No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Tuesday, 7 May 2013

የኢህአዴግ ባለስልጣናትን ዓለምአቀፍ ፍርድ ቤት የማቅረቡ ጉዳይ ከመለስ ሞት ጋር የሚሞት አይሆንም።

እኛ ስንስተካከል ዓለምና አቶ ኦባንግ ሜቶ የአኢጋን ዋና ስራ አስፈፃሚ የፍርድ ሚዛንዋ ወደ እኛ ያዘማሉ።


Obang Metho's interview with Tela Magazine አቶ ኦባንግ ሜቶ ይባላሉ። የስቃይ ሰለባ የሆኑና እሳቸው የሚመሩትን ድርጅት ድጋፍ ያገኙ ኢትዮጵያውያን “አባታችን“ ይሏቸዋል። እሳቸው ብዙ ሃላፊነት ያለባቸው ሰው በመሆናቸው ዛሬ አፍሪካ ነገ አውሮፓ ከነገወዲያ አሜሪካ ከዛም ኤሺያ የማይዞሩበት ዓለም የለም።ግን የትም ይሂዱ ሁል ጊዜም በራቸው ለሁሉም ዜጋ ክፍት ነው።የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ወይም አክቲቪስት ናቸው።አሁን አሁን በየትኛውም ዓለም ኢትዮጵያን አስመልክቶ በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ ግንባር ቀደም ተጋባዥ በመሆን የሚያምኑበትንና ለአገሪቱ ይጠቅማል የሚሉትን ሃሳብ ግራና ቀኝ ሳያዩ በቅንነትና በግልፅ ያቀርባሉ።በዚህ አቋማቸውም የበርካቶችን ቀልብ ለመግዛት ችለዋል አንደበተ-ርቱዕ ናቸውም ይሏቸዋል በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች- አቶ ኦባንግን።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኦባንግ ስም ካላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በማይተናነስ እንዲያውም በሚልቅ ሁኔታ ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ሰው በመሆናቸው የኢትዮጵያውያንን ብሶትና ቅሬታ በማንኛውም መድረክ ላይ ፊት ለፊት በማቅረብ ለመፍትሄ የሚሰሩ ናቸው። ምንም እንኳን እንዲህ ይሰራል መባላቸውን ውዳሴ ከንቱ አታድርጉብኝ ቢሉም እውነታውን ግን ከመግለፅ ወደ ሁዋላ ለማለት ያስቸግራል።



የጥላ መጽሔት የዚህ እትም ልዩ እንግዳ የሆኑትን አቶ ኦባንግን በተለያዩ ወቅታዊና አንገብጋቢ የአገራችን ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጠኛ መስፍን አብርሃ ከሚኖሩበት ከካናዳ አነጋግሯቸዋል።መልካም ንባብ።
ጥላ፡- ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) መቼ ተቋቋመ? ለምን ተቋቋመ? ዓላማውስ ምንድን ነው?
አቶ ኦባንግ ፡– ሰዎች ነን። በሰውነታችን ማሰብና ማከናወን የሚገባን አቢይ ጉዳይ ቢኖር በተፈጠርንበት ደረጃ ልናስብ ይገባል። በጎሳና በዘር በማሰብና በመደራጀት ላለፉት አርባ ዓመታት የፈየድነው ነገር የለም። የጎሳ አደረጃጀት ተከትለን ምንም ያተረፍነው ነገር እንደሌለ ኢትዮጵያዊያን ነጋሪ የሚያስፈልገን አይመስለኝም። ገዢ ነን የሚሉትን ጨምሮ ሁላችንንም ነጻ የሚያወጣ ህብረት ያስፈልጋል። የጋራ ንቅናቄያችን ይህንን ሃላፊነት ወስዶ የተመሰረተ የበጎ ፈቃደኞች ስብስብ ነው። የተቋቋመው በነሐሴ ወር 2000 ወይም ኦገስት 2008 ዓ ም ነው።
ጥላ፡- አኢጋን የሚንቀሳቅስባቸው አገሮች የት የት ናቸው?ተቀባይነቱስ ምን ያህል ነው?
አቶ ኦባንግ ፦ አኢጋን ድንበርና አገር የለውም። የድርጅታችን ዋናው መቀመጫ ንጹህና የሰውነት ደረጃውን አውቆ፣ ወይም ለማወቅና በዛው ደረጃው በማሰብ በሚስማሙ ወገኖች ልቡና ውስጥ ነው። ስለዚህ በሁሉም ቦታ አለን ማለት ነው። ድርጅታችንን መስርተን ወደ እንቅስቃሴ ስንገባ ዓላማችንን መዝራት ጀመርን። አሁን በቁጥር የማንገልጻቸው ለዓላማችን እየተገዙ ነው። ምርቱን በመሰብሰብ ላይ ነን። በተለያዩ መድረኮች የአኢጋን መርህ እየተሰበከ ነው “ሁላችም ነጻ ካልወጣን ማንም ነጻ ሊወጣ አይችልም” በሚል መሪ ቃል የመመራትና አቋምን የማስተካከል ዝንባሌ ባደባባይ እየሰማን ነው። ይህ ታላቁ ስኬታችን ነው።
ጥላ፡- “ሁላችንም ነፃ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነፃ ሊሆን አይችልም“ የሚል መፈክር ያነገባችሁት ለምንድን ነው?ከማ ነው ነፃ የምንወጣው?እንዴትስ ነው ነፃ መውጣት የሚቻለው?
አቶ ኦባንግ ፦ መፈክራችን መቅደም ያለበትን የሚያመለክት ነው። ለሰው ልጅ ቀዳሚው ነገር በሰውነት ደረጃ ማሰብ መቻሉ ነው። ሰዎች በተፈጠሩበት ውድ ስብዕናቸው ሊኖሩና በዛው መጠን ሊያስቡ ይገባል። ከጎሳቸውና ከዘራቸው በላይ ሰውነታቸው ወይም ሰው መሆናቸው ትልቅ ነገር ነው። ሁሉም ነገር ከሰውነታቸው በታች ነው። ለምሳሌ አንድ መኪና ለገዛ ሰው መኪናው የሱ ለመሆኗ በሱ ስም የተዘጋጀ የባለቤትነት መታወቂያ ይሰጠዋል። የመኪናዋ ባለቤት እሱ በመሆኑ መኪናዋ “የአቶ እገሌ መኪና” ተብላ ትጠራለች። ይህ ትክክለኛው አግባብ ነው። ማንም ሰው በገዛው መኪና አይጠራም። መኪናዋ የባለቤቷ መጠሪያ ወይም የገዛት ሰው የበላይ አትሆንም። ስለዚህ ከትልቁ ነገር ይልቅ ትንሹን ነገር መምረጥ ትክክለኛ አይሆንም። መቅደም ያለበት ሰውነት ወይም ሰው መሆን ነው የምንለው ለዚህ ነው። ሰውነትን አስቀድሞ በሰውነት ደረጃ ማሰብ ትልቅነትም ነው። በሰው ደረጃ ተመጥኖ ማሰብ ከሌሎቹ ካልጠቀሙን አስተሳሰቦች ሁሉ የበላይ ስለመሆናችን ማረጋገጫ ይሆናል።
ጥላ፦ ሰብዓዊነት ከምንም ነገር ጋር ሊወዳደር የሚችል ጉዳይ አይደለም።ጎሳ የሚለው አባባል በስህተት ወይም በግድ ጎሰኝነቱን የተቀላቀሉትን ወገኖች አያስኮርፍም ወይ?ድርጅታችሁ የመላው ኢትዮጵያዊ ድርጅት እንደመሆኑ እነዚህን ወገኖች አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ በማድረግ አኢጋንን እንዲደግፉ ማድረግ አይቻልም ነበር?
አቶ ኦባንግ ፦ አስቀድሜ የገለጽኩት ይመስለኛል። በጎሳ ተደራጅተን ምን አተረፍን? በጎሳ ተቧድነን ምን አተረፍን? በጎሳና በዘር ተሰባስበን ምን ተጠቀምን? ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚችሉ በርካታ ወገኖች አሉ። ውጤቱ በደንብ የታየና ሊካሄድ በማይችል ደረጃ ማስረጃ የሚቀርብበት ነው። እንግዲህ ከዚህ ውጤት አልባ የድርጅት አዙሪት እንውጣ ማለት ምን ክፋት አለው? ለምንስ ቅሬታ ይፈጥራል? በሰውነት ደረጃ በማሰብ፣ ሰብአዊነትን በማስቀደም ብንሰባሰብ ቢያንስ ራሳችን በራሳችን ወገን ላይ የምንፈጽመውን በደልና ግፍ እናቆማለን።
የርስ በርስ መከባበርና ተረዳድቶ መኖርን በተፈጠርንበት ውድ ደረጃችን ጋር በማጣጣም ካከናወነው እናተርፋለን። ስለዚህ ከጎሰኛነት አስተሳሰብ መላቀቅ ግድ ነው። ወደ ሰውነት መሸጋገር!!
ጥላ፡- “ቅድሚያ ለሰብዓዊነት“ ብቻ ቢባል ሁሉንም ያሳትፋል።የተሳሳተውንም ያርማል ብለን እንደ ጥላ መጽሄት እናምናለን።ምን አስተያየት አሎት?
አቶ ኦባንግ፦ ትክክል ናችሁ ብዬ አምናለሁ። ከናንተና እናንተን ከመሳሰሉ የሚዲያ አካልትም ብዙ ስራ ይጠበቃል። አገርን ማዳን የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነ ያለ አንዳች ወገናዊነት አምኖ ማሳመን የሚዲያው ፈንታ ነው።
ጥላ፡- እስራኤልና ኖርዌይ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ከችግር ለማላቀቅ ያከናወናችሁዋቸው ተግባራት ምን ውጤት አስገኙ?ኢትዮጵያውያኑንስ በአስገዳጅ ወደ አገራቸው ከመመለስ ታደጋችሁዋቸው ወይ?
አቶ ኦባንግ፦ ከዚህ ቀደም ጎልጉል በሚባል የድረ ገጽ ጋዜጣ ላይ በዝርዝር ተናግሬያለሁ። የአኢጋን ቤተሰቦች በዚህ ረገድ ብዙ ሰርተናል። በየጊዜው የሰራነውን ብንናገር ሚዲያ ማጨናነቅ ይሆናል። እኛም አንፈልገውም። ይህንን ስል ግን በቂ ስራ ሰርተናል ለማለት አልደፍርም። ውስን አቅም ቢኖረንም ከችግሩ አንጻር መስራት የሚገባንን ያህል አልሰራንም። አንድ መታወቅ ያለበት እውነት አለ። ስራው አድካሚና በርካታ ደጆችን ማንኳኳት የሚጠይቅ ነው። በተጠቀሱት አገሮች የሚኖሩትን ወገኖች ጉዳይ ለአፍታም የምንዘነጋው አይደለም። ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላት ጋር እየሰራን ነው። መፍትሄም ያገኙ ወገኖች አሉ። በዋናነት ግን መታሰብ ያለበት ነገር የስደት ፈቃድ ስለማግኘት ሳይሆን አገራችን ላይ ተከብረን የምንኖርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ሁሉም እልህ አስጨራሽ ትግል ይጠይቃል።
ጥላ፡- በኬንያና በአውሮፓዊቷ ማልታም በስደት የሚሰቃዩና ለእስር የተዳረጉ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።እነዚህን ወገኖቻችንን ከስቃይ ለመታደግ ምን የታሰበ ነገር አለ?
አቶ ኦባንግ፦ ተመሳሳይ ጉዳይ ነው። በተመሳሳይ እየሰራንበት ነው። ለጊዜው ቁጥራቸውን በውል የማላውቃቸው ሰዎች ነጻ እንዲሆኑ አድርገናል።
ጥላ፡- ከስደት ውጪ በስራ ምክንያት ከአገር ወጥተው በተለያዩ አረብ አገራት አሳረ መከራቸውን እያዩ የሚገኙትን እህቶቻችንን እንባ ለማበስስ አኢጋን ምን አስቧል?በተለይ እርሶ ያሎትን ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ተጠቅመው ምን ለማድረግ ተዘጋጅተዋል?
አቶ ኦባንግ ፦ እጅግ ረፍት የሚነሳ ጉዳይ ነው። አንድ አገር እመራለሁ የሚል መንግስት ዜጎቹን መጠበቅና መብታቸውን ማስከበር ሲያቅተው መመልክት ያሳዝናል። አንድ ዜጋ አድኑኝ ብላ ኤምባሲ በር ላይ ስትደርስ በር ዘግቶ ጀርባ መስጠት በየትኛውም መስፈርት የሰውነት ደረጃንና ሰው የመሆንን መስፈርት ያጎድለዋል። በዚህ በኩል ያለው ችግር ስፍር ቁጥር የለውም። አስቀድሜ እንደገለጽኩት የበኩላችንን እያደረግን ነው። ችግር አለ በተባለበት ቦታ ሁሉ ለመድረስ እንጥራለን። በዚህም መላው የአኢጋን ቤተሰቦች ደስተኞች ናቸው። ለጊዜው በዝርዝር መግለጽ ባልችልም ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ማህበራት ጋር እንዲሁም ሴቶች ጉዳይን በሃላፊነት ለመከታተል በቅርቡ ከተቋቋሙ እህቶቻችን ጋር ለመስራት ሃሳብ አለን። ጅማሬው ጥሩ ይመስላል።
ጥላ፡- አገሪቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለማስረዳት በበርካታ መድረኮች ተገኝተው ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ይታወቃል።በጀርመንም የ2012 ምርጥ ሰው ተደርገው ተመርጠዋል።ጥረቶ ምን ውጤት እያመጣ ይገኛል?
አቶ ኦባንግ፦ በደፈናው ምርጥ ሰው ነኝ ብዬ አስቤ አላውቅም። እኔ የምመራው ድርጅት ዓላማና መርህ ግን አማራጭ የሌለው መንገድ በመሆኑ “የተመረጠ” መርህ እንደሆነ አምናለሁ። ክብሩና ምርጥነቱ የመነጨው ወይም መነሻው የድርጅቱ ዓላማ ከሆነ ደስታው ለመላው የአኢጋን ቤተሰቦችና የዓላማው አፍቃሪዎች በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ። ለአገራችን የተወሳሰበ ችግር መፍትሄ ነው ለምንለው መርህ ለተሰጠው ክብር ደግሞ መራጮቹን አመሰግናለሁ። ከዚህ በተለየ የምለው የለም። ሃሳቡን ያመጡትና ከድምዳሜ የደረሱት ወገኖች ቢጠየቁና ምላሻቸውን ቢሰጡ የተሻለ ይሆናል። በግሌ አንድ የማልስማማበት ጉዳይ አለ። እኔ አንድ ግለሰብ ነኝ። ደጋግሜ ቤተሰብ እያልኩ የምጠራው የአኢጋን ስራ አመራር ከሚወስነውና ከሚያወጣው መርሃ ግብር ውጪ በግሌ የማደርገው ነገር የለም። ግለሰብ ላይ የተንጠለጠለን ሙገሳና ውዳሴ ብዙም አልወደውም። አስቦ፣ አልሞ፣ መዝኖና ፣በሰከነ አእምሮ መርምሮ መራመድ ያስደስተኛል። ከምንም በላይ ምክንያታዊ መሆን የተፈጠርንበት ደረጃ መለኪያ እንደሆነ ይሰማኛል። አኢጋን ውስጥ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የተለመደ ነው።
ጥላ፡- የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮችን በጦር ወንጀለኝነት ለመክሰስ የሚያስችል ማስረጃ/መረጃ አቅርባችሁዋል።ግን እስካሁን ያየነው ነገር የለም::ምክንያቱ ምንድን ነው?ያቀረባችሁዋቸው መረጃዎች ማስረጃ መሆን አልቻሉም ወይስ ሌላ ችግር አለ?
አቶ ኦባንግ፦ በችኮላና እኛ በምንፈልገው ፍጥነት የሚሆን ነገር የለም። ስንቸኩል የያዝነውንም እናጣለን። ኢህአዴግንና ተባባሪዎቹን በፈጸሙት ወንጀል መነሻ ከሶ ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ የመረጃ ችግር የለብንም። አንድ ምሳሌ ላንሳ። የሱዳን ፕሬዚዳንት አልበሽር በጦር ወንጀለኛነት እስር ተፈርዶባቸዋል። እስካሁን ግን ያሰራቸው የለም። ብዙ የተወሳሰቡ ጉዳዮች አሉ። ብዙ ጉዳዮች በጊዜ ምላሽ ያገኛሉ። አቶ መለስን በዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ከሰናል። ፋይላቸው ተከፍቶ እንዲከሰሱ ከውሳኔ ተደርሶ ነበር። በመካከሉ ሞቱ። ከሞት ቀስቅሰን የክሱ ሂደት ይቀጥል ማለት ራሱን የቻለ ሌላ ጉዳይ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ታዛዦችም መከሰስ አለባቸው። መለስ ቢሞቱ የተቀሩት አሉ። ጉዳዩን ወደዛ ቀይረን እየሰራን ነው። አሁን በዝርዝር ለመናገር ቢችግረኝም አሁን በስልጣን ላይ ያሉትን ወንጀለኞች ህግ ፊት ለማቅረብ የመረጃ ችግር እንደሌለ ላረጋግጥልህ እወዳለሁ። እንዳልኩት ጊዜ የሚወስድ ሥራ ነው፡፡
ጥላ፡- በአንፃሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት በቅርቡ ኢህአዴግ የሚመራት ኢትዮጵያን በአመራር ቦታ እንድትገባ መርጧታል።አለ የምንለው ችግር በእውነት ስለሌለ ነው
ወይስ እኛ አለ የምንለውን ችግር ማሳየት ስላቃተን ነው?
አቶ ኦባንግ፦ አየህ ልዩነታችን እዚህ ላይ ነው። እነሱ ላመኑበት ዓላማ ሌት ተቀን ይሰራሉ። እኛ ገና ከራሳችን ጋር አልታረቅንም። እንደውም የነሱን የጎሳና የብሄር አዝማች እያስተጋባን ራሳችንን ለበለጠ ሽንፈትና ለተስፋ መቁረጥ እናመቻቻለን። እነሱ የህልውና ጉዳይ ብለው ሃይላቸውን አስተባብረው ይታገላሉ። እኛ በተቃራኒው እንባላለን፤ እርስበርስ እንጣላለን። ለምንና እንዴት እንደምንደራጅ እንኳ በወጉ ያልተረዳን አለን። አሁን ለመቀየር የተነሳነው እንዲህ ያለውን አክሳሪ አስተሳሰብ ነው። ከስሜት የጸዳ አስተዋይነት የተሞላው ትግል ማካሄድ ግድ ነው። መስፈሪያችንን ማወቅ አማራጭ የለውም። እኛ ስንስተካከል ዓለምና የፍርድ ሚዛንዋ ወደ እኛ ያዘማሉ። የዚያኔ የተባበሩት መንግስታትም ሆነ የፍትህ አካሎችና ፍትህ አቀናባሪዎች አንቀጽ ይጠቅሱልናል። አሁን በርካታ ጉዳዮች አፋፍ ላይ ናቸው። ተጠናክሮ መቀጠል ነው።
ጥላ፡- በኢህአዴግ መራሹ መንግስት ተጠንስሶ እንደ እናንተ አይነት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አስመልክቶ በወጣው ሕግ ላይ ድርጅታችሁ ምን አስተያየት አለው?
አቶ ኦባንግ፦ ይህ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው። እኛም አቋማችንን አሳውቀናል።ኢህአዴግ ህግ እየጠቀሰ ዜጎችን ማፈን ልዩ ባህሪው ነው። እንደፈለገው የሚተረጉመው ህግ በማውጣት፣ እንዳሻው የሚፈርዱለት ፈራጆች በማሰማራት ህግን ከፊት አደርጎ ዜጎችን፣ ማህበራትን፣ ድርጅቶችን፣ ሲቪክ ተቋማትን፣ ባለሙያዎችን፣ አገራቸውን የሚወዱትን……. ወህኒ ወርውሯል። እየወረወረ ነው። የአገዛዙ አንዱና ክፉ መገለጫው እንደሆነ የሚታወቅ ነው።
ጥላ፡- የእናንተን አይነት ድርጅቶች እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅና ገለልተኛ የሲቪክ ማህበራት እንዲጠናከሩ ለማስቻል ከነፃው ፕሬስ ምን ይጠበቃል?
አቶ ኦባንግ፦ አሁን ያሉት ሚዲያዎች አገዛዙን በተለያየ መንገድ ለሚቃወሙ ድርጅቶችና ፓርቲዎች ብሎም ግለሰቦች በመወገን የሚዘግቡ ናቸው። ሚዲያዎቹ መረጃ ከማስተላለፍ ጀምሮ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እጅግ ዋጋ ያለው እንደሆነ ይሰማኛል። እንደ ድርጅታችን እምነት ከሆነ ሚዲያዎች አሁን ካላቸው አስተዋጽኦ በላይ ማደግ ይገባቸዋል። የመስማማት አቋም በማራመድ ብቻ አገርና ህዝብን መጥቀም አይቻልም። የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን መሞገት አለባቸው። መከራከርና መመርመር አለባቸው። የተቃዋሚ ፓርቲዎችን መገሰጽ አለባቸው። መፈታተን አለባቸው። መከራከርና መመርመር አለባቸው። ጋዜጠኛነት ሙያው እንደሚያዘው የመስማማትና የመቀበል ጉዳይ አይደለም። ለምሳሌ እኔን አንድም ጊዜ አንድም ሚዲያ ተከራክሮ ጠይቆኝ አያውቅም። ለምን? ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ በተለያዩ ደረጃዎች የምንገኝ አካላት አንዳንዴ እንኳ ቢሆን ልንፈተን ይገባልና ሚዲያዎች ከዚህ አንጻር የጋዜጠኛ ስራ ስለመስራታቸው ራሳቸውን ሊመረምሩ ይገባል።
ጥላ፦ በቅርቡ የመሬት ነጠቃን አስመልክቶ በዩኤስ ኮንግረስ ላይ ባልተለመደ ሁኔታ ሃይለቃል መጠቀምዎ ተሰምቷል።ለምን?
አቶ ኦባንግ፦ በፍጹም። የመከራከሪያዬን ሃሳብ ከተከራካሪው ሰው ከፍ በማድረግ መናገሬን አስታውሳለሁ።
ጥላ፦ ስለመሬት ነጠቃ እርስዎ ያቀረቡትን ጉዳይ የተቃወሙት የህወሃት ሰው ናቸው?
አቶ ኦባንግ፦ ነገሩ እንዲህ ነው። በዩኤስ ኮንግረንስ ስለ መሬት ነጠቃ ያቀረብኩትን ንግግር አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የመጡ አንድ የአገዛዙ ሰው “የምታወሩት ሁሉ ውሸት ነው። ሰዎችን ወደ ስህተት ጎዳና እየመራችሁ ነው” በማለት ሃቀኛ ለመሆን ሞክረው ተናገሩ። እኔ መልስ የመስጠት እድል አገኘሁና ባለስልጣኑ ሊያስተባብሉ በማይችሉበት ሁኔታ መለስኩላቸው። የምንናገረው እውነት እንደሆነ አስረግጬ አስረዳሁ። የመከራከሪያዬን ጭብጥ ሰውየው ከተናገሩበት ደረጃ በማሳደግ ክፉ ቃል ሳልጠቀም እሳቸውን ጭምር ነጻ ለማውጣት እንደምንሰራ ነገርኩዋቸው። ይኸው ነው። ዘለፋ የለም። ዘለፋ አልወድም። በመዛለፍ አላምንም። የምትናገረው ነገር ማሳመኛ ነጥብ አለውና የገዘፈ መሟገቻ ከታከለበት በንግግሩ ውስጥ ያለው የእውነት ሃይል ከስድብ በላይ ሊሆን ይችላል። እነሱ ቢጠሉንም እኛ ግን ከቂምና ከበቀል ርቀን እነሱን ነጻ እስከማውጣት ድረስ እንደምናስብ ስንነግራቸው ይዞርባቸዋል። እውነት መሆኑን ለመቀበል ያዳግታቸዋል። የኖሩበት የፖለቲካ ሰፈር፣ ያደጉበት የመተላለቅ መንገድና የተመረቁበት የጭካኔ መንፈስ ይህን አይነቱን ለሰብአዊነት ቅድሚያ የሰጠ የመረዳዳትና ራስን ከፍ አድርጎ በእኩልነት የማኖር ስርዓት ስለማያውቁ ግራ ይጋባሉ። ማስተማርና ሰዎችን ወደ ሰውነት ደረጃ ከፍ ማድረግ አድካሚ ስራ ነው የምለው ለዚህ ነው።
ጥላ፦ እና ሃይለ ቃል ጠቃሚ አይደለም እያሉ ነው?
አቶ ኦባንግ፦ አዎ! ምን ያደርጋል። እንግሊዞች “use soft words and hard argument” የሚሉት አባባል አለቸው። በጨዋ ቋንቋ ጠንካራ መከራከሪያ በማቅረብ መልዕክት ማስተላለፍ ይቻላል። ዘለፋ ከሰውነት ደረጃ የመውረድ ያህል ይሆንብኛል። እኔ ጠላት አለኝ ብዬ አላስብም። የቆምንበት ኣላማም ለዘለፋ እውቅና አይሰጥም። በዘለፋ ለውጥ ማምጣትና ማሸነፍ አይቻልም።
ጥላ፡- አቶ ኦባንግ ለፍፁም ቅንነቶና ተባባሪነቶ የጥላ መጽሄት ዝግጅት ክፍል ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።
አቶ ኦባንግ፡- እኔም ለተሰጠኝ ዕድል ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡
source:http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/7624

No comments:

Post a Comment