No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Sunday, 14 April 2013

የ“አብዮታዊ ዲሚክራሲ” መንገድ የት ያደርሳል ? (በአብርሃ ደስታ)


ወቅቱ የአካባቢና ከተሞች “ምርጫ” የሚካሄድበት ነው ። ሰለ “ምርጫ” ሲታሰብ ስለ አማራጮች ማሰላሰል ግድ ነው ። አንድ ፖለቲካዊ ምርጫ ምርጫ የሚያሰኙት ነገሮች ምንድን ናቸው? ምርጫው ዲሞክራሲያዊና
የተሟላ እንዲሆን አማራጮች (ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች) መኖር አለባቸው። ምክንያቱም በምርጫ የሚመርጥ ህዝብና የሚመረጡ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች መኖር አለባቸው ። መራጩ ህዝብ በአግባቡ መምረጥ እንዲችል ለምርጫ ሰለሚቀርቡ ፓርቲዎች በቂ መረጃ ሊኖረው ይገባል።
ህዝቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው በምርጫ የሚቀርቡ ፓርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ከህዝቡ ተገናኝተው አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውና ዓላማቸው ማስተዋወቅ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ፖሊሲዎችና ዓላማዎች ለማስተዋወቅ ነፃና ገለልተኛ የግል ሚድያዎች መኖር አለባቸው። መራጩ ህዝብም በነፃነት የፈለገውን የመምረጥ መብት ሊከበርለት ይገባል።
ስለዚ በምርጫ የፖለቲካ ድርጅቶች ማቅረብ የሚጠበቅባቸው “የሚመረጡ ሰዎች” ብቻ ሳይሆን ለመመረጥ የሚያስችላቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎች ጭምር ነው ።
የኢትዮዽያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ዓፋኝ ስለመሆኑ ይነግሩናል። ኢህአዴግም በበኩሉ ተቃዋሚዎች አማራጭ ፖሊሲዎች እንደሌላቸው ያስረዳል ። ነገር ግን ተቃዋሚዎች አማራጭ ፖሊሲ ይኑራቸው አይኑራቸው “አለን” የሚሉትን ነገር ለህዝብ እንዲያቀርቡት ተፈቅዶላቸዋል ወይ? ፓሊሲ እንዳላቸው ወይ እንደሌላቸው መወሰን ያለበት መራጩ ህዝብ አይደለምን ?

የተቀዋሚዎች አማራጭ የፖሊሲ አቅጣጫ ለማወቅ እንቸገር ይሆናል። ምክንያቱም ገዢው ፓርቲ በሚፈጥረው የመረጃ ዓፈና (የግል ሚድያ ዓፈና) ፣ የፖለቲካ ሙስና ፣የኢኮኖሚ ሸበራ፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ወዘተ የተቀዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ከህዝቡ ጋር ተገኛኝተው መግባባት ተስኗቸዋል። በአንፃሩ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ኢህአደግ የመንግስትን ሃብት (ለምሳሌ የኢትዮዽያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት) ለግል ፕሮፓጋንዳ በማዋል፣ግለሰዎችን በጥቅማጥቅሞች በመደላል ፣ከምርጫ ደምብ ውጪ የራሱ ሚድያ በመጠቀም (ለምሳሌ ህወሓት ድምፂ ወያነ ሲኖረው ኢህአዴግ ደግሞ ሬድዮ ፋና አለው) ከህዝብ ጋር ያለ ገደብ የመገናኘት ዕድል አለው። ኢህአዴግ ታድያ ከህዝብ ጋር እየተገናኘ የትኛው አማራጭ ይዞ ነው የሚቀርበው ? ተቀዋሚዎች አማራጭ ፖሊሲ ከሌላቸው ኢህዴግስ ይኖረው ይሆን?
ስለ ኢህአዴግ አማራጭ አቅጣጫ ስናስብ ስለ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ማስታወሳችን አይቀርም።
“አብዮታዊ ዲሞክራሲ” የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ኦፊስየላዊ አይዲዮሎጂ (ርእዮተ ዓለም) ተደርጎ ይወሰዳል ። የአብዮታዊ ዲሞክራሲ
መንገድ የት ያደርሳል? አብዮታዊ ዲሞክራሲ መንገድ አለው? ወይስ ራሱ መንገድ ነው ?
“አብዮታዊ ዲሞክራሲ አይደዮሎጂ (ርእዮተ ዓለም) ነው” ካልን “ አይዲዮሎጂ” ምንድ ነው ? አይዲዮሎጂ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት (ወይ ድርጅቶች) የሚከተለው የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሚከተለው የፖለቲካ ኢኮኖሚ አቅጣጫ ነው ። አቅጣጫው አመክኖያዊ ቀጣይነትና
ተከታታይነት (Consistency of interrelated ideas) ባላቸው ሓሳቦች ተዘጋጅቶ ለሁሉም ዘርፎች መንገድ የሚያሳይ ነው ። የአንድ አይዲያሎጂ ዓላማ ልማት ማምጣት ነው ። ልማት የሚመዘገብባቸው መንገዶች ግን ሊያዩ ይችላሉ።
ልማት ለማምጣት የሚሳተፉ ተዋናዮች ሁለት ናቸው። መንግስትና ገበያ (State vs market) አይዲዮሎጂዎች የሚመጡ ታድያ “ልማት ለማምጣት የየትኛው ሚና (የመንግስት ወይ የገበያ) ከፍ (ወይ ዝቅ) ማለት አለበት?” ከሚል እስቤ የሚመነጩ ናቸው ። ስለዚ ልማት (ግብ)ና አይድያሎጂ (መንገድ) እስቤያቸው ፓለቲካ ኢኮኖሚ መሰረት ያደረገ ነው።
በዚ መሰረት “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” እንደ “ አይዲዩሎጂ” ወስደን እንገምግመው ።
የአብዮታዊ ዲሚክራሲ መነሻ ምንድ ነው? ማሌሊት (ማርክሲስት ሊኒኒስት ሊግ ትግራይ) ነው ። ህወሓት ተዋጊ ቡድን በነበረበት ግዜ ዝንባሌው ወደ ከሚኒስት ሀገራት ያደለ ነበር። ከሚኒስታዊ አስተሳሰብ በሀገራችን (እንዲሁም በአሁና ዓለማችን) እንደማይሰራ አያውቁም ነበር። ምክንያቱም “ ኮሚኒስት ሀገር ወይ ፓርቲ ሊኖር አይችልም።
There cannot be a “communist state or party”, because if we reach the stage of communism, there will not be state. In a communist stage, there is no private property. If there is no private property, there is no politics. If there is no politics, there is no state. If there is no state, there is no political party. Therefore, the very assumption of communist state or party is wrong. Yet, the essence of “Communist state or party” is state Capitalism.
ህወሐት ማሌሊት ሲመሰርት የግንዛቤ ችግር ነበረው ብዮ አሰባለሁኝ ። ህወሐት ስለ ርእዮተ ዓለም ሙሉ ግንዛቤ ባይኖረውም ማሌሊትን የመስረተበት ምክንያት ግን ሳይኖረው አይቀርም። ተዋጊ ቡድን እንደመሆኑ መጠን ግራ ዘመም አቅጣጫ መያዙ ግድ ይላል፣ ተራማጅ ሃይል ለመመሰረት ። በዛን ግዜ “ ማርከሲስቶች ነን “ የሚሉ State Capitalists ተራማጆች (progressive) ሲባሉ የምዕራባውያን individual capitalists ደግሞ አድሃርያን (reactionaries) በሚል ተሰይመው ነበር። ስለዚ progressive ለመሆን “ማርክሲስቶች” መሆን ሳይመርጡ አልቀረም።
ህወሓቶች ያንን የጫካ አስተሳሰብ እንደማይሰራ በከፊል የተገነዘቡ ስልጣን ከያዙ በኃላ ነው ። አሁን ሁለቱም (የማርክሲስትና የካፒታሊዝም) ፅንስ ሓሳቦች ቀላቅለው (ከግዜው ጋር አብሮ ለመጓዝ) አይዲዮሎጂያቸው “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” መሆኑ ነገሩን።
የ”አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ፅንስ ሃሳብ ምንድ ነው ? የአይድዮሎጅው social base (የሚደግፈው ወይ እንዲደግፈው የሚጠበቅ የሕብረተሰብ ክፍል) የትኛው ነው ? አንድ አይድዮሎጂ መሰፍርቱ (1) social base መታወቅ አለበት፤ (2) ድጋፍ እንዲሰጥ የሚጠበቅ የሕ/ሰብ ክፍል በአመክንዮ የተደገፈ መሆን አለበት ። (3) አይድዮሎጂውን የሚያራምድ ፓርቲ ድጋፍ የሚሰበሰበው (ወይ በምርጫ የሚያሸንፈው) ህዝብን በሓሳብ በማስመን (ከአይዲዮጂው የመነጩ ሓሳቦች) መሆን አለበት ።
በነዚህ መስፈርቶች ታድያ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ Social base ማነው ? ነጋዴው ? ከተሜው? ሰራተኛው? ባለሃብቱ?… በትክክል አይታወቅም ። በአንድ ወቅት ግን መለስ ዜናዊ “የአብዮታዊ ዲሞክራሲ Social base ገበሬው ነው” ሲለን አስታውሳለሁ ። እንደ መለስ አገላለፅ “ አብዮታዊ ዲሞክራስዊ ገበሬው ማእከል ያደረገ ነው? ፅንስ ሓሳቡን በደምብ ተነግሮናል ?
ኢህአዴግ በምርጫ ለማሸነፍ የሚጠቀመው ስትራተጂ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሓሳቦች (ideals) ለህዝብ በማስረዳት ነው? ወይስ በጭቆና ?
ኢህአዴግ በስልጣን ያለው “ አብዮታዊ ዲሞክራሲ “ በተሰኝ “ አይዲዮሎጂው” ትክክለኛነት ለህዝብ አሳምኖ፣ ህዝቡም በምክንያታዊነት ደግፎት አይደለም።
(በመጀመርያ) የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሓሳብ ምን እንደሆን በትክክል አይታወቅም (ሁለተኛ) ኢህአዴግ ስልጣን የያዘው (በስልጣን ያለው ) በህዝብ ድጋፍ ሳይሆን በሃይሉ (በጠመንጃ) ነው። (ሦስተኛ) የፓርቲው መሰረት ቤተሰባዊነት ነው፣ ሙስና ነው፣ እህል ውኃ ነው ፤አይዲዮሎጂው አይደለም ። ስለዚ “አብዮታዊ ዲሚክራሲ” እንዳ አማራጭ አይደዮሎጂ ሊወስድ አይችልም ።
አንድ የፖለቲካ ድርጅት ስልጣን ከያዘ (አይዲዮሎጂ ቢኖረውም ባይኖረውም) አንዳንድ ተግባራት ማከናወኑ አይቀርም። “ኢህአዴግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ከአብዮታዊ ዲሚክራሲ የመነጩ ናችው” ካልን እስቲ የተወሰኑ እንይ ።
በአብዮታዊ ዲሞክራሲ እሳቤ የቡደን መብት ከግል መብት ይቀድማል ። ቅድሚያ የሚሰጣቸው የኢትዩዽያ ብሄር ብሄረሰዎችና ህዝቦች ናቸው ። እነኚህ ብሄር ብሄረሰዎችና ህዝቦች ግን ሰዎች ናቸው ። ማንኛውም ብሄርና ብሄረሰብ ግለሰዎች አሉት ።
የሁሉም ህዝቦች ወይ ቡዱኖች መሰረት ግለሰብ ነው። “ብሄርና ብሄረሰዎች” የግለሰዎች ስብስብ ስሞች ናቸው ። የግለሰብ ሁለንታናዊ መብት ከተከበረ የብሄርና ብሄረሰዎች መብትም መከበሩ አይቀርም። ኢህአዴግ ግን የግለሰዎች መብት እያጣሰ የብሄረብሄረሰዎች መብት አከብራለሁ ይላል ። ስለዚ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስሕተት ነው ።
በ “ቡድን መብት” መሰረት የኢትዮዽያ ብሄር ብሄረሰዎችና ህዝቦች “የየራሳቸውን ሃብት” (በየክልላቸው) own ያደርጋሉ ። እንዲውጤቱም የአንድ ክልል ተወላጆች በሌላ ክልል (በገዛ ሀገራቸው) መኖር የመቻላቸው ተስፋ እየጨለመ ነው ። አማርኛ ተናጋሪ
ኢትዮዽውያን ከደቡብና ቬኑሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉበት (ከቀያቸው የተባረሩበት) መንገድ ከዚህ “ ቡድን መብት” ከሚል የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና የመነጫ ነው ።
የ “ቡድን መብት” አስተሳሳብ የ “ከፋፈለህ ግዛ ፓሊሲ” በመተግባር ኢትዮዽያውን እርስበርሳቸው አንድነት እንዳይኖራቸውና ገዥውን መደብ በአንድነት እንዳይቃወሙ፣ ጥቅማቸውና ደህንነታቸው እንዳያስከብሩ ለማሰናከል የታለመ ነው ። ይህን አስተሳሰብ ታድያ
የኢትዮዽያ ሀገራችን አንድነት የሚፈታተን ፣ በህዝቦች አለመተማመንና የጥላቻ ፖለቲካ እንዲሰፍን የሚያደርግ ነው። ስለዚ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ለኢትዮዽያ የሚጠቅም አይደለም ።
በአብዮታዊ ዲሞከራሲ ፍልስፍና መሰረት መሬት የመንግስት ነው ። መሬት መሸጥ ወይ መለወጥ አይፈቀድም ። መሬት እንዳይሸጥ ወይ እንዳይለወጥ የተደረገበት ምክንያት መሬት እየተሸጠ በተወሰኑ ባለሃብቶች እጅ ተካማችቶ ሌላው ድሃ ገበሬ መሬት አልባ እንዳይሆን ታስቦ ነው ። ይሄንን ሓሳብ ግን ምክንያታዊ አይደለም ።
(አንደኛ) “መሬት ይሸጥ ይለወጥ” ስለተባለ ብቻ “ ገበሬው መሬቱ ያለአግባብ ይሸጣል “ ብለን መደምደም አንችልም። ገበሬው (ይሁን ሌላ የሕብረተሰብ ክፍል) የሚያዋጣውና የማያዋጣው በደምብ ያውቃል ። ምናልባት ይሄንን ሓሳብ ከተጠራጠርን ግን መንግስት ለህዝቡ አስፈላጊው ( የመሬት ገበያ በተመለከተ) መረጃና ስልጠና መስጠት ይችላል። የገበሬው በሬ (ሊሸጥ ወይ ሊለወጥ) ስለሚችል ብቻ ሁሉም (ወይ አብዛኞች ) በሬዎች ተሸጠው በተወሰኑ ባለሃብቶች ሲሰበሰቡ አላየንም ።
(ሁለተኛ) አንድ ገበሬ መሬት ለመሸጥ ወይ ለመለወጥ የሚገደደው አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገጥመው እንጂ መሸጥ ስለሚችል ብቻ አይደለም። ለምሳሌ አንድ ገበሬ ሊታመም ይችላል። መታከምያ ገንዘብ የለዉም። የራሱ መሬት ካለው (መሸጥ ከቻለ) ግን ሽጦ ታክሞ ድኖ ሰርቶ
መሬቱን እንደገና ገዝቶ ማስመለስ ይችላል። መሬት የመንግስት ከሆነ (መሸጥ ካልቻለ) ግን ለሕክምና የሚሆን ገንዘብ ስለማይኖረው ህይወቱ ሊያጣ ይችላል።
(ሦስተኛ ) ገና ለገና ገበሬዎች መሬታቸው ሊሸጡ ይችላሉ ተብሎ መንግስት ቀምቶ ይውሰደው ? መንግስት እኮ ህዝብን የማገልገል ግዴታ እንጂ የህዝብ ሃብት (ለምሳሌ መሬት) የመውሰድ መብት የለውም ። “መሬት እንዳይሸጥ” በሚል ሰበብ ዜጎችን መሬት በግል እንዳይዙ ማድረግ ተገቢ አይደለም ።
(አራተኛ) መሬት የመንግስት እንደሆን ከተወሰነ መንግስትና ገዢው ፓርቲ በተቀላቀሉበት ሀገር መሬት የገዢው ፓርቲ ከድሬዎች መሆኑ አይቀርም ። በዚህ ምክንያት ካድሬዎች በፈለጉት ግዜ ገበሬዎችን እያፈናቀሉ መሬታቸው እየነጠቁ ለፈለጉት ሰው (ባለሃብት) ሊሰጡት
ይችላሉ ። የዜጎችን መፈናቀል ይከተላል ። በሌላ በኩል ደግሞ ለም መሬታችን ለውጭ ዜጎች በርካሽ ዋጋ ይሸነሸናል ። ከኢትዮዽያውን ይልቅ ለውጭ ዜጎች ቅድሚያ እየተሰጠ ይገኛል ።
(አምስተኛ) መሬት የመንግስት በመሆኑ ዜጎች መሬት ከመንግስት ተከራይተው (በሊዝና በፖለቲካ ታማኝነት) ሲጠቀሙ መንግስት ኪራይ እየሰበሰበ በስልጣኑ ተደላድሎ ይኖራል ። እንደውጤቱም መንግስት ኪራይ ሰብሳቢ ሁነዋል ።
“አብዮታዊ ዲሞክራሲ” የዲሞክራሲ መርሆች አሉት? ስልጣን ለህዝብ ይሰጣል ? ገዢው ፓርቲ የያዘው ስልጣን ከህዝቡ ተውሶ የተረከበው ነው ወይስ በራሱ የዘረፈው ነው? አብዮታዊ ዲሞክራሲ “ የሕግ የበላይነት ይቀበላል ?
በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሁሉም ነገር ከሕግ በታች ነው ። ሁሉም ነገር ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ይከናወናል ። የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ፍርድ ቤት ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን ዳኞች (ናሌሎች) ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ፣ የማያዳሉና በሙያው (በህግ) እውቀት ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል ። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለዚህ ዓይነት ሁኔታ ይፈቅዳል ? ወይስ ፀረ ዲሞክራሲ ነው ? በዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሕግ የበላይነት ለማስከበር ሕጉን መተርጎም ያለበት ፍርድ ቤት ነው (በአንዳንድ ሀገሮች ሌላ ዓይነት አሰራር ሊኖር ይችላል ። ዙሮ ዙሮ ሕግ ተርጓሚዎች ግን ገለልተኛ ፣ የሕግ እውቀት ያለቸው ናቸው) ።
በአብዮታዊ ዲሞክራሲ እሳቤ ግን ሕግን የመተርጎም ስልጣን የተሰጠው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ነው ። የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ግን ፖለቲከኞች ናቸው ፣ በገዢው ፓርቲ የተመረጡ የፓርቲው አባላት ናቸው ። ሕግን የመተርጎም ስልጣን ከተሰጣቸው ታድያ ፓለቲካ ከሕግ በላይ ሆነ ማለት ነው ። ፓለቲከኞች (የሕግ ሂደትን በማጣስ ) በፈለጉት መልክ ፓለቲካዊ ትርጓሚ (ውሳኔ) እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ። በዚ መሰረት ፓለቲከኖች ከሕግ በላይ ናቸው ።
ስለዚ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሕግ የበላይነት የለም ። የዜጎች ዋስትና ደግሞ ሕገ መንግስት ነው ። ስለዚ አብዮታዊ የለም ። የዜጎች ዋስትና ደግሞ ሕግ መንግስት ነው ። ስለዚ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ችግር አለበት ።
ኢህአዴግ የግብርና መር ኢንድስትሪ (ADLI) ፖሊሲ እንዳለው ይነግረናል ። ይህንን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለ 21 ዓመታት የተፈለገውን ለውጥ ሳያመጣ ቆይተዋል ። ኢህአዴግ ህዝብን ለማታላል “ጥሩ ፖሊሲ አለው ። ችግሩ ያለው አፈፃፀም ላይ ነው” ይለናል ። ግን አንድ ፖሊሲ ጥሩ ሆኖ እንዴት የአፈፃፀም ችግር ይኖረዋል ? የአፈፃፀም ችግር ያለበት ፖሊሲ እንዴት ጥሩ ፖሊሲ ሊባል ይችላል?
አንድ ፖሊሲ ከሕልም የሚለይበት ዋናው ቁምነገር አፈፃፀሙ ነው ። ፓሊሲ ካልተፈፀመ ፓሊሲ ሊባል አይችልም ፣ ምክንያቱም የማይፈፀም ከሆነ ሕልም ነው ። አንድ ፖሊሲ ወጥቶ የአፈፃፀም ችግር ካጋጠመው ፖሊሲው እንደገና መፈተሽ አለበት።
ፓሊሲ ወደ ግብ የሚወስድ መንገድ ነው ። ግቡ ልማት ማምጣት ነው ። ፓሊሲው በአሰፋልት መንገድ እንመሰለው ። “አስፋልት መንገዱ ጥሩ ነው” የምንለው በተጠበቀው መሰረት አሸከርካሪዎችን ማስተናገድ ሲችል ብቻ ነው ። (ሲፈፀም) አገልግሎት መስጠት
ካልቻለ (ተሽከርካሪዎችን ማሳለፍ ካልቻለ) ጥሩ መንገድ ነው ልንል አንችልም ። ፖሊስም እንደዛው ነው ። የአፈፃፀም ችግር ካለው ፖሊሲው ስህተት ነው ማለት ነው ። ምክንያቱም ፖሊሲ የሚወጣው እንዲፈፀም ተደርጎ መሆን አለበት ።
“አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስህተት ነው” ካልን ታድያ የኢህአዴግ አማራጭ ፓሊሲ (የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት የሚጠቀመው ሓሳብ ወይ መንገድ) ምንድነው ? ዓፈና ነው። ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ያለው ዓፈና እንደ መሳርያ አይዲዮሎጂ በመጠቀሙ ነው ። ስለዚ
የኢህአዴግ አይዲዮሎጂ አብዮታዊ ዲሞከራሲ ነው ካልን አብዮታዊ ዲሞከራሲ ገዥው ፓርቲ በስልጣን ለመቆየት የሚጠቀመው የዓፈና ስትራተጂ ነው ብንል እንሳሳትም ።
የገዠው ፓርቲ ዓላማ በሰልጣን መቆየት ነው ። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስም በሁሉም ዘርፎች ጣልቃ የመግባት ስትራተጂ ይከተላል ። ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ በኢኮኖሚው ዘርፍ ጣልቃ ሲገባ እንደሌሎች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎች ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ሳይሆን ለመቆጣጠር ነው ። ዋነኛ የሚባሉ የኢኮኖሚ ሴክተሮች በቁጥጥሩ ስር ናቸው ። በትምህርት ቤቶች ፣ በሃይማኖቶች፣ በተለያዩ የሲቪክ ማሕበራት ጣልቃ ይገባል ።
ሰለዚ ኢህአዴግ ሰላማዊ የሓሳብ አማራጭ የለውም ። አማራጩ ሃይል መጠቀም ነው ። ሰሞኑ እየተካሄደ ባለው ምርጫ ያቀረበው አማራጭም ያው በሃይል የተደገፈ ዓፈናው ነው። ዜጎችና የተቃዋሚ ፓርቲዎች በማፈን ብቻውን እየተወዳደረ ነው ። ብቻውን ሮጠ ብቻውን አሸናፊ ለመኖን ። ተወዳዳሪዎች በሌለበት “ምርጭ”ም ቢሆን ኢህአዴግ የራሱ ጥላ ማመን አልቻለም ። ምክንያቱም በሃይል ድጋፍ የሚኖር ሁሉ መሰረቱ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል ነው ።
ግን የአሁኑ ምርጫ ምርጫ ሊባል ነው ? ምርጫ ‘ምርጫ’ የሚሆነው ኣማራጮች ሲኖሩት ነው። የኣሁኑ ምርጫ ኣማራጮች ኣሉት? መራጩ ህዝብ ስለነዚህ ኣማራጮች ሙሉ መረጃ ኣለው? መረጃው የተገኘው ከነፃና ገለልተኛ ሚድያ ነው? ለመሆኑ ነፃ ሚድያ ተፈቅዷል? ህዝቡ መረጃ የማግኘት ሙሉ መብት ኣለው? ህዝቡ የሰጠው ድምፅ እንደሚከበርለት ዋስትና ኣለው? የህዝብ ድምፅ የሚያከብር ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ኣለ? ህዝቡ ከምርጫ በኋላ ምንም ዓይነት ዛቻና ኣድልዎ እንደማይደርሰው የሚተማመንባቸው ተቋማት ኣሉት? እነዚህ ጥያቄዎች በኣግባቡ መመለስ ካልቻልን በምርጫ ጣቢያ ወረፋ ይዞ መዋል ጥቅም የለውም።
****
ከኢትዮሚድያ ዝግጅት ክፍል – አብርሃ ደስታ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ አስተማሪ ነው። ከአንድ የደቡብ አፍሪቃ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የዶክትሬት ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል። ይህ የዓረና/መድረክ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል እና ወጣት ምሁር ከሌሎች ልዩ የሚያደርገው በህወሓት/ኢህአዴግ የፍርሃት እና የጭንቀት አገዛዝ እየተናጠ በሚኖረው ህብረተሰብ መሀል ውስጥ ህገመንግስቱ ላይ
ሰፍረው የሚገኙትን መብቶች ተጠቅሞ የህዝቡ “ድምጽ” ለመሆን መቻሉ ነው። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአብርሃን ጽሁፎች በጥሞና ያነቧቸዋል።
Ethiomedia.com April 13, 2013

No comments:

Post a Comment