No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Sunday, 30 June 2013

ተመስገን ደሳለኝ ለማን ደስ ይበለው ብሎ ጠፋ!? (ከአቤ ቶኪቻው)

ተመስገን ደሳለኝ ለማን ደስ ይበለው ብሎ ጠፋ!?
ባለፈው ጊዜ አንድ ወዳጄ ጋር አዲሳባ ስልክ ደውዬ ሳናግረው በአካባቢው ከእርሱ ድምጽ ጎልቶ የሚሰማ የመኪና ጥሩንባ ሰማሁና ይሄ ሁሉ የመኪና ጥሩምባ ምንድነው… ብዬ ጠየኩት፡፡
Journalist Temasegan Dasalegሃይለማሪያም ደሳለኝ እየገቡ ወይም እየወጡ ነው መሰለኝ መንገድ ተዘጋግቷል፡፡ አለኝ፡፡
ወዲያውም ቀጠል አድርጎ፤ እንደ ሀቁ ቢሆን ኖሮ መንገድ መዘጋጋት የነበረበት ለሀይለማሪያም ደሳለኝ ሳይሆን ለተመስገን ደሳለኝ ነበር… አለኝና በቁጭት፤ ይሄው የሚያጅቡትን አያቀውቁምና… እልኩ እያታዘብኩ ነው…! ሲል አወጋኝ!
ተመስገን ደሳለኝ ገዢውም ተገዢውም ፓርቲ ሊያመሰግነው የሚገባ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ነገር ግን ገዢዎቻችን ማመስገን የሚቆጥር ይመስል ሰውን ማመስገን አይወዱም፡፡ ስለዚህ ተሜንም በማመስገን ፈንታ ከሰሱት፡፡ ጎሽ በማለት ፈንታ እንደ ጎሽ ሊወጉት ቀንዳቸውን አሾሉበት፡፡ እሰይ በማለት ምትክ ሰይ ባንከረባብት ብለው ለሁለቱም አሰቡት፡፡ (ለማሰርም ለማሰደድም) (ሰይ ባንከረባብት በልጅነታችን ብይ ጨዋታ ላይ ተወርዋሪዋ ብይ ጉድጓዳ ውስጥ ብትገባም የተቃራኒውን ብይ ብትመታም ነጥቡ እንዲያዝልን ውል የምንገባባት ቃል ነበረች፡፡)
ተመስገን ደሳለኝ እንዲሰደድ መንግስት ከፀሎት ጀምሮ ሁሉንም አይነት የትግል ስልቶችን እንደተጠቀመበት ትዝ ይለኛል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ጊዜ ምንም የቀጠሮ ወረቀት ወይም መጥሪያ ሳይሰጠው በራዲዮን፤ “ተመስገን ደሳለኝ በሌለበት የፍርድ ሂደቱ ታየ ለሚቀጥለው ጊዜ ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርበው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል!” የሚል አይነት ዜና በሰላም ቁጭ ብሎ ሻይ በሚጠጣበት ካፌ ውስጥ ሰማ፤ (እናጋን ካልን ደግሞ ዜናውን እንደውም ያነበቡት ተሜ ልክ ዜና ሲሰማ አይተው ነው…! ማለት እንችላለን…) የዚህ ዜና አላማ ግልፅ ነበር፡፡ ተሜ ደንግጦ ፖሊስ ሳይዘው በፊት መንገዱን እንዲያያዘው ማድረግ ነበር፡፡ ወዳጃችን ግን፤ ብታስሩኝ ባለ ጊዜም ባለ ብረትም ናችሁና እግሬ እምቢ ማለት አይቻለውም፡፡ ለመሰደድ ግን እሺ የሚል እግር የለኝም፡፡ ብሎ እንቅጩን ነገራቸው እና የመጣው ምጣ ብሎ ቁጭ አለ…
በነገራችን ላይ ተመስገን እስከ አሁን ድረስ በመንግስት የተሰነዘረበት ክስ ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ እንደው የሪከርድ መዝጋቢ መስሪያ ቤቶች የሚያስታውሳቸው አጥተው እንጂ ከዚህ ሁሉ ክስ ጋር አብሮ መኖር የቻለ ጋዜጠኛ ብለው ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ የሚያሰፍሩት ሁሉ ይመስለኛል፡፡ መንግስታችን በክስ ላይ ክስ ሲደራርብ ሲደራርብ ክሱ ተቆልሎ አለመናዱም የእግዜር ተዓምር ነው፡፡ አንዱ ሳይቋጭ አንዱን አንዱ ሳይቋጭ አንዱ ክስ ሲመጣ በአሁኑ ሰዓት ተመስገን ደሳለኝ ከሃምሳ በላይ ክሶች ጋር ተመስገን ብሎ እየኖረ ነው፡፡
የተሜ እና የእኛ ፍትህ ጋዜጣ “መለስ ሞቱ” በማለቷ እኛ ሳንል ምን ሲደረግ እንዲህ ትያለሽ ተብላ ከሳላሳ ሺህ ኮፒ በላይ እንድትቃጠል ተደረገች፡፡ (የመለስ አምልኮ ይሎዎታል ተመስገን…!) አንዱ ሲዘጋ በአንዱ እንከሰታለን በምትለው ስትራቴጂ መሰረት፤ አዲስ ታይምስ ተተካች፡፡ አዲስ ታይምስ ደግሞ “ብር ከየት አምጥታችሁ ነው…” ተብላ ህትመቷ ተከለከለ፡፡ መንግስታችን እንደሆነ ኮሚክ ነው ጮክ ብለን በያይነቱ ስናዝ ራሱ “ብር ከየት አምጥተው ነው” ብሎ ይጨንቀዋል፡፡ በእርሱ ቤት እርሱ አበል ያልሰጠው ሰው፤ ወይም ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ያልተበደረ ሰው ምንም ገንዘብ የለውም…!
ተመስገን እና ጓደኞቹ እጅ መስጠት ብሎ ነገር አያውቁም ነበር፤ እና ከየትም ከየትም ብለው ድጋሚ ልዕልና ጋዜጣን አበረከቱልን፡፡ መንግስት መንግስት ሆኖ እንጂ… በብስጭት ካቲካላ ይጠጣ ነበር፡፡ ግን ሳይጠጣም ሞቅ አለው፡፡ ሰከረም፡፡ እናም ልዕልናንም ጥርቅም አድርጎ ዘጋት፡፡ (ይህ ውሳኔ የሞቅታ ካልሆነ ሌላ ሊሆን አይችልም)
ተመስገን ደሳለኝ ሲናገር ሰዎቻችን ደስ አይላቸውም፡፡ እናም በተቻለ አቅም ዝም ማሰኘት ይፈልጋሉ፡፡ ልጁ ግን በቀላሉ ዝም ብሎ የሚያስደስታቸው አልነበረም፤ በማህበራዊ ድረገፆች የሚተነፍሰውን ይተነፍስ ጀመር፡፡
ኢህአዴግ ሰው እንደማትንቅ ያወኩት እኔ ምስኪኑን ሳይቀር ለመከታተል የደህንነት ሰው የመደበች ዕለት ነው፡፡ ለተመስገን ደሳለኝማ ሁሉን አቀፍ የትግል ስልት ነው የተጠቀመችበት፡፡ በእውነቱ ከሆነ፤ ለአንድ ግለሰብ ሁሉን አቀፍ የትግል ስልት መጠቀም ትልቅ የሀይል ብክነት ነው፡፡ ፍጹም ተመጣጣኝ ያልሆነ ርምጃ፤ ጎጆ ቤትን በሚሳኤል እንደ መደብደብ በሉት…
ተሜ በኢህአዴግ ክሶች ብዛት፤ በኢህአዴግ ሚዲያዎች ማስፈራራት፣ በኢህአዴግ የደህንነት ሰዎች ከበባ፣ በኢህአዴግ ማተሚያ ቤቶች አድማ አበሳውን አየ፡፡
“አንበሳው” መንግስታችን ተመስገን ግለሰብ ነው ብሎ አልናቀውም፡፡ ያለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ ሊገድበው ተንቀሳቅሷል፡፡ እርሱን ለመገደብ ያላደረገው ነገር ቢኖር ቦንድ ግዙ ብቻ አላለንም፡፡ ለአባይ የምንገዛው ቦንድ ብዙ ነገር ይገድባልና!
አሁን ተመስገን ደሳለኝ ከሜዳው ላይ ጠፍቷል፡፡ ከመንግስታችን ሃይል የተሞላበት አጨዋወት አንጻር እስከዛሬም በቃሬዛ አለመውጣቱ የሚገርም ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ሁሉ ችሎ ሜዳው ላይ ስናየው እኛ ደስ ይለን ነበር፡፡ አሁን ታድያ ሲጠፋብን ጊዜ በአዲስ መስመር ላይ ጮክ ብለን እንጮሃለን እንጂ እንደምን ዝም እንላለን…
ተመስገን ደሳለኝ ሆይ ማን ደስ ይበለው ብለህ ጠፋህ…!

No comments:

Post a Comment