No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Friday, 21 December 2012

ወደ ጠፈር ማዕከሉ የተደረገው ጉዞ


በሔኖክ ረታ

በቅርቡ አይከን ኢትዮጵያ በተሰኘ የግል ድርጅት አማካይነት ከተማ አቀፍ የጥያቄና መልስ ውድድር ከተዘጋጀ በኋላ ተማሪዎቹ በሒሳብና በሳይንስ ትምህርቶች ላይ ያላቸው ችሎታ ተገምግሞ በውጭ አገር ከሚገኙ ተማሪዎች ጋራም በአህጉር ደረጃ ከተወዳደሩ በኋላ አንድ መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል፡፡
ይህም የኬኔዲ የጠፈር ማዕከልን በሎስአንጀለስ አሜሪካን ተገኝቶ መጎብኘት፡፡ ናሳ በሚል ምሕፃረ ቃል የሚታወቀው የአሜሪካ ብሔራዊ የጠፈር ማዕከል የነገዎቹን ጠፈርተኞች ከመፍጠርና ሳይንሱንም ከማስፋፋት አንፃር በየዓመቱ ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ታዳጊ ተማሪዎችን ለጉብኝት ይጋብዛል፡፡ የእኛ ልጆችም ይህን ዕድል ያገኙት አስፈላጊውን የማጣርያ ውድድር አልፈው በመጨረሻው ዙር በሕንድ የተካሄደውን ዓለም አቀፍ ውድድር አሸንፈው ነው፤” ይላሉ የአይከን ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ሰናክሬም መኰንን፡፡

በተያዘላቸው መርሐ ግብር መሠረት አንድ ሳምንት በናሳ ቆይታ ያደረጉት ተማሪዎች በጉብኝቱ ምን ያህል እንደተደሰቱና ለወደፊቱም ትልቅ ተስፋ እንዲሰንቁ እንዳስቻላቸው ይናገራሉ፡፡ ከስድስቱ ተማሪዎች መካከል አንዷ
የሆነችውና የ12 ዓመቷ የኢትዮ ፓረንትስ ትምህርት ቤት ተማሪ ሔርሜላ ዝናው “ከጠፈርተኞች ጋር አብሬ ምሳ እበላለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ ይህ ነው እኔን በጣም ደስተኛ ያደረገኝ፤” ትላለች፡፡ እንደ አብዛኛው የክፍል ጓደኞቿ ለሳይንስና ሒሳብ ትምህርቶች ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትና ትኩረትም እንደምታደርግ የምትናገረው ሔርሜላ፡፡

ለአንድ አገር መራቀቅና ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ መድረስ መንገዱ በሒሳብና በሳይንስ ትምህርት ዘርፎች ላይ በቂና የተካነ የሰው ኃይል ማፍራቱ እንደሆነም ትገልፃለች፡፡ በአገሯ የተፈጥሮ ሳይንስ ዕውቀት እምብዛም እንደማይታወቅ የምትገልጸው ሔርሜላ ቅጣው እጅጉ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ግን በናሳ ውስጥ በጠፈር ሳይንቲስትነት ይሠሩ እንደነበር ማንበቧን ትናገራለች፡፡ “የብዙ ጠፈርተኞቻቸው ታሪክ በሚገኝበት ቦታ ላይ የኚህን ኢትዮጵያዊ ታሪክ ባለማግኘቴ አዝኛለሁ፡፡ ለጥያቄዬም ምላሽ አልተሰጠኝም፤” ስትል ቅሬታዋን ትገልጻለች፡፡

ልዑል ሰሎሞን የተባለው የአስረኛ ክፍል ተማሪ በበኩሉ በእሱ ዕድሜ ያላየውን የጠፈር ማዕከል በአገሩ አፈር ላይ የማቋቋም ሕልም እንደጨበጠ ይገልጻል፡፡ “በአንዳንድ መጻሕፍትና በፊልም ብቻ የማውቀውን ሳይንስ ከዋናው ቦታው ሄጄ መመልከቴ ለሳይንሱ ያለኝን ፍላጎት በጣም ከፍ አድርጎታል፡፡ ይህን ስል ግን እዛ ሄጄ ትምህርት የመቅሰም ዓላማ እንጂ የመሥራት ፍላጎት የለኝም፤” ሲል አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ ያሬድ ግርማም እንዲሁ በኢትዮ ፓረንትስ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ በጉብኝቱ የተመለከተው ነገር በጣም እንዳስደሰተውና የአገሩን ኃያልነት ለማረጋገጥ እንዲህ ዓይነቱ የተራቀቀ ሳይንሳዊ ተቋም አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻል፡፡ “በተለይ የቅጣው እጅጉን ታሪክ በማንበቤ ቦታውን በመጎብኘቴ የተሰማኝን ደስታ ልዩ ያደርገዋል፤” ሲልም ለወገኑ ያለውን ክብር ይናገራል፡፡

በዳንዲ ቦሩ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ቤዛዊትም ብትሆን ማዕከሉን በመጎብኘቷ የተሰማት ስሜት ከሌሎቹ እንደማይለይ ገልጻ በአገሯ ይህንን መሰል ተቋም እንዲኖር መሻቷን ግን እንዲህ ነበር የገለጸችው፡፡ “ይህ ማለት ለብዙ ነገር መሠረት ነው፡፡ የምድርን እንቅስቃሴ ከመቆጣጠርና አስፈላጊውን ረቂቅ ዕውቀት ለመጨበጥ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደሞ ጠንክሬ በመማር አገሬን ለዚህ ዓይነት ቴክኖሎጂ የማብቃት ፍላጎት አድሮብኛል፡፡”

ከጊብሰን ዩዝ አካዳሚ የተመረጠችው ኤደንም ስሜቷ ተመሳሳይ ነው፡፡ “ወደ ትምህርት ቤቴ ስመለስ በጓደኞቼ ላይ የተመለከትኩት የመደነቅ ስሜት ጉዞዬ ምን ያህል የተለየ እንደነበር አሳይቶኛል፡፡ ይሄ ደሞ ጥሩ ነው፣ እነሱም ይህን ዕድል ለማግኘት ሲሉ የበለጠ ጠንክረው ይማራሉ፤” ስትል ሐሳቧን ትገልጻለች፡፡

በእንዲህ ዓይነቱ ላቅ ያለ ግምት በሚሰጠው ትምህርታዊ ጉዞ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ወላጆችና መምህራኑም ደስተኞች ናቸው፡፡ ከሦስት ልጆቻቸው መካከል ውጤታማ ሆኖ የተመረጠው አንዱ ልጃቸው መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ራሔል ጳውሎስ የተባሉ የተማሪው እናት፣ “ይህ ትምህርታዊ ጉብኝት ከትምህርታዊ ቁም ነገሩ ባሻገር ገጽታንም የሚቀይር ነው፤” ሲሉ አስተያየታቸውን ይገልጻሉ፡፡

በርካታ ወገኖቻችን በስደት ወደሚነጉዱባት አገር ልጆቻችን ከሌሎች አገር ከተወጣጡ ተማሪዎች ጋር ተወዳድረው እንዲህ ያለውን የተከበረ ዕድል ማግኘታቸው እጅግ የሚያበረታታና በልጆቻችን ተስፋ እንድናደርግ የሚያበቃን ነው፤” ይላሉ፡፡ ወይዘሮ አያንቱ ዘውገም በልጆቹ ብርታትና የነገ ተስፋነታቸው ይስማማሉ፡፡ “ከዚህ ጋር በተያያዘ ግን የነዚህን ልጆች መጨረሻ ለማሳመር መልካም ጅምሩን መከታተልና ለሌሎችም ዕድሉ የሚኖርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ሆነ ባለሀብቶች በእንዲህ ዓይነት ትልቅ ዋጋ በሚያሰጥ የሥራ መስክ ላይም እንዲሳተፉ ማበረታቻ ይሆናል፤” ብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment