠቡ ወይም ትናንት የማያደርጉትን ነገር ዛሬ እንደሚያደርጉ ከልምድ መማር እንችላለን፡፡ ለምሳሌ በሃያዎቹ ያለ ወጣት በአብዛኛው ወደምሽት ክበቦችና ወደኮረዳዎች መንደር ለመሄድ ሲመኝ በስልሳዎቹና በሰባዎቹ የሚገኝ ሰው ወደአምልኮ ቤቶችና ወደቤተ መጻሕፍት ለመሄድ እንደሚሻ -ቢያንስ በንድፈ ሃሳብ ደረጃና በመሠረቱ- የሁላችን ግንዛቤ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን አጠቃላይ ቅኝት የሚጥሱ ከታችኛውም ከላይኛውም ሠፈር አይታጡም ማለት ግን አይደለም – በተለይ በዚህኛውና አሁን ባለንበት የጠፎች ዘመን በ80 ዓመት ዕድሜው ምንጅላቷ ከሚሆናት በማለዳማው የአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከምትገኝ ታዳጊ ሕጻን ጋር በየዳንስ ቤቱ ሲልከሰከስ የሚገኝ የእንጨት ሽበት ቢያጋጥም የስምንተኛውን ሺህ ፍካሬ ኢየሱስ በማስታወስ አፍን መተምተም እንጂ ለክስ የሚሆን ቦታና ዳኛ እንደሌለን የታወቀ ነው፡፡ዝርዝሩ ጥልቅ ነው፡፡ ተከድኖ ይብሰል ማለቱ ይቀላል፡፡…
ባጭሩ ኮሎኔል መንግሥቱ ተለውጠዋል ወይ ነው ጥያቄው፡፡ መጽሐፋቸውን ለማንበብ በቅድሚያ ሰውዬው መለወጥ አለባቸው – ለውጣቸውን ደግሞ ከመጽሐፉ ርዕስ ጀምሮ ልናይ በተገባን – ‹ትግላችን› ከሚለው፡፡(የመጽሐፍ ትችት ለማቅረብ አለመድፈሬን ማስታወስ እፈልጋለሁ፤ ጨርሼ አላነበብኩትምም፣ ሳነበውና ባነበውም ለመተቸት አቅምም ድፍረትም ዕውቀትም የለኝም፡፡) እናም የዛሬው መንግሥቱ ከያኔው መንግሥቱ ጋር ተካካይ ከሆኑ መንግሥቱን በጉጉት የምንጠብቅበት አዲስ ነገር አይኖርምና በብሂሉ ‹ዋጮን ቢገለብጡት ያው ዋጮ ነው› እንደሚሉት ነው፡፡ ለውጥ ቀላል አይደለም – በተለይ ማራኪ ለውጥ፡፡ ለለውጥ ራስን መካድ ሁሉ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ አዲስ ስብዕናን መላበስ የሚቻለው አሮጌውን በመፀየፍ ጭምርም ነው፡፡ ሥራቸውን ግን በደርጉና በአብዮቱ ስምም ያውጡት በራሳቸውም ስም ይጻፉት መቀበሉና ለታሪክ መዝገብና ፍርድ ማስቀመጡ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይዘቱ ግን ሊመረመርና ሊተች ይገባዋል፡፡ ብዙ አባባሎች አሉ – ‹መጽሐፍ በሽፋኑ አይፈረድም›፤ ‹የሚያብለጨልጭ ሁሉ ወርቅ አይደለም›… እናም መጽሐፋቸውን በድፍኑ ከመጥላትና ወደቅርጫት ከመወርወር አንብበን ወይም በመጽሐፉ ላይ የተዘጋጁ ሂሶችን ተመልክተን ስለመጽሐፉ የሚሰማንን ስሜት ብንሰጥ የተሻለ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ በሰውዬው የኋላ ዳራ ላይ ብቻ ተመሥርተን የምንፈርድና ‹የዚህን ሰውዬ መጽሐፍ በሩቅ፤ ወደዚያ አቃጥሉልኝ!› የምንል ከሆነ በለውጥ የምናምን አይደለንም ማለት ነው – እንደአካሄድ፡፡ ይህን የምለው በተለያየ ምክንያት በጭፍኑ ‹ከመንግሥቱ ምንም ነገር አይጠበቅም› ለሚሉ ወገኖች ነው – እንደኔ እንኳ በጨረፍታም ሳያነብቡ፡፡ ‹ሳያነቡ› እንዳልል የቃሉ መንታ ትርጉም አስጨንቆኝ ነው፡፡ በርሳቸው ዘመን ያላነባ ማን አለና?
እንደኔ እንደኔ ግን አለፍ አለፍ ብዬ መጽሐፉን እንደተመለከትኩት በቅርቡም ከዶክተር ካሣ ከበደ ጋር ኢሣት ባደረገው ቃለ መጠይቅ እንደተከታተልኩት በማከያውም ከሌሎች ምንጮች እንደተረዳሁት ሰውዬው የተለወጡ አይመስሉኝም ወይም ለመለወጣቸው በቂ ዕውቀት እንድንጨብጥ ያደረጉ አይመስለኝም፡፡ እሳቸውን ልሆን አይቻለኝም እንጂ ብሆን ኖሮ ይህን መጽሐፍ እንደዚህ ብዬ እጀምር ነበር፡- (መመኘት ነውርና ኃጢኣት የሚሆነው ምኞትን ለማሳካት በሚደረግ ጥረት የሚታይ የሥልት ልዩነት እንጂ መመኘት በራሱ መጥፎ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡)
ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ!
ዕድሜ አሰተማሪ ነው፤ የችግር ውጣ ውረድም አስተማሪ ነው፡፡ ይሆናል ብለን በጀመርነው አብዮት በመካሪ ዕጦትና በትኩስ የአፍላነት ዕድሜ ተወናብደን በሀገርና በሕዝብ ላይ ታላቅ ጥፋት አስከትለናል፡፡ ይህ ሁለንተናዊ ጥፋት በፖለቲካውም፣በሃይማኖቱም፣ በባህሉም በሁሉም ዘርፍ ያልታዬ ማለትም የተከሰተ ነበር፡፡ መስሎን ባደረግነው ነገር የተፈጠረው ስህተት ሀገሪቱንና ሕዝቧን ወደማይወጡት ችግር ዳርጓል፡፡ በኢሕአፓና በተለያዩ የክፍፍል ወቅቶች ሀገርን ሊገነቡ የሚችሉ ብዙ ወጣቶችን ጨረስን – አስጨረስን፤ ከየጎራው በሚተኮሱ ጥይቶች እኛው በኛው ተላለቅን፡፡ የሀገርን ድንበር ለማስከበር ብዙ እንዳልለፋን ያህል ዴሞክራሲን ለማስፈን ምንም ጥረት አላደረግንም ብል አልተሳሳትኩም፤ ይልቁንም የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት ነግሦ ሀገርና ሕዝብ ተረሱና በሕዝቡና በጦሩ ማኩረፍ የተነሣ መንገዶች ሁሉ ለወያኔው አፍራሽ ተልእኮ ምቹ ሆኑ፡፡ ያሳዝናል!
ውድ ጓዶች!
አባቶቼ፣እናቶቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ!
ይህን በዋናነት በኔ አመራር በሀገር ላይ የወረደውን መቅሰፍትና ዕልቂት አሁን ዘወር ብዬ ሳስበው እንደእግር እሳት ይፈጀኛል፤ ሳስታውሰውም ይዘገንነኛል፡፡ በይቅርታ ብቻም የሚታለፍ እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ነገር ግን ሌላ ምን የሚያዛልቅ ምርጫ አለኝ? ያ ሁሉ የተፈጀ ወጣትና የጠፋ ጥፋት በኔ መሞት ቢመለስ ቅንጣት ባላቅማማሁ፡፡ ከዚያ ይልቅስ ሀገርንና ሕዝብን ይቅርታ ለመጠየቅና ቢቻለኝ ደግሞ ለመካስ የምችልበትን አጋጣሚ ከማሰብ ቦዝኜ እንደማላውቅ በትህትና ልገልጥላችሁ እወዳለሁ፤ ይህን መሰል ዕድል የሚያገኙ አምባገነን መሪዎች እጅግ በጣም ጥቂት መሆናቸውንም አውቃለሁ፡፡ የሥልጣን ነገር አሳሳች ነውና የውጪ ጋዜጠኞች ሰው ገድዬ እንደማውቅና እንደማላውቅ በጠየቁኝ ጊዜ ‹እንኳን ሰው ትንኝ አልገደልኩም› ለማለት የተገደድኩትና ትልቅ ውሸት የዋሸሁት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኔ ላይ ያለውን አመለካከት ለማለዘብ እንጂ እኔ ሳላውቀውና ሳልፈቅድ የሚገደል ዜጋ ከስንት አንድ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የ12ቱ ጄኔራሎች ሞት ለምሳሌ በኔ ቀጥተኛ የፍርድ ተጽዕኖና ጣልቃ ገብነት ነው የተከናወነው – ምሕረት እንዳደርግላቸው ብዙዎች ተማፅነውኝ የነበረ ቢሆንም በእልህ ተነሳስቼ ሞት እንዲበየንባቸው ግፊት አድርጌያለሁ – ቤተሰባቸውና ልጆቻቸው ይቅር ይበሉኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሀገሪቷ በስንትና ስንት ወጪ ያሰለጠነቻቸውን የጦር መኮንኖች የኔን የአንድ ግለሰብ ሥልጣን በመቀናቀናቸውና ለውጥን በመፈለጋው ብቻ እንድታጣ በማድረጌ ጸጸቱ አሁን ድረስ እያገረሸ መቆሚያ መቀመጫ አሳጥቶኛል፡፡ይህም ጥፋቴ ከይቅርታ በላይ መሆኑን እረዳለሁ፡፡ አሁን የፈሰሰ አይታፈስምና ይህን ሀገራችንን እንደገና ዳቦና እንደቡና ቁርስ በማቃረጫ ጀንዲ ላይ መድቦ ለባዕዳን ሀገራትና ለወራሪ ኢንቬስተር ተብዬዎች ባገኘው ዋጋ እየቸረቸረብን የሚገኘውንና በዓለም ፊት ያዋረደንን የወያኔ መንጋ ተባብረን እናስወግድ፡፡ ነጻነታችንን ካረጋገጥን በኋላ የፈለጋችሁትን ብያኔ ታሳልፉብኛላችሁና ቅድሚያውን የኔ መንግሥት ላጠፋቸው ጥፋቶች ሰጥተን ወያኔን በቻልነው መንገድ ሁሉ በውጪም በውስጥም ቆርጠን እንድንታገል ወገናዊ ጥሪየም አስተላልፋለሁ፡፡…
እንደዚህ ዓይነት ወይም ወደዚህ የቀረበ የጸጸትና የይቅርታ ተማጥኖ በመጽሐፉ ውስጥ በአንደኛው ገጽ እንኳን ቢካተት ኖሮ ለብዙ ሰዎች ልብ መራራት መልካም በሆነ ነበር፡፡ አለበለዚያ የ32 ዓመቱ ጎረምሳው መንግሥቱ በለዘበ ቋንቋ በ70 ዓመታቸው ቢመጡ ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ ከመሆን አይዘልም፡፡ አሁንም ቢሆን እያልኩ ያለሁት አይጻፉ ሳይሆን ይጻፉ ግን ማንበብ የሚፈልግ ያንብብ ማንበብ የማይፈልግ ይተወው፤ ከጻፉ ደግሞ የነበረውን በመድገም የተሠራውን ስህተት ጽድቅና ለማሰጠት ሳይሆን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመንቀስ በተለይ የአሁኑና መጪዎቹ ትውልዶች ሊማሩበት የሚችል ተጨባጭ ታሪክ ቢጽፉ ይበልጥ ይወደሱበታል ባይ ነኝ፡፡ ምን እንደነካኝ እንጃ ውሸትና ከልደት እስከሞት ዓይነት ሁልአቀፍ ዝባዝንኬ ትረካ ሰለቸኝ፤ ለጤና ያድርግልህ በሉኝ ኧረ!
ጨው ድንጋይ ቢሆን ይጣላል እንደሚባል የሚጻፍ ነገር ከፍ ሲል እንዳልኩት መስዋዕትነትን ይጠይቃል – ስብዕናን እስከሚነካ ድረስ፡፡ የሚጻፈው እውነት ከሆነ ሰው ይቀበላል – ካልሆነ ዐዋጅም ውግዘትም የሰውነት ደረጃን ዝቅ በሚያደርግ መልኩ ጽሑፍን በማሽን እስካን አድርጎ መበተንም ሳያስፈልግ በሽቅጦ ይቀራል – በራሱ ሂደት፤ ይህን ደግሞ እንወቅ – አታንብብ ማለት አንብብ ማለት ነው፤መከልከል መፍቀድ ነው፤ ማራቅም ማቅረብ ነው፤ መጥላት የመውደድ ምልክት ነው – መውደድም የመጥላት፡- እነአዳም ፍሬዋን ተከለከሉ፤ ሲከለከሉ ለመብላት ጓጉ፤በሉና የሆነው ሁሉ ሆነ – ጦሱም በነመለስ በኩል እኛው ጋ ደረሰ፤ መለስ የአሳሳቹ የእባቡ ዝርያ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ያቺ ፍሬ ግን ከሌሎች አትለይም ነበር አሉ፡፡ አንዷ ጥንቁቅ ሴት እንትኗ ድምፅ እንዳታወጣባት ፈልጋ ስትታገል ቆየችና ሳይሳካላት ሲቀር ‹ውይ! መንግጌ አባስኳት› ያለቸው ወድዳ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሚጽፍ ይጻፍ – ይነበብ፡፡ አንባቢም ይፍረድለት፡፡ ስለአንባቢ ‹መጨነቅ› አንባቢን መናቅ ይመስለኛል፡፡
በመሠረቱ ውሸት የሚበረታበት ሰው መጽሐፍ ቀርቶ ተራ ደብዳቤም መጻፍ አይችልም – ባለአድራሻው አንዱ ሰው ራሱ ሊያነብለት አይችልም፡፡ መግደልን ከባህል የሚቆጥር ሰው ስላለመግደል በጎነት የሚናገረው ነገር ብዙም አይኖርም፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን በየትኛውም ምክንያት ቢሆን መግደል ስህተት ነው፡፡ የገደለ ሰው ተሳሳተ፤ የገደለን ሰው የሚገድልም ተሳሳተ፡፡ ግድያ በግድያ አይቃናም፡፡ ስህተት በስህተት አይታረቅም፡፡ የሞተን ሰው መወንጀልም ራሱ ወንጀል ነው፡፡ ‹ጥፋተኞች ስለነበሩ ተገደሉ› የሚል ነገርም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ስህተትን ማመን ደግሞ ለእውነተኛ ለውጥ በር ከፋች ነው፡፡ የሞት ፍርድ በቀረባቸው ሠለጠኑ በሚባሉ ሀገሮች ውስጥ የገደለንም ሆነ ያጠፋን ይዞ ለሕግ በማቅረብ እንዲታረምና ወደሕዝብ እንዲመለስ ወይም እንደጥፋቱ ደረጃ ወደማኅበረሰቡ ቢቀላቀል አያርመውምና ሌላ ጥፋት ስለሚያስከትል እስከወዲያኛው ተገልሎ ይኑር በሚል የዕድሜ ይፍታህ ሕግ ያቆሙት ለዚህ ነው፡፡
የኮ/ል መንግሥቱን ጉዳይ የምመለከተው በላይኛው አንቀጽ አንጻር ነው፡፡ በመጽሐፋቸው ውስጥ አብዮቱን እያንቆላጰሱ ያቀረቡ ይመስለኛል፡፡ ያ አብዮት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በርግጥም አብዮቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነበር? ሊያነጋግረን የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ነው፤ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ አይደለም፡፡ ለነገሩ በዚያ ጉዳይ እኔን ምን ጥልቅ አደረገኝና ነው አይደለም ብዬ እፈተፍታለሁ? ግን ግን የሕዝቡ አብዮት ቢሆን ኖሮ ቢስ እንዳያይብን እቅፍ ድግፍ አድርገን እንይዘው ነበር፤ በወቅቱ ልናውቀው ላልፈለግነው ከደርጉ ለባሰ የሀገር ጠላት አሳልፈን አንሰጠውም ነበር፤ ያ ሁሉ ትውልድ አያልቅብንም ነበር፤… የሚል የልዩነት ሃሳብ አለኝ – በበኩሌ፡፡ በሥልጣን መፈነቃቀልና ሥልጣንን በማጠናከር ሂደት የተሞላ የጥቂት አንበሣዎች የእርስ በርስ ፍልሚያና በመጨረሻው አንዱ ጥቁር አንበሣ ወንበሩን ለብቻ ተቆጣጥሮ በጠላትነትና በሥልጣን ባላንጣነት የሚፈርጃቸውን ዜጎች ለማጥፋት ደኅንነቱንና የፀጥታ መዋቅሮችን – ልክ እንደአሁኑ- ለብቻ የተቆጣጠረበት ሁኔታ ታዝቤያለሁ፤ ያ የሕዝብ አብዮት ከተባለ እስማማለሁ፡፡ ስለዚህ የዚህን መጽሐፍ ይዘት በቅጡ መፈተሸ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ውድቀት ሲመጣ ‹የሕዝብ አብዮት› በሥኬት ዘመን ደግሞ ‹ከእገሌ ቆራጥ አመራር ጋር ወደፊት› ማለቱ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ለመታረም ዝግጁ ነኝ፡፡
እቅጩን ልናገር፡፡ አምባገነኖች ወደ ኅሊናቸው የሚመለሱበት ጊዜ ብዙውን ጊዜ አይስተዋልም፡፡ ጥፋትን ወደሌሎች በማላከክ ልማትን ብቻ ወደራሳቸው በመሳብ በዘመናቸው የተሠሩ እንከኖችን ሊደብቁ ይሞክራሉ፤ ማስረጃ የለኝም – ግምት ነው፡፡ ሂትለርና ቢስማርክ፣ አጼ ቦካሳና ዚያድባሬ፣ ኢዲያሚንና ቻውቼስኮ፣ ሙሶሎኒና ስታሊን ሥልጣን ለቅቀው መጽሐፍ ጽፈው ከሆነ አላነበብኩም፡፡ ግን ግን የአምባገነኖች ባሕርይ አንድና አንድ መሆኑን ከሰዎች አባባል ስለተረዳሁ ከኮ/ል መንግሥቱ የምጠብቀው ብዙም ነገር የለም፤ እንዴ፣ እንደዚህ ግን ይባላል እንዴ? ላሻሽለው መሰለኝ፤ የሌሎችን አባባል ልዋስና ‹ኮሌኔሉ በቀሪ መጽሐፎቻቸው አንጀቴን የሚያርስ ቃለ-ኑዛዜ ወንስሃ የሚያስነብቡን ከሆነ ሁላችንንም ዕድሜ ይስጠንና በጊዜው ልል የምችለውን እላለሁ፡፡ በዚህ ተፈጥሮየ ግን አዝናለሁ – መጽሐፉ ውስጥ ጥሩ ነገር ቢኖራቸውም ያልፈኛል ማለት ነው – ለማንኛውም አንብቤ ልጨርሰው፡፡
እነዚህ ሰዎች – አምባገነን የሚባሉቱ – ሲፀነሱ ወይም ሲወለዱ በሰማይ የሚኖረው ኮከባቸው የተለዬ ተፅዕኖ የሚያሳድርባቸው ይመስለኛል፤ ከልደት እስከሞታቸው የተስተካከለ ወጥ ባሕርይ የሚኖራቸው እንደሚሆንም አምናለሁ፡፡ ከአምባገነን ወንበር ወርዶ አንድም ወደሞትና መቃብር አሊያም ወደስደትና ወደእሥራት እንጂ ወደገዳምና ወደሱባኤ የገባ የዓለም ፈላጭ ቆራጭ መሪ አላስተዋልኩም፡፡ ነገረ ሥራየ ያሳዝናል – ምን ለማለት እንደፈለግሁ ለራሴ እንኳን ሳይገባኝ ጽሑፌን ላጠናቅቅ ደረስኩ፡፡ ኤዲያ! ይሄ የብሶት ጎተራ ተቆንጥሮለት አያልቅ፤ በቃኝ፡፡
No comments:
Post a Comment