No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Sunday 30 June 2013

! .... ትንሽ ስለ ጀዋር መሓመድ ......!



አንድ ጓደኛየ አንድ የተቀናበረ ቪድዮ በፌስቡክ ገፄን ለጠፈልኝ፤ እንዳነበው እየጋበዘኝ መሆኑ ነው። ቪድዮው ስለ ጀዋር ነው። ግን የሌሎች ሰዎች ስሞችም (የኔን ጨምሮ) ተጠቅሷል። ልጁ ቪድዮውን ሲጋብዘኝ አንዳንድ ዲያስፖራ ተቃዋሚዎች ስለኔ ያላቸው አመለካከት እንዳውቅና ኢህአዴግ መቃወሜን እንዳቆም 'በአሪፍ' ተፅዕኖ ማሳደሩ ነው፤ ይህን ድምዳሜ የመጣልኝ ልጁ (ቪድዮው የላከልኝ) ከዚህ በፊት ይልክልኝ በነበሩ ተመሳሳይ መልእክቶች በመነሳት ነው። ይህን የፖለቲካ ስትራተጂ እንደማይሰራ በተደጋጋሚ ለማረጋገጥ ሞክርያለሁ።

ግን ...

ሰዎች በኔ ሓሳብ ሊደሰቱ ወይ ሊናደዱ ይችላሉ፤ መደሰትም መናደድም መብታቸው ነው። እኔ ደግሞ የፈለኩትን የመፃፍ መብት አለኝ። ስለዚህ የኔ አቋም ሌሎች ሰዎች በሚሰጡኝ ምላሽ የተንጠለጠለ አይደለም።


ወደ ጀዋርና ቪድዮው ልመለስ። ቪድዮው ጀዋርና ሌሎች ሰዎች ስለተናገሩት ሓሳብ ቀነጫጭቦ ያቀርባል። በመጀመርያ ቪድዮው ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር። በኋላ ስለ ቪድዮው የተፃፉ ነገሮች ሳነብ ግን ትኩረት እንደሚያስፈገው ገባኝ።

ባጠቃላይ ሲታይ የተቀናበረውን ቪድዮ አልወደድኩትም። አንደኛ የተቀመጠው የጀዋር ሓሳብ የተቆራረጠ ነው። ለድምዳሜው የሰጣቸው ማስረጃዎች በትክክል በቪድዮው አልተካተቱም። አንድ ጥሩ የነበረ ሓሳብ ቆራርጠን በማቅረብ ጥላሸት መቀባት ይቻላል። ስለዚህ ጠቅላላው የቀረበ አመክንዮ በተፈለገው መጠን ስላልቀረበ በቪድዮን በቀረቡ የተቀነጫጨቡ ሓሳቦች መገምገም አንችልም።

ሁለተኛ በቪድዮው የቀረበው የተቀነባበረ ሓሳብ ጀዋርን ለመገምገም ያስችለናል ብለን ከተነሳን የተናገረው ነገር የልጁን ስም ለማጥፋት በቂ ምክንያት ይሆናል ወይ? የሰጠው ሓሳብ የራሱ (የግሉ) አስተያየት ነው። 'ኦሮሞዎች በደል ይደርሳቸው ነበር' ብሎ ማለት 'ኢትዮዽያን መጥላቱ' ያሳያል ወይ? የብሄር ጭቆና መኖሩ ሓሳብ መሰንዘር 'ኢትዮዽያዊ ስሜት' እንደሌለው ምክንያት ወይ ማረጋገጫ ሊሆን ይችላል ወይ?

ስለ ኢትዮዽያ ስናወራ ስለኢትዮዽያውያን እየተናገርን ነን። ኢትዮዽያውያን ህዝቦች ናቸው። ህዝቦቹም ኦሮሞዎች፣ አማራዎች፣ ትግራዮች፣ ጉራጌዎች፣ ሶማሊዎች፣ ደቡቦች፣ ጋምቤላዎች፣ ቤኑሻንጉሎች ... ወዘተ ናቸው። 'ጉራጌ ተበደለ' ሲባል ኢትዮዽያዊ እየተበደለ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ጀዋር 'ኦሮሞች ተበድለዋል' በማለቱ የተፈጠረ ችግር ምንድነው??? እንኳንም በድሮ ዘመን አሁንም እኮ 'ጭቆና አለ' ብለን እየተከራከርን ነን።

ሦስተኛ ጀዋር የሰጠው አስተያየት ጥሩ አይደለም ብለን እንነሳ፤ ታድያ ማድረግ ያለብን ጉዳይ ስም ለማጥፋት መሯሯጥ ሳይሆን አስተያየቱ ስህተት መሆኑ በሓሳብ ማሳመን መቻል ነው። በሰጠው አስተያየት ላይ የሓሳብ ክርክር መክፈት ይቻላል። አስተያየቱ 'ስህተት' ስለመሆኑ ማረጋገጥ የምንችል ከሆነ ጀዋርን ለማስተካከል እንዴት ያቅተናል?

አራተኛ አንድ ሰው የተለየ አስተያየት ስለሰጠ 'የኢትዮዽያ ጠላት' አድርጎ መፈረጅ መፍትሔ ይሆናል ወይ? ሁሉም ሰው ስለ አንድ ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም ይኖረው ዘንድ ግድ አይደለም። የምንታገለው አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን ለማድረግ ሳይሆን እንደየምርጫችን በነፃነት መኖር እንድንችል ነው።

በመጨረሻም

ጀዋር በያዘው አቋም ልዩነት ቢኖረኝም በሰጠው አስተያየት ግን አልተከፋሁም፤ ጥፋቱም አልገባኝም። የብሄር ጭቆና እንደነበር (አሁንም ችግሩ በተገቢ መንገድ እንዳልተፈታ) ከጀዋር ጋር እስማማለሁ። በአሁኑ ሰዓት (ችግሩ ለመፍታት) ምን መደረግ አለበት በሚለው (ብሄርን ከሀገር ማስቀደሙ) ግን ከጀዋር ጋር የሓሳብ ልዩነት አለኝ።

እንደኔ ከሆነ የዘመናት የፖለቲካ ችግሮቻችን መፍታት የምንችለው ታሪክን እያስታወስንና ብሄርን እያስቀደምን የሀገራችን አንድነት በሚያዳክም መልኩ በመወያየት ሳይሆን የነበረው ጭቆና እንዲወገድ አብረን በመታገልና በእኩልነትና በአንድነት የምንኖርባት ኢትዮዽያ እውን በማድረግ ይመስለኛል።

ጀዋር መሓመድ በጣም ከማደንቃቸው ብርቅዬ ወጣት ኢትዮዽያውያን የፖለቲካ ተንታኞች አንዱ ነው። ጀዋር አድናቆቴን ይድረሰህ።

በሓሳብ መለያየት ጥፋት አይደለም። ስለዚህ የሰው ስም ለማጥፋት ዘመቻ መክፈት ተገቢ አይደለም።

ኢትዮዽያችንን ይባርክልን፤ አሜን።

It is so!!!

በአብርሃ ደስታ

2 comments:

  1. አቶ አብርሃ

    ሃሳብን በሃሳብ ተከራክሮ ማሳመን የሚባል ነገር እኮ በኢትዮጵያ ፓለቲካ ዓለም ውስጥ ድሮም ኖሮ አያውቅ ዛሬም የለም::

    If you don't agree on what I say, that mean you're my enemy የሚለው logic ነው የሚሰራው

    ReplyDelete