No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Wednesday, 28 November 2012

አጫጭር የሀገር ቤት ወሬዎች (ከአዲስ አባባ) ቁጥር 2


ይነጋል በላቸው

ከአዲስ አባባ
Addis Ababa is the capital city of Ethiopia.ባለፈው የዜና ዕወጃችን ይህን መሰል የሀገር ውስጥ አጫጭር ወሬዎች ዘገባ ቢያንስ በሣምንት አንድ ጊዜ እናቀርባለን ብለን ቃል ባልገባነው መሠረት ከመጀመሪያው የቀጠለውን የዛሬውን ዝግጅት ቀጥለን የምናቀርበው በታላቅ  የደስታ ስሜት ነው፡፡ እነዚህ ወሬዎች በምናባዊ የአቀራረብ ፋሽን በመዋዛታቸው የአንዳንዶችን አመኔታ በቀላሉ ላያገኙ እንደሚችሉ ቢጠረጠርም ሀሰት እንዳልሆኑ ግን ለተከታታዮቻችን በዚህ አጋጣሚ ልናስታውስ እንወዳለን፡፡ የዜና ማዕከሉ ውሸትን በመዘገብ የሚያገኘው ቅንጣት ትርፍ አለመኖሩን በሚገባ ስለሚገነዘብ ጥቂቶቹን የሥነ ጽሑፍ አላባውያንና ነገር ማስዋቢያ ግብኣቶችን(literary flavors) ከመጠቀም ውጪ ያልተሰማና ያልተደረገ ወይም ከነአካቴው ‹ይህን ዓይነቱ ነገር ሊደረግ አይችልም!› ተብሎ የሚገመትን ክስተት በዜና ፋይል ውስጥ እንደማያካትት በትህትና ያስታውቃል፡፡ ሃሳብን በተፈለገው መንገድ ማቅረብ ይቻላል፤
ማንበብና ማስነበብ ደግሞ የአስነባቢዎችና የአንባቢዎች ድርሻ ነው፡፡ መንገደኞች ይለያያሉ – ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የመንገዱ መለያየት ግን የግድ ያህል አይደለም፡፡ መቃወም ጥሩ ነው፤ መቃወምን የባሕርይ ያህል መላበስ ግን ተፈጥሯዊ አይደለም፡፡

የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሠራተኞች በሥራቸው መሰላቸታቸው ተገለጠ
በአንዳንድ ነገር ጎንጓኞች ‹የስዬ ኮሚሽን› በመባል የሚታወቀው የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አንዳንድ ሠራተኞች በመሥሪያ ቤታቸው የአሠራር ወጥነት መጥፋት የተነሣ ክፉኛ እየተበሳጩና እየተናደዱ መሥሪያ ቤታቸውንም ጥለው በመውጣት ወደሌላ ኅሊናን የማይፈታተን ሥራ ለመግባት እያሰቡ እንደሆነ ከሥፍራው የደረሰን ጥቆማ ይፋ አድርጓል፡፡ ዝርዝሩ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
“እኔ ከተቀጠርኩ ይሄውና አሥር ዓመት አለፈኝ፤ ነገር ግን የሠራሁት ሀገርንና ሕዝብን ሊጠቅም የሚችል ተጨባጭ ነገር የለም፡፡ በሙስና የተጠረጠረን ሰው ልንመረምር እንላካለን፤ በአዲስ አበባም ከአዲስ አበባም ውጪ፡፡ ነገር ግን ምርመራው ተጣርቶ ተጠቋሚው ግለሰብ አንዳች እንከን ሲገኝበት ባላሰብነው ወቅት ከበላይ አካል በሥልክ ለአለቃችን ይነገርና ‹ያን የእገሌን(የነእገሌን) ጉዳይ ተውት፤ ፋይሉ ይዘጋ› እንባልና ልፋታችን ሁሉ ዜሮ ይሆናል፤ ፋይሉም ተዘግቶ ሰውዬው በጀመረው የሙስና መስመር መንጎዱን ይቀጥላል፡፡ ሕግ የማይገዛቸው ብዙ ምርጥና ዕንቁ ዜጎች አሉ፤ ሀገሪቷን እንዳለ ቢሸጧት ዝምባቸውን እሽ የሚል የመንግሥት አካል የለም፤ ዘበናዮች ናቸው፡፡ እንዲህ እንዳፈለገው የሚሆን ሰው ግን በዘርም በዓላማም የነሱው ሰው ከሆነ ወይም በፖለቲካ የማይፈለግ ከሆነ ወይም በልዩ ልዩ ነገሮች ደጋፊያቸውና የሥርዓታቸው ታማኝ ከሆነ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ የራሱ አቋምና የአሠራር ነጻነት ብሎ ነገርም የለውም፡፡ የወያኔው ቱባ ባለሥልጣናት የሚፈልጉትን ሰው ሀብት ለመቀማትና ሙልጭ ድሃ ለማድረግ ወይም ዘብጥያ ለማውረድ የሚጠቀሙበት እንደግል አሽከራቸው በሥልክ ወይ በቁራጭ ወረቀት ‹የእከሌን ነገር ባፋጣኝ አሳዩን› ሲባል ብቻ የነሱን የበቀል ጥማት ለማስታገስ የቆመ መሥሪያ ቤት ነው፤ የሚያሳዝነው የሕዝብ ከፍተኛ ሀብትና ሁለንተናዊ ፈሰስ ለዚህ ምንም ዕርባና ለሌለው መሥሪያ ቤት እየተመደበ በከንቱ መባከኑ ነው፡፡ ስሜ በዚህ መሥሪያ ቤት የሠራተኞች ዝርዝር ውስጥ ተካትቶ መገኘቱ በውነቱ በጣም ያሳፍረኛል፤ያንገበግበኛልም፡፡ እርግጥ ነው ደመወዙ ከሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስለሚሻል ለቅቆ መሄዱ በተለይ የተሻለ ሥራ ባልተገኘበት ሁኔታ ቤተሰብን ለኑሮ ችግር መዳረግ ነው፡፡ እንጂ እንደአሠራሩ አንድ ቀንም የሚውሉበት አይደለም፤ የብዙው ሠራተኛ ልብቡ እንደሸፈተ መረዳት አይከብድም፤ መድረሻ በማጣት እንጂ፡፡” በማለት ለዘጋቢያችን ያብራራው ስሙ እንዳይገለጥበት በ44ቱ ታቦት የተማጠነ የኮሚሽኑ አንድ ሠራተኛ በመቀጠልም ይህ መሥሪያ ቤት እንደሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ከከፍተኛ እስከዝቅተኛ የኃላፊነትና የሥራ ቦታዎች ላይ የተመደቡትና የሚመደቡት ሠራተኞች በትምህርትና በልምድ ሳይሆን በታማኝነታቸውና የገዢው መደብ የዘር ሐረግ ያላቸው በመሆናቸው በልዩ ትዕዛዝ የሚላኩ ዜጎች መሆናቸውን፣ ከጠቅላላው የሠራተኞች ቁጥር ሌሎቹ ብሔር/ብሔረሰቦች 20 በመቶ ገደማ ቢሆኑ እንጂ የተቀረው ሙሉ በሙሉ ወይም አንድ ሁለተኛው ወይም ሦስት አራተኛው ወይም ቢያንስ አንድ ስምንተኛው በጥናት የተረጋገጠ የአንደኛ ደረጃ ዜግነት ካለው የገዢ መደብ መሆኑን ለዘጋቢያችን የእምነት ክህደት ቃሉን የሰጠው ይህ ሠራተኛ ገልጧል፡፡ ወጣቱ የቢሮ ኃላፊ ሲያጠቃልልም “ እኔ በውነቱ ይህ መሥሪያ ቤት እጅ እጅ ብሎኛል፤ልቀቅ ልቀቅ ብሎኛል፡፡ ወደዚህ የመጣሁት ባለችኝ ትንሽ የደም መጠጋጋት ቢሆንም በትግሬነቴ የሚመጣ ጥቅም ጥንቅር ብሎ ይቅር፤ ወያኔዎች ስልችት ብለውኛል፤ መድረሻ ማጣት እንጂ የነሱ ቀረቤታ በጭራሽ አያስፈልግም፡፡ የማየው የዘረኝት በሽታም አንገሽግሾኛል፡፡ ‹ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ› ለማታለልና ስዬ አብርሃን መሰል ተቃዋሚዎችን ለማሰር በአንድ ቀን በመለስ ተጠፍጥፎ በአንድ ቀን አዳር ፀድቆ በአንድ ቀን አዳር በተመሠረተ የውሸት ኮሚሽን ለእንጀራ ስል ብቻ ‹መሥራቱ› ቋቅ እስኪለኝ አስጠልቶኛል፡፡ ለተግባራዊ ክንውን ሳይሆን ለማስመሰያነት ለተቋቋመ መሥሪያ ቤት ይህን ያህል በጀትና የሰው ኃይል መባከኑ፣ ይህን ያህል ሰፊ ቢሮ ለቲያትርና ለቧታይ ድንቃይ ድራማ ሲባል ካለጥቅም ለገሀር እምብርት ላይ መጎለቱ በእጅጉ ያሳዝነኛል፡፡ ስለዚህ ጡረታ ለመውጣት የቀረችኝ ጊዜ አንድ ሃያ ዓመት ብቻ ስለሆነች ያቺ ስታልቅልኝ ጡረታ ወጥቼ የግል ሥራየን እሠራለሁ፡፡” በማለት በከፍተኛ መንገፍገፍ ብሶቱን ገልጧል፡፡ ምኞቱ እንዲሠምር የዝግጅት ክፍላችን ይመኛል፡፡
በሌላ ዜና የዚህን መረጃ ትክክለኝነት ለማረጋገጥ ዋና ኮሚሽነሯን እንወይ ገ/መድኅንን በሥልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ሴትዮዋ ከለቀቀች ብዙ ዓመታትን በማስቆጠሯ ምክንያት ሊሳካልን አልቻለም፡፡ የአሁኑ ኮሚሽነር ግን ‹እኔ ለማላዝበት መ/ቤት ምን አዳረቀኝ?እኔ ምን ቤት ነኝና?› በሚል ደመወዝና አበል ለመቀበል  ብቻ በወር አንዴ ወይ ሁለቴ ወደመ/ቤት እንደሚመጡና እንደማይመጡ ከውስጥ ዐዋቂ ምንጮች ለማጣራት ያደረግነው ጥረት አሁንም አልተሳካም፡፡
ፍርሀትና ትግስት ውሕደት መፍጠራቸው ተነገረ
እስከቅርብ ዓመታት ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በተናጠል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይታወቁ የነበሩት አቶ ፍርሀትና ወይዘሮ ትግስት በመካከላቸው ነበረ የተባለው የልዩነት ክፍተት ከጊዜ ወደጊዜ እየጠበበ መጥቶ አንዳቸውን ከሌላኛቸው ለመለየት የማይቻልበት ወቅት ላይ በመደረሱ በአቶ መኖር በዘዴ አደራዳሪነት በቅርቡ ውሕደት መፍጠራቸውንና ከዚያም ባለፈ በትዳር ተቆራኝተው ልጆችን ለማፍራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለንጋት የዜና ወኪል ሰሞኑን አስታወቁ፡፡ ትዳራቸው ሠምሮ ልጆችን ማፍራት ቢችሉ ለልጆቻቸው ምን ዓይነት ስሞችን ለመስጠት እንደሚፈልጉ የተጠየቁት አቶ ፍርሀትና ወይዘሮ ትግስት ሲመልሱ “በቅድሚያ ስለተሰጠን ዕድል ልናመሰገን እንወዳለን፡፡ በመሠረቱ እኛ በተፈጥሯችን እንኳንስ ለጋብቻና ለዘር ሐረግ ጥምረት ይቅርና ለጉርብትናም ልንበቃ የማንችል በጣም የተለያየን ፍጡራን ነበርን፡፡ ነገር ግን ዕድሜ ለትውልድ ሞራልና ሃይማኖት መላሸቅ ይሄውና በየፊናችን ተከብረንና ተፈርተን እንዳልኖርን ሁሉ ዛሬ አዳሜ እየተነሣ ‹ታግሼህ እንጂ ፈርቼህ እንዳይመስልህ! ‹ትግስት መራራ ብትሆንም ፍሬዋ ጣፋጭ ነው›፣ ቆይ ብቻ! አሳይሃለሁ!› እያለ በውስጡ ግን በፍርሀት እየራደ ለመኖር ሲል ብቻ የዛሬ እስትንፋሱን ለነገ ለማሳደር ሲዋረድ፣ በገዛ ቀዬው በሕዝብ ፊት ሳይቀር ቆለጡን በገመድ እየተጎተተ አውሮፓና አሜሪካ ላይ ያለ ይመስል የምሽቱን እንትን በአደባባይ እንትን እንዲል ሲገደድ፣ በስማም እንደተባለበት ሰይጣን በፍርሀት ቸነፈር የእኖርባይነት ጋግርት እጁና አንደበቱ ተለጉሞ በቁም ለሞተበት የመከራ ሕይወት ቀጣይነት ሲል የላም አለኝ በሰማይን የነገ ውሎ ለማየት ሲጓጓ፣ ወዘናው ተንጠፍጥፎ ሁሉም ነገር ያለቀበት ዛሬ ለሚያከናንበው ውርደት አንገቱን ደፍቶ  ሲልመጠመጥ ስታየው …› በማለት ወዳልተጠየቁት ጥያቄ መልስ ውስጥ ሲገቡ ያቋረጣቸው ዘጋቢያችን እንደገለጸው ከሆነ ሁለቱ ለሚወልዷቸው ልጆች ከሚሰጧቸው ስሞች መካከል ‹ጉድሠራኝ፣ አቀለለኝ፣ አዋረደኝ፣ባዶአስቀረኝ፣› እና ‹ባገርናኘ› ጥቂቶቹ መሆናቸውን እንደገለጹለት አስታውቋ፡፡ አቶ ፍርሀት አክለውም ‹ከእንግዲህ ሰውም ጉድ ይበል፤ ዓለምም ሲፈልግ ተወቅሮ ይሳቅ፤ በኢትዮጵያ ምድር ፍርሀትና ትግስት ተጋብተዋል፤ አንድ ሆነዋል፤ ለዚህ ደረጃ ያበቁንን ደርግንና ወያኔን ደግሞ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ደርግ በጠራራ ጠሐይ ትውልድን በመትረየስ እየጨፈጨፈ በሕዝቡ ውስጥ ፍርሀትን አነገሠ፣ የትዕግሥትንም ዋጋ አኮሰሰ፡፡ በዚያም ሳቢያ በሁለታችን መካከል የነበረው ልዩነት ሲጠፋ  ተቀላለቅልን፡፡ በኛ ማን ሊፈርድ ይችላል?› በማለት ሁለት የማይገናኙ ነገሮች እንዴት ሊገናኙ እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች መጨናነቅ ችግር ማስከተሉ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ከየት መጡ በማይባሉ ዘመናዊ መኪኖችና ተሸከርካሪዎች እየተሞላችና ለእግረኞች መሄጃ መንገድ እየጠፋ መምጣቱ ታወቀ፡፡ በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ አብዛኛው ሕዝብ ይልሰውንና ይቀምሰውን አጥቶ በርሀብና በችግር እየተንጠራወዘ በሚገኝበት በዚህ ዘመን በአውሮፓ እንኳን በብዛት የማይታዩ ሀመርንና ራቭ6ን የመሳሰሉ ዘመናዊ አውቶሞቢሎች እንዴት በአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች ሊርመሰመሱ ቻሉ የሚለው ጥያቄ ሃሳብ የሆነባቸው አስተዋይ ዜጎች እንደሚሉት ወያኔን የተጠጉ መዝባሪና ሙሰኛ ዜጎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው በሀገር ሲወረር አብረህ ውረር ፈሊጥ በለየለት ዘረፋ ወስጥ ተሠማርተው የሚገኙ ብዙዎች ዜጎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹ደመወዙ በጣም አነስተኛ ከመሆኑ የተነሣ የቤተሰቡን ነፍስ ቢያውል እንደማያሳድር የሚታወቅ ሰው ሽንጣም አውቶሞቢል ይዞ ብታየው ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለህ ሊገርምህ አይገባም› በማለት የሙሰኛ ባለሥልጣናትንና ሠራተኞችን እንዲሁም ከቀረጥ ነጻ ዕቃዎችን ወደሀገር በማስገባት በአንድ ቀን አዳር የሚከብሩ ባለጊዜዎችን ገመና ያጋለጠው አንድ ስሙ እንዳይገለጥ የተማጠነ ታዛቢ ‹ ይህች ሀገር የዕንቆቅልሽ ሀገር ናት፡፡ ሰው እንዴት እንደሚኖር አታውቅም፡፡ የሁሉም ነገር ዋጋ ተሰቅሏል፡፡ ጥሩ ደመወዝ የሚያገኙ ሰዎች ራሳቸው ከሥጋና ከወተት እንዲሁም ከአትክልትና ፍራፍሬ ተፋትተው አንጀታቸው በሽሮና በበቆልት ምግብ እየተቆዘረ ባለበት ሁኔታ ጥቂት የማይባሉ የሀገሪቱ ምርጥ ዜጎች የሀገሪቱን ሀብት ለብቻ ተቆጣጥረው እንዲህ የተቀማጠለ ኑሮ መኖራቸው መጨረሻው የማያምር ከመሆኑም በተጨማሪ – ከምላሴ ፀጉር ይነቀል – የከፋ ቀን ሲመጣ ከፍተኛ መተላለቅን የሚያስከትል ይሆናል፡፡ መኪናው ግድ የለም፤ ይንዱ፡፡ ይፏሉበት፡፡ ነገር ግን ለተራው ዜጋ ቢያንስ በቀን አንዴ ቀምሶ እንዲያድር ሊፈቅዱለት በተገባ ነበር፡፡ባለሥልጣኑና ነጋዴው እየተመሣጠረ ሀገሪቱን ለራሱ ምድረ ገነት ሲያደርጋት ለአብዛኛው ሕዝብ ግን ከሲዖልም የባሰች ዘግናኛ ሲዖል አደረጋት፡፡ ግዴለም፤ የበደል ቋቱ ሲሞላና እግዚአብሔር የቁጣ ጅራፉን ሲያነሳ በሠፈሩት ቁና መሠፈራቸው አይቀርም፡፡እነሱ እያሉ ስደቱም ሆነ ስቃዩ አይቆምም፡፡ የጀመራቸው እሳት አቃጥሎና ለብልቦ እስኪፈጃቸው ድረስ ለጥቂት ጊዜ እንቸገራለን እንጂ እንዲህ ላያችን ላይ እንደተጎመሩብን የሚቀሩ እንዳይመስላቸው፡፡› በማለት በቁጭት ተናግሯል፡፡
በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ብዙ ሥፍራዎች መንገዶች እየታደሱ ወይም እየተስፋፉ በመሆናቸው በሰዓት ወደ ሥራ መግባትና ከሥራ ወጥቶም በጊዜ ወደቤት መግባት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ ታውቋል፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ወቅት በትራፊክ እንቅስቃሴ መጨናነቅ የተነሣ በመኪና ከመሄድ ይልቅ በእግር መሄድ እንደሚሻል ጓደኛው ሊፍት ሊሰጠው መኪና አቁሞለት ሲያበቃ እንዲሣፈር ግባ ሲለው ‹አይ፣ ሂድ ግዴለም፤ እቸኩላለሁ› በማለት አስቆ ግብዣውን ያልተቀበለውን አንድ ሠራተኛ  በመጥቀስ ለዚህ ዘጋቢ የገለጸ አንድ ታዛቢ አስታውቋል፡፡ ይህ የመንገዶች መጨናነቅ እንደወትሮው በሥራ መግቢያና መውጫ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን እሁድንና ቅዳሜን የበዓላት ቀናትንም ጨምሮ ሁልጊዜ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቀን እንደጅብ እየተኙ ወይም ቅጠላ ቅጠል እያመነዠኩ የሚውሉ ገንዘብ በመተት መሰል ነገር የሚያገኙ የሚመስሉ ዜጎች  ለጭፈራና ለቢስነስ ሥራ ሌሊቱንም በመኪኖቻቸው ሲዘዋወሩ ስለሚያድሩ የሌሊቱም መጨናነቅ በተለይ በካዛንቺስና በዑራኤል አካባቢዎች ከቀኑ ብዙም እንደማይለይ አንዲት ለጉዳዩ ቅርበት ያላት ኮረዳ አስታውቃለች፡፡
የመኪና መንገድ ሥራን በተመለከተም አንድ የአውራ ጎዳና ሠራተኛ እንደገለጡት ‹መንግሥት የመንገድ ሥራዎችን ለቻይኖቹና ለግል ተቋራጮች እንደመሥጠት ለዳተኛው የመንግሥት አውራ ጎዳና ባለሥልጣን እየሰጠ አንድ ኪሎ ሜትር ሠርቶ ለማጠናቀቅ ከሁለት ዓመት በላይ እየፈጀ ያለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ ከላምበረት መገናኛ አደባባዩ ድረስ ያለው የሦስት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ሥራ ይሄውና በሁለተኛ ዓመቱ እንኳ ገና ከቁፈራ አልወጣም፡፡ የግሎቹ ቢይዙት ኖሮ እስካሁን አልቆ ነበር፡፡ በጀት ለማስያዝ ሲሆን ቀና ደፋ ይላሉ፤ ከፀደቀ በኋላ ሥራው ምንም አይሠራም፡፡ የሀገር ፍቅርና የሥራ ፍቅር ጠፍቷል፡፡ ብዙዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ዘመዳቸው ሙስናና ገንዘብ ብቻ ነው፡፡ ተራው ሠራተኛም ተገትሮ ነው የምታየው፡፡ ተግቶ እንዲሠራ ንቁ ኃላፊና ጥሩ ክፍያ የለውም፡፡ ስለዚህ በምንቸገረኝነት አካፋውን ተደግፎ ከጧት እስከማታ በወሬ ተጠምዶ ታየዋለህ፡፡ ዛሬ ዛሬ ሥራ በግል እንጅ በመንግሥት ቤት ቀርቷል ወይም ተዳክሟል ማለት ይቻላል፡፡ ማን ማንን ይቆጣጠራል? አለቃና ምንዝር ሁሉም ተፈራርቶ ዝም ብሎ ነው እንደበግ እየተጋፋ የሚኖር፡፡
የሀገሪቱ የአሁንና መፃዒ ዕድል በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ የኔ የሚላት ዜጋ ባለመኖሩ በየመስኩ ሥራ እየተበደለ፣ የምንቸገረኝነት መንፈስም ዜጎችን እየበከለ ሀገሪቱ አደገኛ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚያ ላይ ወያኔ ሊያዛምተው የሞከረው የዘረኝነት ልክፍት ብዙውን ዜጋ እየተፈታተነው መጥቶ አንጎሉን በወንዘኝነት ልምሻ እየበከለው ይገኛል፡፡ መሬትን በዘርና በአጥንት የመከፋፈል አባዜም እየተንሰራፋ ሄዶ መኪናና ሕንፃ ሳይቀሩ በዘርና በጎሣ ታፔላ እየወጣላቸው ሁሉ ነገር የተመሰቃቀለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል – ትግሬ ስካይባስ፣ አማራ ሚኒባስ፣ ኦሮሞ ስካኒያ፣ ደቡብ ሕዝቦች አይሱዚ…ይባልልሃል – ዱዳዎቹ ተንቀሳቃሾችና ግዑዛኑ ዕቃዎች አለዘራቸው አማራ ኦሮሞ እየተባሉ እነሱም ዘረኛ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ብቻም ሳይበቃ ለአንድ ቦታ ሁለትና ሦስት ስም በመስጠት ባቢሎንን መልሰው በኢትዮጵያ ላይ ነፍስ ዘርተውበታል፡፡ የጉልቻ መለዋወጥ ወጥን እንደማያጣፍጥ ሁሉ በስም መለዋወጥ የሚመጣ ከሥነ ልቦና የዘለለ ጉልህ ምጣኔ ሀብታዊና ቁሣዊ ጥቅም እንደማይኖር መገንዘብ አቅቷው ሕዝቡን ያወናብዱት ይዘዋል፤ ስም ደግሞ መጠሪያ እንጂ ይህን ያህል አቅልን ሊስቱለት የሚገባ ነገር  አይደለም፡፡ እስኪ እንዲያው ለመሆኑ ግን – እግዜር ያሳያችሁ – ንብረት እንዴት በዘር ሐረግ ይጠራል? ለነገሩ ሁሉም በየዘር ቋጠሮው – በየከረጪቱ ሲከት ሀገሪቱ የኔ የሚላት አጥታ መለመላዋን እንድትቀርና ጠላቶቿም የዘመናት ዕቅዳቸው ባሰየጠኗቸው የገዛ ልጆቿ አማካይነት እንዲሣካላቸው  በመታቀዱ ነው፡፡  በዚህም ተባለ በዚያ ባጭሩ ሀገሪቱ ባለቤት አጥታለች፡፡ የሰው ያለህ እያለች ነው፡፡› በማለት አሳዛኙን የሀገር ገጽታ አስረድተዋል፡፡
የአምልኮ ሥፍራዎች ለድምፅ ብክለት ተጠያቂ ናቸው ተባለ
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኦርዶክስ እምነት ተከታይ እንደገለጡት ‹ ማንኛቸውም የአምልኮ ሥፍራዎች ይሄን በተለይ ሌሊት ሌሊት የሚከፍቱትን የድምጽ ማጉያ ቢተውት ይሻል ነበር፡፡ ታሞ የሚተኛ አለ፤ በአካባቢው ሐኪም ቤት ሊኖር ይችላል፤ አዳሪ ትምህርት ቤት ይኖራል፤ ቀኑንና ምሽቱን በሥራ ሲደክም ቆይቶ ቤቱ ገብቶ ማረፍ የሚፈልግ ሰው አለ፤ ከነአካቴውም ሃይማኖት የሌለው ነገር ግን በሰላም ተኝቶ የማደር መብቱ ሊነፈገው የማይገባ ዜጋ አለ፤… ስለዚህ በቀን እንደፈለጉ ቢያደርጉም በሌሊት ግን በእልህ በሚመስል ሁኔታ ወደውጭ የሚለቁትን ከፍተኛ የድምጽ ሞገድ ማቆም አለባቸው፡፡ የሃይማኖት ተቋማቱ የአመራር አካላትም ይህን ችግር በቀናነት ተረድተው አንዳችም ሕግና መመሪያ ሳይጠብቁ ቢያንስ ሰማይና ምድር እስኪላቀቁ ድረስ ይህን ጩኸት ቢያስቆሙ መልክም ነው፡፡ ይህን መናገር ደግሞ በፀረ-ሃይማኖተኝነት ሊያስፈርጅ አይገባም፡፡› በማለት ለዚህ ዘጋቢ ገልጠዋል፡፡
ተዘዋውረን የሕዝብ አስተያየት ለመቃረም እንደሞከርነው በርግጥም ብዙ ነገሮች እየተደረጉ ያሉት ከመጻሕፍቱ በተቃራኒ እንደሆነና የሃይማኖት ሰዎች ቅዱሳት መጻሕፍታቸውን ቢመረምሩ እንደሚሻላቸው  ብዙዎች አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ በክርስትናው ሃይማኖት ለምሳሌ የሃይማኖቱ የማዕዘን ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወት በነበረበት ወቅት እንደመከረው ሰዎች መንግሥተ ሰማይን ሊወርሱ የሚችሉት በጸሎት ርዝመት ሳይሆን በእምነታቸው ጥብቀትና በሥራ በሚገለጽ ፍቅር እንደሆነ በመግለጽ ‹አባታችን ሆይ …›ን ከልብ መጸለይ ብቻውን በቂ እንደሆነ አስተምሯል፡፡ ‹ስለዚህ› ይላሉ አንድ አስተያየት ሰጪ ‹ስለዚህ እንደክርስቶስ ከሆነ በአሁኑ ዘመን ያሉት ካህናትና ቀሳውስት የድምጽ ብክለት ብቻ ሳይሆን የጸሎት ብክነትም እያደረሱ ነው ቢባል ከክርስቶስ አስተምህሮ አኳያ ትክክል ነን ማለት ይቻላል› ሲሉ ይህ ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶበት መንግሥትም የሃይማኖት ተቋማትም እንዲያስቡበትና በተለይ የሌሊት የማጉሊያ ጩኸቶች ገደብ እንዲበጅላቸው አበክረው አሳስበዋል፡፡ በማጉሊያ ከሚሰሙና ቤተ ክርስቲያንን ወይም መስጂዶችን በየመኝታ ቤታችን ካለሰዓቱ ከሚያመጡ የጸሎት ዓይነቶች መካከል ጥቂቶቹ የሌሊት ማኅሌቶች፣ የአዛን ጥሪዎችና በከፍተኛ የሰውና የሙዚቃ መሣሪያ ድምፅ የታጀቡ የመዝሙር ሽብሸባዎች መሆናቸውም ተገልጾኣል፡፡ ስለሆነም ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ የጩኸት ማስተጋቢያ ባልተሠራባቸው ጥንታዊ ዘመናት የተደነገጉና ከአንድ ሰው የመጮህ አቅም በላይ ሄደው አካባቢን ያውኩ ያልነበሩ ጸሎቶች ዛሬ በከፍተኛ ቴክሎጂ ታግዘው የሕዝብን በሰላም የመተኛትና የማረፍ መብት በባህልና በሃይማኖት ሽፋን እንዳይጋፉ ያስፈልጋል ሲሉ ብዙዎች አስተያየታቸውን በምሬት ገልጠዋል፡፡
ከዚሁ በተያያዘም በየአካባቢው በተለይ ሐሙስና ቅዳሜ በየቃልቾችና ጠንቋዮች ቤት በሚደረገው የዛር ድልቂያና የአውሊያ ዳንኪራ ብዙ ዜጎች ቅሬታ እንዳደረባቸው ተዘግቧል፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ዳርቻዎች ነዋሪዎች ለሪፖርተራችን እንደገለጡት እነዚህ ሰይጣናዊ የዛር መንፈስን ለመጥራትና በፈረሱ – ሰው ላይ ተሹሞ የመጡበትን ፍርድና ቅድ ለማግኘት የሚጥሩ ወገኖች ዛሩ ገብቶ እስኪወጣ በሚያሰሙት የድቤና የከራማ መጥሪያ መንዙማ እንዲሁም የበሽተኞች ጉሪያ ምክንያት ስለሚረበሹ እንቅልፍ የሚባል ነገር ሳያዩ እንደሚያድሩና ከዛሩ ቤት በሚወጡ ጢሳ ጢሶችም ለአስም ህመም እንደሚዳረጉ ጠቁመዋል፡፡ አንድ በዚህ ችግር የተበሳጨ ሰው እንደተናገረው ‹ እርግጥ ነው  ሰው ሲቸገር ጠንቋይ ቤት ቀርቶ ገመድ ይዞ ወደሚቀርበው ዛፍ ሊሄድና ሊሰቀልም ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰዎች ማወቅ ያለባቸው ነገር ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ ወደፈጣሪ እንደመጮህና መልሱን በትግስት እንደመጠባበቅ የራሱን ችግር መፍታት ወደማይችል የሰው ልጅ ዘንድ በመሄድ ለዛርና ለአውሊያ ማፈንደድ በፍጹም ተገቢ አለመሆኑን ነው፤ ከጤናማ ሰውም አይጠበቅም፤ ለምታልፍ ዓለም ለሚያልፍ የስደት ዓለም ፈጣሪን ማሳዘን አይገባም፡፡ ብዙ ዜጎች በዚህ የተሳሳተ ጎዳና ሲነጉዱ ይታያል፡፡ በዚህ የማያዋጣ ሙከራቸው ነፍሳቸውንም ሥጋቸውንም ለሚያቆሽሽ የአጋንንት ተግባር ይጋለጣሉ – ለጊዜው ሰይጣን ማስመሰልና መማረክ ያውቅበታልና የተወሰነ ሥጋዊ ድሎትና ምቾት ሊሰጣቸው ይችላል፤ አሁን ዓለምን እየገዛ ያለውም እርሱ ነው – ቀድሞ ቃል ተገብቶለታልና፤ ዘመኑ ግን እያለቀች እንደሆነች አበቅቴው ይናገራል፡፡ ይሁንና ሰይጣን የሚናቅ ኃይል አይደለምና እያዋዛ ወደግዛቱ አስገብቶ ለመከራ ነፍስና ለመከራ ሥጋም ይዳርጋል፤ ብዙ አይተናል፡፡ እርሱን ለማሸነፍ ብርቱ የመንፈስ ጥንካሬና የጸሎት ጥሩር መታጠቅ ይገባል፤ ፈሪ ነው – በአንዲት ‹በስማም› 40 ሜትር የሚሸሽ ድንጉጥ ነው፡፡ ያቺ ‹በስማም› ግን ጠንካራ እምነት ካለው ግለስብ የምትወጣ መሆን አለባት፤ ‹ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ› በእግዜር ቤት አይሠራም፡፡ የሰይጣን ስጦዎች በሬን ጨው እያላሱ ወደመታረጃው እንደመውሰድ ያህል ናቸው፡፡ የሃይማኖት መምህራንም በዚህ ረገድ ኃላፊነታቸውን የተወጡ አይመስሉኝም፡፡ እንዲያውም ከነሱም መካከል ወደነዚሁ የአጋንንት ሰዎች የሚሄድ እንደማይጠፋና በጥንቆላው ውስጥም የሚሳተፉ ደብተራዎችና መሪጌታዎች እንዳሉ በማኅበረሰቡ ዘንድ በስፋት ይታወቃል – ደንበኛቸው ማን ሆነና? ኮከብ እቆጥራለሁ – ዓይነጥላሽን እገፍልሻለሁ፤ ጠላትህን በአንደርብ እመታልሃለሁ፣ ዐውደ ነገሥቱን ቆጥሬ የምታገባትን ሴት እለይልሃለሁ … የሚለው ቀጣፊ የአጋንንት ውላጅ ደብተራ ሁሉ ይህን ዕኩይ የሰይጣን ሥራ የሚያከናውነው ቤተ ክርስቲያንን ተጠልሎ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ብቻ ችግራችን የተወሳሰበ ነው፡፡…› በማለት የተሰማውን ስሜት በምሬት ገልጾኣል፡፡
በአዲስ አበባ ያገለገሉ ዕቃዎችን መሸጫ ሱቆች እየተበራከቱ መሆናቸው ተገለጸ
አዲስ አበባን ከራስጌ እስከግርጌ የሚጎበኝ ሰው በየሥፍራው ያገለገሉ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ለዳግመኛ ሽያጭ ከየቸገረው ሰው በቅናሽ ዋጋ እየተገዙ እንደሚሰባሰቡ መረዳት ይቻለዋል፡፡ እንዳንዳንዶች አስተያየት ከሆነ ባልተለመደ ሁኔታ ይህን ያህል የአሮጌ ዕቃዎች ሽያጭ ደርቶ ሊታይ የቻለው የድህነቱ መባባስ ያስከተለው የነበረን ጥሪት እያወጡ በመሸጥ ጊዜ የማይሰጠውን የቤተሰብን ወስፋት ለመሸንገል መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በዚያ ላይ ልጆችን ለማስተማር፣ ለመመገብና ትምህርት ቤት ለመላክ ገንዘብ ስለሚያስፈልግ ቤትን ባዶ እያደረጉ በደህናው ቀን የተገዛን ዕቃ ለመሸጥ የሚገደዱ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ታውቋል፡፡ በአንድ በኩል የወቅቱ ማይማን ሀብታሞች ለአንድ የቤት ዕቃ በመቶ ሺዎች የሚገመት ብር እያወጡ ቤታቸውን ሲያሸበርቁ ቤላ በኩል ደግሞ ብዙዎች ለዕለት ጉርስ ሲሉ የዘመናት አንጡራ ጥሪታቸውን እያወጡ በርካሽ ሲሸጡ ሲታይ ኑሮ በኢትዮጵያ የመጨረሻው ዕንቆቅልሽ ደረጃ መድረሱን ያሳያል የሚሉ ወገኖች ሞልተዋል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በመንገዶች ዳርና ዳር የሚታዩ ያገለገሉ ዕቃዎች ሽያጭ የሚያሳየው የሕዝቡን መደኽየት ሲሆን በሌላ ቀጭን መስኮት በኩል ደግሞ ባለጊዜዎቹ በአንድ ቀን አዳር ከብረው ሲድሩ የነበራውን የቤት ዕቃ ለአሮጌ ዕቃ ተቀባዮች ስለሚያስረክቡ ከተማዋን ወደአሮጌ ዕቃ መደብርነት እየለወጧ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡
ዘጋቢያችን ተዘዋውሮ ባደረገው የዋጋ ጥናት መሠረት በደርግ ጊዜ ከኢትሆፍ 500 ብር ገደማ ይሸጥ የነበረው ባለስድስት ወንበር የምግብ ቤት ጠረጴዛ አሁን እንደየይዞታው በአሮጌ ተራ ከአራት እስከ ስድስት ሺህ ብር እንደሚጠራ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በስድስት መቶ ብር ገደማ ይገዛ የነበረው ባለሦስት ተካፋች የልብስ ቁም ሣጥንም በአሁኑ የአሮጌ ተራ የሳልቫጅ ግዢ ከሰባት ሺህ ብር በላይ እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡ ሻጮቹ ለአትራፊዎቹ ሲሸጡ ግን ያን ያህል ጥቅም እንደማያገኙበትና የመጣል ያህል እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዕድሜ ጠገብ የቀድሞ ደህና ነዋሪ ሰዎች ምርጫ ሲያጡ ከመዶሻና ማርቴሎ አቅም እንኳን ሳይቀር ቤታቸው ውስጥ የሚገኝን ዕቃ እያወጡ በመሸጥ ለዕለት ጉርሳቸው እንደሚጠቀሙበትና ለዚህ ውርደት የዳረጋቸውም የወያኔው ሥርዓት በዜጎች መካከል የፈጠረው ዐይን ያወጣ የሀብት ክፍፍል ሥርዓት አልባ መሆን እንደሆነ አንዳንድ ምሁራን በጥናቶቻቸው ገልጠዋል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ የሚፈልግ አንባቢ ኬኔዲ የዘፈነውን ‹አንድ ነኝ› የሚለውን ብሶተኛ የዘፈን አልበም ማዳመጥ ወይም ኬኔዲ ቤተ መጻሕፍት ገብቶ ጽሑፎችን ማገላበጥ ይችላል፡፡
በተያያዘ ዜና አዲስ አበባ ውስጥ የድሃና የሀብታም ሠፈሮችን ማወቅ ለሚፈልግ አዲስ ግኝት መዘገቡ ታወቀ፡፡ ይሄውም አዲስ ግኝት በሀብታሞች ሠፈር ውስጥ የሚገኙ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች የሚይዟቸው ዕቃዎች ኬክ፣ የአውሮፓ ብስኩቶች፣ ሀምበርገር፣ የታሸገ ውኃ፣ ፖም፣ ሙዝና ብርቱካን፣ የፊልም ሲዲዎች፣ ብላክቤሪና አይፎን የእጅ ስልኮችና የመሳሰሉት ሲሆኑ በኛ ሠፈር የሚገኙ አዟሪዎች ደግሞ ሎተሪ፣ ሸንኮራ አገዳ፣ቆሎ፣ መፋቂያ፣ የቻይና የሚያቃጥል ካልሲ፣ ኮቸሮ፣ እዛው በላች እዛው ሞተች የዐይጥ መርዝ፣ መርፌና ክርና መርፌ ቁልፍ፣ የቻይና ተማሪ በቤት ሥራ ታዝዞ የሚሠራት ፎርጅድ ኖኪያ የእጅ ስልክና የመሳሰሉ እንደሸንኮራው አላቂና እንደመርፌዋ ቋሚ ዕቃዎችን ነው፡፡
በሌላ ዜና እስከምንገናኝ ቸር እንሰንብት፡፡
source. ECADF

1 comment:

  1. The articles are not visible.please try to make it visible colour like black...otherwise don't waste u r time!and make the words bold ,attractive.

    ReplyDelete