No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Thursday 2 May 2013

የመጨረሻው መጨረሻ ጥላሁን ከስዊዘርላንድ

አብዮት በእያንዳንዱ ብሶተኛ ልብ ውስጥ ተፀንሶ በጋራ ይወለዳል፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ስር-ነቀል አብዮት ሊፈጥሩ የሚችሉ ተጨባጭና መሬት የያዙ ምክንያቶች አሉ፣ ስር-ነቀል—እደግመዋለሁ—ስር-ነቀል—አብዮት በኢትዮጵያ እንደማይታሰብ የወያኔ ጭፍራዎች ሲለፍፉ ቆይቶአል በመሆኑም እነሱ ባሰመሩት መስመር ብቻ ተከበን በፈቀዱልን ክበብ ብቻ ተወስነን በጉንጭ አልፋ ክርክሮችና ንትርኮች ተወጥረን በትናንሽ ሃሳቦች ላይ ከትናንሽ ካድሬዎቻቸው ጋር ስንሻኮት ከሕዝብና ከሀገር በልብም በአስተሳሰብም በአካልም ተደብቀው የሚገኙት የህወሓት(ወያኔ) መሀንዲሶች ባሻቸው ሰዓትና ቀን ከመጋረጃው ጀርባ ተደብቀው የጥፋት መርዛቸውን ከመጋረጃው ጀርባ ተደብቀው እየረጩ ሲያሻቸው የዘረኝነት መርዝ፣ ሲላቸው የሃይማኖት ጂሃድ ለማቀጣጠል የሚያስችል “ጅሃዳዊ ሐረካት” የመሰለ መርዝ፣ የኢትዮጵያዊነት ማንነትን በማጥፋት በትናንሽ ጎጠኝነት ጥንባት በማጀል ከዚህ የጎጠኝነት ክበብ እንዳንወጣ የጥፋት ሰንሰለቱን በዚህ ልክ በማጠር፣ በተሳከረ የኢኮኖሚ ፍልስፍናና ያሻቸውን ቁጥር እየመዘዙ 11 በመቶ አድገናል፣ 20 በመቶ የኑሮውን ውጣ ውረድ(ግሽበት) ቀንሰናል፣ የተራበው 12ሚሊዮን ሳይሆን 7ሚሊዮን ነው፣ የተፈናቀለው አማራ ብቻ ሳይሆን ኦሮሞም አለበት፣ ምናምን—ምናምን—እያሉ እነሱ በሚመዙልን ርዕሰ-ጉዳይ ብቻ ተጠምደን የእሳት ማጥፋት የጉንጭ ማልፋት ሥራ የምንሰራበት፣ እነሱ የሚሰጡንን የቤትስራ ተቀብለን የምንጨናበስበት ጊዜ የጨለመ ይመስላል።


ህዝቡ በጋራም ይሁን በነጠላ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እምቢ እያለ ነው—ይሄ ግለሰባዊ እንቢተኝነትና ብሶት ነው እንግዲህ አብዮትን ፀንሶ ይሄ የእንቢባዮች ህብረት ደግሞ አብዮትን የሚወልደው—ከላይ እንደጠቀስኩት አሁን ለስር-ነቀል አብዮት ፍሬ የቁዋጠሩ ምክንያቶች ከበቂ በላይ ተፈጥረዋል፣ ሁሉም በየቦታው አሻፈረኝ እያለ፣ ከአሽከር ካድሬዎች ጀምሮ እስከመጋረጃው ጀርባ መርዛም እባቦች ድረስ ከእምቢባይነት ባሻገር መርዛቸውን ለመርጨትና ከሀገር ወጥተው በአባይ ስም አቁማዳ ስልቻ ይዘው ለመለመን የመጡትን እባቦች(ቴዎድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ) አደግዳጊ አሽከር ካድሬዎችን እያሳፈረ በጉዋሮ ተደብቀው እንዲወጡ እያስገደዳቸው ይገኛል።
አሁን አብዮቱ ያመረረ ይመስላል፣ አረ እንደውም ከሮአል—ከሀገር ውስጥ እስከውጪ፣ ከባለራእይ ወጣቶች እስከ ኖርዌይና ስታቫንገር ወጣቶች፣ ከሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም 33ቱ ፈራሚ ፓርቲዎች እስከ ግንቦት 7፣ ከሊቅ እስከደቂቅ፣ አረጋውያንም ሳይቀሩ አሁንስ መረረን አያሉ ነው። ሰሞኑን በያዝነው ሚያዚያ ወር ብቻ ብሶተኛና አብዮተኛ ሕዝብ ከሁዋላቸው ያስከተሉ ፓርቲዎች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች ከያሉበት አሁንስ በቃን በዛብን ብለው አምርረው ሲናገሩ ሰማሁ፣ አዎ—አዎ—አዎ—በዛ፣ እኔም እደግመዋለሁ ግፉ በዛብን፣ ጭቆናው በዛብን፣ ዘረኝነቱ በዛብን፣ እንዴ—??? አላልቅ አለኮ መከራችን።
ጥቂት የኢትዮጵያ ሁኔታ ያሳሰባቸው አርቆ አሳቢ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና፣ የሰብአዊ-መብት ታጋዮች መፃኢ ሃገራዊ ትንቢት ሲናገሩና የትንቢቱ መፈፀሚያ አዋጅ ነጋሪ ነቢያት የሆኑት እኒህ ምሁራን በደማ፣ በቆሰለና፣ ባመረቀዘ ልብ ሳግ በተናነቀው እልህና የውርደትን ዘመን ለመፈፀም ባቀደ ቁርጠኝነት በዚህ በያዝነው ወር ብቻ የተናገሩትን ጥቂቱን እንመልከት።
1-”የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሆናችሁ በሀገር ውስጥ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሀገራችን ከገባችበት ፈተና፣ ህዝባችን ከሚደርስበት ስቃይ ልናላቅቀው የምንችለው ከያዘን የፍርሃት ቆፈን ተላቀን በአንድነት በመቆም ወደተማሰው መቃብር ጉድጉዋድ በጉዞ ላይ ያለውን አምባገነን በህብረት ለመሸኘት ዘዴው ፅናትና ቆራጥነት ስለሆነ ሁለንተናዊ ድጋፋችሁና ቁርጠኝነታችሁ አይለየን።” (የ33ቱ ፈራሚ ፓርቲዎች ህብረት መግለጫ)
2-”ፓርቲዎች ህዝብን ማንቀሳቀስ ካልቻሉ፣ ፓርቲዎች በጉልህ ሕዝብ ከጀርባቸው እንዳለ ማሳየት ካልቻሉ፣ እኛ መሪዎችም ፈራ ተባ እያልን የምንሄድ ከሆነ፣ በዚህ ሁኔታ እኔ ማፈር ከጀመርኩ ውሎ አድሮአል። በየኢንተርቪው፣ በየጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እየፎከርን ብቻ የወረቀት ላይ ነብር ሆነን መቀጠል አለብን ብዬ አላምንም፣ ስለዚህ ትግሉ የሚጠይቀውን ሁለንተናዊ መንገድ መጠቀም አለብን።” (አቶ አስራት ጣሴ የአንድነት ፓርቲ ህ/ግንኙነት ኃላፊ)
3-”በምንም—በምንም—ለደቂቃ እንኩዋን ሕዝብ የማይጠራጠረው ነገር፣ እዚህ(ግንቦት7) ውስጥ ያለነው ለፎርም አይደለም፣ እዚህ ውስጥ ያለነው ለጨዋታ አይደለም፣ እዚህ ውስጥ ያለነው ይሄ ስርአት ወድቆ በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እስኪፈጠር ድረስ መደረግ ያለበትን ለማድረግ ነው፣ እነሱም(ወያኔዎችን) እንዲሁ ያዝ ለቀቅ አድርገን እንደማንተው ያውቁታል፣ በዚህ ደረጃ በደንብ እንተዋወቃለን፣ ወያኔን ለመጣል መደረግ ያለበትን ሁሉ እናደርጋለን፣ እኛ ይሄን ስርአት ለመጣል ያለን እልህ መሰረቱ አጥንታችን ስር ድረስ ዘልቆ የገባ የውርደት ስሜት ነው፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንደዚህ ተዋርዳ ልትኖር አይገባትም፣ ብለን ለመጪው ትውልድ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመፍጠር የምንታገል ነን፣ ለዚህ አላማ ብንታሰር ብንቆስል ብንሞት ደስ የሚለን ሰዎች ነን—” (ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የግንቦት 7 ሊቀመንበር)
4-”አፓርታይድ በኢትዮጵያ ይቁም፣ ነፃነት እንፈልጋለን፣ ዜጎችን ማፈናቀል ይቁም፣ ዘረኝነት በቃን፣ ድምፃችን ይሰማ፣ በጫካ ሕግ እየኖራችሁ ስለሕግ-የበላይነት እኛን አታስረዱንም—ነፃነት፣ ነፃነት፣ ነፃነት—” (በኖርዌይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች)
5-”እኔ ማንም አይደለሁም—በርግጥ ለኢትዮጵያ ፍቅር አለኝ፣ ከዚህ ያለፈ ምንም—ምንም—ይሄ ሁሉ የሚገባኝ ሰው አይደለሁም—ይቺ ሀገር በጣም ትላልቅ ሰዎች የነበራት በተባበሩት መንግሥታት መድረክ ላይ ሲናገሩ አለምን የሚያስጨንቁ ሰዎችን የፈጠረች ናት—ዛሬ ግን ሰው የላትም፣ ኢትዮጵያ መሪ የላትም!!! ዛሬ ዜጎቹዋ በዓለም ላይ ተዋርደን ከጅቡቲ አንስተን ሞዛምቢክ ድረስ እስር ቤቱን የሞላነው እኛ ነን፣ በፍፁም እግዚአብሔር ከዓለም ሕዝብ መርጦ ለእንዲህ አይነት መከራ አይዳርገንም፣ ይሄ ሁሉ መከራ የመጣብን አምባገነኖችን የሚያለምድ ምቹ ጀርባ ስላለን ነው፣ ውርደት በቃ የሚል ትውልድ መፈጠር አለበት፣—እንደዚህ የሚያስተሳስረን አንድ አዳራሽ ውስጥ  ያስቀመጠን ኢትዮጵያዊነት ነው፣ አንተ እዚህ መኖር አትችልም የሚል ነገር ከመጣ ግን ኢትዮጵያዊነት አበቃ—የሚያስተሳስረን ገመዱ ተበጠሰ ማለት ነው። ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከዚህ መሬት አይደላችሁም ተብለው ሲባረሩ ጉንጭ የምናለፋ የምንነታረክ ከሆነ ኢትዮጵያን አብረን እየገደልን ነው—!!! በምንም መለኪያ በምንም ሁኔታ በዓለም ላይ ዘር የሌላቸው እነማን እንደሆኑ ታውቃላችሁ? ሕፃናት—ሕፃናት ዘር የላቸውም፣ ሕፃናት ብሄረሰብ የላቸውም፣ ምክንያቱም በራሳቸው ፈቃድ ያልመጡበት ነው፣ እኛ ፈልገን ባመጣናቸው መሬት ላይ ከዚህ አልተወለድክም ብለን በረሃብ የምንቀጣቸው ከሆነ እግዚአብሔርንም ሕግንም የተላለፍን ሰዎች ነን፣ ስለዚህ በኢትዮጵያ መሬት በፈለግነው መለኪያ በፖለቲካ ልንጣላ እንችላለን—እዚህ መሬት ላይ አትኖርም ወይም ከዚህ መሬት አይደለህም የሚል ፖለቲካ ግን ያጫርሰናል—!!! ስለዚህ ይሄን እዚህ ላይ ማቆም አለብን። (ፖለቲካል አክቲቪስት ና አርቲስት ታማኝ በየነ)
አሁን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነን፣ ሁሉም ብሶተኛ ተሰባስቦ ለአመታት የፀነሰውን ብሶት መተንፈሻ፣ የማይቀረው ሕዝባዊ አብዮት ማቀጣጠያ ምዕራፍ—እንዲህ በምሬት ግፉ በቃን፣ ጭቆና በቃን፣ ዘረኝነቱ በቃን እያልን በወያኔ የተማረርን ሁላችን፣ በውስጣችን ያለው መለያየት በቃን፣ መከፋፈል በቃን፣ ለአጥፊዎች በተመቸ መልኩ መሰነጣጠቅ በቃን! ኦሮሞ ብቻ አይደለንም፣ አማራ ብቻ አይደለንም፣ ትግሬም ብቻ አይደለንም፣ ጉራጌም እንዲሁ የትናንሽ ጎሳዎችና ጎጦች ህዝቦች ሳንሆን እስልምናም ክርስትናም ሃይማኖቶች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ የነበረች ከፍጥረት ስርአት እኩል ተፈጥራ የነበረች የታላቁዋ ኢትዮጵያ ዜጎች ነን። ጊዜው ወያኔን የመቅበርና ኢትዮጵያን ለማዳን የምንተጋበት ወቅት እንደሆነ ይሰማኛል፣ ከፊት ለፊታችን ያለው ጠላት ላይ ብቻ የምናነጣጥርበት፣ ለጥቃቅን  ግላዊ ፍላጎቶችና ጉዳዮች ቁብ የማንሰጥበት፣ ከራሳችን እግሮች ጋር እየተጠላለፍን ለመውደቅ የማንጣደፍበት፣ ራሳችንንም ጭምር ለትግሉ አሳልፈን የምንሰጥበት፣ በየሰልፉ ፊታችንን ሸፍነን የማንወጣበት፣ ይልቁንም በታላቅ ድምፅና ጩኅት የጠላትን ቅጥር የምናፈርስበት የመጨረሻው መጨረሻ ላይ እንደደረስን ይሰማኛል።
ሰላም ለኢትዮጵያ—ድል ለተገፉት ህዝቦች!

No comments:

Post a Comment