No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Friday 30 November 2012

የእስላም ኢትዮጵያውያን የትግል ስልት ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም

በአለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ እስላም ኢትዮጵያውያን ማካሄድ የጀመሩት ትግል በዓይነቱም፣ በስፋቱም፣ በአስተሳሰቡም፣ በስሜቱም እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአገዛዙ ጋር ከተደረጉ ትግሎች በጣም የተለየ ነው፤ በመጀመሪያ ደረጃ ትግሉ ለሃይማኖት ነጻነት ነው፤ ስለዚህም በአገዛዙ በኩል የፖሊቲካ ዓላማና የፖሊቲካ መልክ እየተሰጠው ሲሆን በእስልምና ምእመኖቹ በኩል ግን ትግሉን ከፖሊቲካ የጸዳ ለማድረግ ግሩም የሆነና የተሳካ ጥረት እያደረጉ ነው፤ ሁለተኛ የትግሉ ስልት ፍጹም ሰላማዊ በመሆኑ የአገዛዙን የጉልበት ስልት እያከሸፈ ያጋለጠው ይመስላል፤ አንዱና ዋነኛው የትግሉ ሰላማዊነት መግለጫ በቤተ መስጊድ መወሰኑ ነው፤ ይህ ስልት አዲስ አይደለም፤ በብዙ የአረብ አገሮች የሚጠቀሙበት ነው።

ተፋላሚዎቹ ያልተገነዘቡዋቸው አንዳንድ ጉዳዮች ይታዩኛል፤ አንደኛ እስልምና በጎሣ የታጠረ ባለመሆኑ ከወያኔ/ኢሕአዴግ የአመራር መሠረት ጋር የመቃወም ዝንባሌ ያሳያል፤ እስልምና አብዛኛዎቹን፣ በተለይም ትልልቅ የሚባሉትን ጎሣዎች ሁሉ በተለያየ ደረጃ የሚያቅፍ ነው፤ ስለዚህም አንዳንዶች የእስልምና መሪዎች ሌሎች (ማለት – ክርስቲያኑ) አልተቀላቀሉንም እያሉ የሚያላዝኑበትን ቆም ብለው መመርመር ያሻቸዋል፤ ክርስቲያኑ በተለይ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ያሉበትን ሁኔታ በትክክል መረዳት ያስፈልጋል፤ እስላሞች ገና ቀደም ብለው ከብዙ ዓመታት በፊት በተደረገ ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ‹‹እስላሞች በጎሣ አይከፋፈሉም›› በማለት የገለጹትን ቁም-ነገር አገዛዙ የረሳው ወይም እስላሞቹ ረስተውታል ብሎ ያሰበ ይመስላል፤ አለዚያ እንዲህ ያለ የከረረ እልህ ውስጥ የገባበትን ምክንያት ለመረዳት ያዳግታል፤ ይቺ ባቄላ ያደገች እንደሆን የሚያሰኝ ነገር ለብዙዎች ሰዎች ምንም አልታየም፤ በጉልበት የማይጨፈለቅ ምንም ነገር የለም ከሚል እምነት ተነሥተው ከሆነ ስሕተቱ እየታየ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ የእስላሙ ኅብረተሰብ ገና በጠዋቱ በጎሣ የመከፋፈሉን አመራር እንደማይቀበለው በማያጠራጥር መንገድ የገለጠ ይመስለኛል፤ ነገር ግን ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች የጎሣ ትግላቸውን ወደቤተ እግዚአብሔር አምጥተው የተከፋፈሉና የተዘጉም ቤተ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ ይህ የሚያሳፍር ነው፤ ቤተ መስጊዶች እዚህ ደረጃ አልወረዱም፤ እስልምና በጎሣ አይቀደድም፤ እስላሞች ሁሉ የአላህ ልጆች ናቸው፤ በቤተ መስጊድ የሚሰበሰበው ሁሉ በአላህ ልጅነቱ ነው፤ ስለዚህም በመሀከላቸው ልዩነት የለም፤ ይህ የእስላሞች አቅዋም ሃያ ዓመት ተፈተነ፤ የማይበገር ሆነ፤ ስለዚህም ከጎሣ አስተሳሰብ ወጥቶ ሌላ ቀዳዳ መፈለግ ግዴታ ሆነ፤ አል-ሀበሽ አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው።
እስቲ ጉዳዩ ለሁላችንም ግልጽ እንዲሆንልን ወደክርስትና ዞረን እንየው፤ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከነገ ጀምሮ የሉተራን ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ተከተሉ ቢባል አንደኛ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን (ካለች) ምን ትላለች? ሁለተኛ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ምን ይላሉ? ሦስተኛ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 ‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤›› የሚለው በጤና አለ ወይ? ብሎ መጠየቅ የማይቀር ይሆናል፤ መልሶቹስ ምን ይሆናሉ?
ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ስዒረ ሊቀ ጳጳስ እንደተደረገ አሁን ታወቀ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም፣ ምእመናኑም፣ ማንም ምንም ያለ የለም፤ የተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያንን ሊቀ ጳጳስ የሻረው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ዛሬ እግዚአብሔር ተገለጠልኝ በማለት ሊቀ ጳጳስዋን የሻረባትን ቤተ ክርስቲያን ትቶ ወደሌላ ተገልብጦአል፤ የተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አባል በነበረበት ጊዜ የሠራውን ኃጢአት ዛሬ የሌላ ቤተ ክርስቲያን አባል ሆኖ እውነቱን ገልጦልናል፤ ታምራት ላይኔ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያንን ከለቀቀ በኋላ የክርስቶስን ጸሐየ ጽድቅነት መረዳቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚያሳፍር ነው፤ ከዚያም በላይ የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አሁንም እውነቱን አላወጣችም፤ አንድም ለሹመት ያኮበኮበ ጳጳስ የክርስቶስን ጸሐየ ጽድቅነት አምኖና ተቀብሎ እውነቱን ለመናገር የደፈረ አልተሰማም፤ ጴጥሮሳዊነት ከጴጥሮስ ጋር ተቀብሮአል አንበል? ይበልጥ ያሳፍራል፡፡
የኢትዮጵያ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያንን ለንጽጽር አመጣሁ እንጂ ዋናው ነገሬ በእስልምና ሃይማኖት ላይ ነው፤ ድርቅና ቁልጭ ያለው እውነት እስልምና አስፈላጊውን መስዋእት ከፍሎ በሰላማዊ መንገድ ጎሠኛነትን ተቃወመ፤ ተቋቋመ፤ አሁን ደግሞ አንደኛ በእስልምና ምእመናን ላይ እንዲጫን የታቀደውን አዲስ የእስልምና ዓይነት አንቀበልም በማለትና ሁለተኛም የእስልምና ካህናትን የምንመርጠው ራሳችን ምእመናኑ ነን፤ ሦስተኛም የእስልምና ካህናቱ ምርጫ የሚካሄደው በመንፈሳዊ ቦታ በቤተ መስጊድ ነው እንጂ በፖሊቲካ ቦታ በቀበሌ አይደረግም አሉ፤ በጎሣ አንከፋፈልም ብለው ጥንካሬያቸውን ያሳዩትን እስላሞች በሃይማኖት ለመከፋፈልና ካህናቶቻቸውን ራሳቸው በየመስጊዳቸው እንዳይመርጡ መከልከል በግልጽ ሕገ መንግሥቱን መዳፈር ነው።
ሁለተኛው ቁም-ነገር አገዛዙ በየቀበሌው ያካሄደው ከሕዝብ ፈቃድ ውጭ ለሆነ ምርጫ እስላሙ ኅብረተሰብ የሰጠው ሰላማዊ መልስ የማያዳግምና የሚያስደንቅ ነው፤ በአገዛዙ ስልት በተመረጡት ሰዎች በሚተዳደሩ ቤተ መስጊዶች ውስጥ አንሰግድም በማለት መስጊዶቹን ባዶ ማድረጋቸው አገዛዙን ራቁቱን አቁሞ ስሐተቱን ያጋለጠው እውነተኛ ሰላማዊ ትግል ነው፤ በቅርቡ ሦስት የአፍሪካ፣ አንድ የእስያ፣ ሁለት ዓለም-አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአቶ ኃይለ ማርያም ኢትዮጵያ ለዓለም-አቀፍ ሕጎች የገባችውን ቃል ኪዳኖች ሁሉ እንድትጠብቅ ከመቼውም የበለጠ ጥረት ማድረግ እንዳለባት የሚገልጽ ረጅም ደብዳቤ ተልኮላቸዋል፤ ለመብቶቻቸው የቆሙ ሁሉ፣ ጋዜጠኞችም ይሁኑ የሃይማኖት ሰዎች በሽብርተኛነት እየተከሰሱና እየተፈረደባቸው ወህኒ ቤት በመግባታቸው ፍርድ ቤቱንም ወህኒ ቤቱንም ጎብኝተው የሄዱት የስዊድን ጋዜጠኞች በሚያሳፍር ሁኔታ ለዓለም አጋልጠውታል።
የቤቴ መቃጠል ለትኋኑ በጀኝ ያለው ቂል ሰው ነው፤ ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ያለው ሰው ሰነፍ ነው፤ ቂልነትም፣ ስንፍናም ለመሪዎች አይበጅምና እግዚአብሔር በጎ መንፈሱን ያሳድርባቸው፤ ያሳድርብን።

No comments:

Post a Comment