No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Saturday 4 May 2013

አሁንም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአፋጣኝ እንዲፈቱ እንጠይቃለን! (አንድነት)

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
Unity for Democracy and Justice (UDJ) partyፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በሰላማዊና ህጋዊ የትግል መንገድ ለውጥ ማምጣት ይቻላላል፤ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንፈጥራለን፤ ስልጣንም በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ይሁንታ የሚገኝ ሳይሆን በህዝቡ በልካም ፈቃድ ይሆናል የሚል ጠንካራ እምነት በመያዝ ከአምባገነኑ ስርዓት ጋር እየታገለ የሚገኝ ነው፡፡
ይሄ ጠንካራ የትግል መነሳሳታችን እና ያለን  የህዝብ ድጋፍ ጠንካራ ተቃዋሚ በዓይኑ ማየት የማይፈልገው ገዥ ፓርቲ ጥርስ ውስጥ የከተተን በምስረታችን ማግስት ጀምሮ ነው፡፡ በርካታ አባሎቻችንንና አመራሮቻችንን ተልካሻ ምክንያት እየተለጠፈባቸው ታስረዋል፣ ተሳድደዋል፣ ተደብደበዋል፡፡
በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ጠንካራ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችና ተቃውሞዎች ሁሉ የሚሰጣቸው ስም ሽብርተኝነት የሚል ነው፡፡ የስርዓቱ የስልጣን ማቆያ፣ የሀቀኛ ተቀናቃኞችና ስርዓቱን የሚተቹ ጋዜጠኞች ማሸማቀቂያ ብሎም ማስወገጃ መሳሪያ ሽብርተኝነት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
ፓርቲያችን አንድነትም ጠኋትና ማታ እየተጠቀሰ ዜጎች እንዲሸማቀቁ የሚደረግበትና የፖለቲካ አመራሮች የሚታሰሩበት
የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም የፀረ ሽብር ህጉ ገና ረቂቅ አዋጅ እንደነበረ ለማፈን እየተሰናዳ መሆኑን በመጥቀስ ‹‹የፀረ-ሽብርተኝነት ረቂቅ አዋጅ በዜጎች ላይ ሽብር ፈጣሪ ነው›› በሚል ርዕስ ባወጣነው መግለጫችን ረቂቅ አዋጁ እንዳይፀድቅ የሚሰማ ባይኖርም አበክረን ጩኸታችንን አሰምተን ነበር፡፡
ወዲያው ህግ ሆኖ እንደወጣም የፀረ ሽብርተኝነት ትግልን ሽፋን በማደረግ የገዥው ፓርቲ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማፈን ድብቅ ፍላጎት ተግባራዊ መሆን ጀመረ፡፡ የመጀመሪያው ሰለባ አንድነት ፓርቲ ነው ብንል ማጋነን አይደለም፡፡ አንዱአለም አራጌንና ናትናኤል መኮነንን የመሰሉ ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮችንና ሌሎችን የፓርቲያችን አባሎች በእስር አጥተናል፡፡ እነዚህ በማናለብኝነት የሚፈፀሙ የገዥው ፓርቲ ሸፍጦች ትግላችንን የበለጠ የሚያጠናክሩና አፈናውን ለመስበር ጉልበት የሚሆኑን ናቸው እንጂ አንገታችንን አያስደፉንም፡፡ የፍትህ ተቋማት ላይ እምነት መጥፋቱ፣ ከላይ እስከታች ያለው የአፈና ቋንቋ ተመሳሳይ መሆኑና የገዥው ፓርቲ እጅ መርዘም ትግሉን ማፋፋምና አጠናክሮ መቀጠል ዋና መፍትሄ እንደሆነ የሚጠቁመን ነው፡፡
ሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ይግባኝ ሰሚ ችሎት በነ አንዷለም አራጌ ፍርድ ላይ በአንድ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል የአንዱን ጥቂት ዓመታት ከመቀነስ ባለፈ የስረኛውን ፍ/ቤት ውሳኔ ትክክል ነው ብሏል፡፡ ይሄ ፍርድ የሚያስታውሰን የኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን ሊሚትድ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ይፋ ያደረገውን ጥናት ነው፡፡ በ27 የመንግስት ተቋማት ላይ በተደረገ ጥናት ‹‹በከፍተኛ ደረጃ የህዝብ አመኔታ ያጡ ተቋማት›› በሚል ርዕስ ስር በመጀመሪያ ደረጃ የተቀመጡት ፍ/ቤቶች ናቸው፡፡ ይሄ የሚያሳየው ፍ/ቤቶች የገዥው ፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚዎች እንጅ ገለልተኛ ተቋማት አለመሆናቸውን ነው፡፡
ከፍተኛው ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ወጣቱን ፖለቲከኛና ከፍተኛ አመራር አንዱአለም አራጌና ናትናኤል መኮንን ሽብርተኞች እንደሆኑና በሰላማዊ ትግል ሽፋን ሽብርተኝነትን እንሚያራምዱ ተደርጎ የቀረበው ሀተታ የፓርቲያችንን ጠንካራ መዋቅር ያላገናዘበ፣ የፓርቲያችንን መልካም ስም የሚያጎድፍ ነው፡፡ እነ አንዷለምም ሰላማዊ ታጋዮች እንጅ ሽብርተኞች አይደሉም፡፡ ሽብርተኝነት በኮሃራም ናይጀሪያ፣ በፓኪስታንና አፍጋኒስታን በየዕለቱ የምንሰማው እንጅ የኢትዮጵያ ችግር አይደለም፡፡
በአጠቃላይም የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የኢህአዴግ የዕድሜ ማራዘሚያና መጠቀሚያ ከመሆን በዘለለ ፋይዳ አለው ብለን አናምንም፡፡ የአመራሮቻችንንና አባሎቻችንን መታሰር አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንለው በሽብርተኝነት ስም ዜጎችን ማሰር ይቁም፤ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሽብርተኝነት አይደለም፤ የፖለቲካና የህሊና እስረኞ በአስቸኳይ ይፈቱ፡፡
ትግላችን እስከለውጥ ድረስ ይቀጥላል!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት)
ሚያዝያ 25 ቀን 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment