(ይህ ጽሁፍ በአሰበ ተፈሪ ተከስቶ የነበረውን አጥማቂ ብቻ ይመለከታል)
(አንድ አድርገን ግንቦት 2 2005 ዓ.ም)፡- የዛሬ ሁለት ዓመት አንድ ሰው ከሰሜኑ ክፍል
ይነሳና የማጥመቅ ስራውን እያከናወነ ወደ ምስራቅ ክፍል ሐረር መንገድ አሰበ ተፈሪ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ አሰበ
ተፈሪ ሲደርስ የማጥመቅ ጸጋ እንዳለው ለቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ለአካባቢው ሊቀ ጳጳስ አስረድቶ ፤ የማጥመቅ
አገልግሎት እንዲሰጥ ህጋዊ ፍቃድ አግኝቶ ሰዎችን ሊያጠምቅ ስራውን በይፋ ይጀምራል፡፡ ቅዳሜ እና እሁድ ከቅዳሴ
በኋላ ስራውን ሲጀምር ለመጠመቅም ሆነ ለመመልከትም የመጡ ሰዎች እያጓሩ ፤ እየጮሁ ፤ ሌሎች እንደሚያደርጉት መውጣት
ጀመሩ ፡፡ መንፈስ ተብዬው ሲለፈልም ‹‹ሟርት ነኝ›› ፤ ‹‹መተት ነኝ›› ፤ እገሌ ነኝ ማለቱን ቀጠለ፡፡ ማነው
ያደረገብህ ? ተብሎ ሲጠየቅ ፤ የሚታዘዘው መንፈስ የደብሩን አስተዳዳሪ ፤ ቄሶችን ፤ ዲያቆናትን ፤መምህራንን ስም
መጥራት ተያያዘው ፡፡ እዛ ያለው ሰው ግራ ገባው ፤ ግማሹ ‹‹ይሄ ሰውዬ ትክክለኛ እጥማቂ አይደለም ፤ እነዚህን ዲያቆናትና ፤መምህራንን እናውቃችዋለን ንፁህ ናቸው›› ሲል ፡፡ ሌላው ክፍል ደግሞ ‹‹ያው መንፈሱ እኮ ተናገረ ፤ ከዚህ በላይ ምስክር አያሻንም›› ብለው
ስማቸው የተጠራውን ቀሳውስ ዲያቆናት ፖሊስ አስጠርተው አፍሰው እስር ቤት ከተቷቸው፡፡ ይህ ሰው መሰል ተግባሩን
በተለያዬ ቦታዎች ውስጥ እየዞረ በመስራት መሰል ነገሮች በሶስት ቤተ ክርስትያኖች ላይ ተከሰተ፡፡ ቀሳውስቱ
፤ዲያቆናቱ ሁሉም ዘብጥያ ወረዱ፡፡
ቤተ ቲያን ማን ይቀድስ? ማንስ ቀድሶ ያቁርብ? ነገሩ በጣም አስቸጋሪ ሆነ ፤ የአካባቢው ምእመንእነዚህን ቀሳውስቱንና ዲያቆናቱን ደግመን ማየት አንፈልግም ስላለ የአካባቢው ሀገረ
ስብከት አስተዳዳሪ ሊቀ ጳጳስ መንፈሱ መሰከረባቸው የተባሉትን አባቶች ወደመጡበት ማሰናበት እና አዲስ
አገልጋዮችን በማምጣት ሂደት ውስጥ ከአንድ ወር በላይ ቤተክርስትያኑ ተዘጋ ፤ አገልግሎቱም ተስተጓጎለ፡፡ ይህ
በእንዲህ እያለ ይህ ሰው ብር መሰብሰቡን ማጥመቁን የከለከለው አካል አልነበረም፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ እሱን
ለመጋበዝ እስከ 7000 ሺህ ብር ድረስ ከምዕመናን ይሰበሰብ እና ይጋበዝ ነበር፡፡ እዛው አካባቢ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በጧፍ እጥረት አገልግሎቱ ማከናወን ሲገዳደራቸው እየተመለከቱ ለአንድ ህገ ወጥ አጥማቂ ግን 7000 ብር በቀናት ጊዜ ውስጥ እንዴት መሰብሰብ እንደቻሉ ለተመለከተ ይገረማል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ ሰውየው ሌላ ቦታ ላይ ተጋብዞ ለማጥመቅ ሄደ፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ደግሞ የተከሰተው ነገር
ከአሰበ ተፈሪው የተለየ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ባልታወቀ ምክንያት ከዓመታ በፊት ተቃጥላ ነበር ፤ የአካባቢውም
ምዕመን በቻለው መጠን የበፈት ይዞታዋን ሳትለቅ እንደገና መስራት ችሎ ነበር ፡፡ ይህ ‹‹አጥማቂ›› ነኝ ባይ እዚች
ቤተ ክርስቲያን ላይ እያጠመቀ ሳለ አንዱ መንፈስ የያዘው ሰው ይነሳና መለፍለፍ ይጀምራል፡፡‹‹ቤተ ክርስቲያኗን ያቃጠላት መምህሬ እገሌ ነው›› ብሎ መሰከረ፡፡ ሰው እውነት መስሎት ያን መምህር ካልገደልነው ብሎ ተነሳ፡፡ በመሀል አንድ አባት ይነሱና እረፉ ‹‹መንፈስን ሁሉ አትመኑ›› ነው የተባለው፡፡ አንተም ማጥመቅህን አቁም ፤ ‹‹በችግር የተያዙትን እስራታቸውን እግዚአብሔር ይፍታ ስንል አንተ ደሞ ሌላ ብጥብጥ አመጣህብን›› ብለው በሰላም ሸኙት፡፡
ለቤተ ክርስትያን መቆርቆራች ባልከፋና ጥሩ ሆኖ ሳለ እንዴት እንደምናስብላት አለማወቃችን ደግሞ ሌላ ችግር
እየፈጠርን መሆኑን ተገንዝበነው አናውቅም፡፡ አሁንም የአካባቢው ሰው አቃጠለ የተባለውን መምህር ይዘው ለፖሊስ
አስረከቡ ፡፡ ፖሊስም እስኪጣራ ብሎ መምህሩን አሰረው ፤ ፖሊስ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ ስላላገኝ መምህሩን
ፈትቶ ሀገር ለቆ እንዲሄድ ያሰናብተዋል፡፡ ህዝቡም አይንህን እንዳናይህ ቤተክርስትያናችን አቃጥለህብን ብለው ‹‹አይንህ ለአፈር›› አሉት፡፡
ይህ ሁሉ እየሆነ ማስተዋል የሚችል ሰው በመጥፋቱ በሌላ ጊዜ ፤ ሌላ ቦታ ላይ ሰውየው መንፈስ ያወጣል ፤
ተዓምረኛ ነው ሲባል የሰሙ ምዕመኖች ይምጣልን ብለው የጠየቃቸውን ብር ከማህበረሰቡ ላይ ፤ ከሀላፊ አግዳሚው ላይ
መሰብሰብ ይጀምራሉ ፡፡ አሁንም የዚህ ሰውዬ ማንነት ለማወቅ ሰው አይነ ልቦናው አልበራለትም ነበር ፤ ራሱ መተተኛ
በመተት የተያዘ ሰው እፈታለሁ ፤ ከዲያቢሎስ ቁራኛነት እገላግላችዋለሁ ብሎ ማወራቱን ማጥመቁን ተያይዞታል ፡፡
አባቶች እዚህ ጋር ተሰብስበው መከሩ ፡፡ እንቢ አይመጣብ ቢሉ ‹‹የራሳችሁ ጉድ እንዳይወጣባችሁ›› ነው
ይባላሉ ፤ ይምጣ ቢሉ ደግሞ ቤተክርስትያኗን ፈትቶ ፤ ያሉትን ካህናት እንዲባረሩ አድርጎ ምዕመኑን ለሌላ እምነት
አሳልፎ ሊሰጥ ነው፡፡ ግራ የሚገባ ነገር ሆነ ፡፡ አባቶች ተሰብስበው መከሩ እንዲህም አሉ ፡- በሚቀጥለው ‹‹
እሁድ ጠዋት መምጣት ይችላል ፤ ነገር ግን እኛ ለሊቱን ሙሉ የገብርኤልን ፤ የሚካኤልን ፤ ሁሉን ድርሳናት
እንድገም ፤ ሙሉ ዳዊት ደግመን ጸሎት እናድርግ ፤ መልካ መልኮችን እናድርስ ፤ ከዛ እኛ በማኅበር ሆነን
ባደረግንበት ፀበል እሱ መጀመሪያ ይጠመቅ ፤ ከዛ እኛ ሁላችንም እንጠመቃለን ፤ ከዛ ምዕመኑን ያጠምቃለል ›› ብለው ቃለ ጉባኤ ይዘው ተፈራርመው ፤ ወስነው ስብሰባን ዘጉ፡፡
አጅሬ ለካ ምን እንደተባለ መንፈሱ ይንገረው ማን ይንገረው አልታወቀም፡፡ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በህብረት
ሆነው ቃል የገቡትን አድርገው ቢጠብቁት ቢጠብቁት ሊመጣ አልቻለም፡፡ በቃ እሺ ብለው ሌላ ቀጠሮ ያዙለት ፤ አሁንም
ሊመጣ አልቻለም ፡፡ የቀረበትን ምክንያት ሲጠይቁት ተልካሻ ነገር ነገራቸው፡፡ ይገርማል !!!! ሰዎች ቀስ እያሉ
የሰውየው ማንነት ስለገባቸው ገፍተው ከአካባቢው አባረሩት፡፡ ይህ ሰው ይህን አይነት ስራ ደቡብ አካባቢ ሲሰራ ሌባና
አጭበርባሪ መሆኑ ታውቆ በእስር ቤት እንደሚገኝ ከጊዜ በኋላ ሰማን፡፡ እኛ ይህ ሰው በአንድ ቦታ ላይ ብቻ
ያደረገውን ብቻ እናውቃለን ፤ በፊት ምን ያህል ቤተ ክርስቲያን ይበትን? ፤ አሁን ምን ይስራ? ፤ በአሁኑ ሰዓት
ምንም የምናውቀው ነገር የለም፡፡
እኛ አይናችን ታውሯል ፤ እናያለን አናስተውልም ፤ እንሰማለን አናዳምጥም ፤ በቃ እንደዚህ ነን፡፡ እነሱም
እየዞሩ ቤተ ክርስቲያን ያፈርሳሉ ፤ ቤቱን ይፈታሉ ፤ ተከታዮች ያፈራሉ ፤ በሲዲ አድርገው አቀነባብረው ለኛው
ይሸጡልናል ፤ እኛም ‹‹ይገርማል›› እያልን እናያለን፡፡ ስራቸው ሳይሆን የሚገርመው እኛ ነን የምንገርመው፡፡
የአካባቢው አባቶች ጠይቀን እንደተረዳነው ፡- ‹‹ይህው እሱ በዚያን ጊዜ አጠምቃለሁ ብሎ ውሀ
የረጨባቸው ሰዎች አሁንም ይጥላቸዋል ፤ ምን እንዳሰፈረባቸው እግዚአብሔር ይወቀው ፤ እሱ ሳይመጣ በፊት ጤነኞች
ነበሩ ፤ እሱ ካጠመቃቸው በኋላ ግን በሽታ ላይ ጥሏቸው ሄደ ፤ አንዳንዶቹ ቤተክርስትያን እየመጡ እየተጠመቁ
እየተሸላቸው ነው ፤ አንዳንዶቹ ግን አሁን በሽተኞች ናቸው›› ብለው ነበር የነገሩን ፡፡ ይህን ሲነግሩን ያለንበት ጊዜ ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን ነው የተረዳነው፡፡
በቅርብ ጊዜ ደብረ ብርሐን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አዲስ አጥማቂ መጥቷል ተብሏል.. እስኪ ነገሩን አጣርተን እንመለሳለን
source: andadirgen.org
No comments:
Post a Comment