No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Wednesday, 18 December 2013

'I Wanna be a Billionaire!' ግን የኛ ሰው ድንገት የአንድ ቢልዮን ዶላር ባለቤት ቢሆን ምን ይሆናል?


‘I wanna be a billionaire so freakin' bad
Buy all of the things I never had
I wanna be on the cover of Forbes magazine
Smiling next to Oprah and the Queen’       .  .  .  .  .  .  . 
ይላል የዘፈኑ ስንኝ፡፡

 ********

ግን የኛ ሰው ድንገት የአንድ ቢልዮን ዶላር ባለቤት ቢሆን ምን ይሆናል?

ግልጽ ነው፡፡ 

መጀመሪያ ይወፍራል፣ያለጠልጣል፣ ይቀላል፡፡ 

ማለትም  ቃተኛ ሄዶ አልጫ ፍርፍር ቁርሱን ይበላል፤ ምሳውን አመስተርዳም ሄዶ የፈረንጅ ምግብ በሹካ እየወጋ ይጎርሳል፤ ከዛ ሸራተን ቴምፕቴሽን ገብቶ ኬክ ይበላል፡፡ ሆዱ ይቆነዘራል፤ ከዛም ሂልተን ሽንትቤት ገብቶ አሩን ያራል (ይቅርታ፣ ይጸዳዳል)፡፡

ቀጥሎ ጉዳይ ገዳዩን ሠውዬ ይተዋወቃል፡፡

ጉዳይ ገዳዩ 'የሺ VIP' ጋር ይወስደዋል፡፡ ከዛም ከሰአት ከሰአት ከነሰይፉ ጋር የሺ ቤት በዝግ እየቃመ እንዴት ራሱን ዝነኛ ማድረግ አንደሚችል ስልጠና ይወስዳል፣ የኢትዮ-ቻነሉ ሳሚም እንዴት ከድህነት ተፍጨርጭሮ እዚህ እንደደረሠ የሚያሳይ ስድስት ቃለመጠይቅ ይሠራለታል፡፡ ሠራዊትም የማስታወቂያውን ውል እዛው ይዋዋላል፡፡ ቀጥሎ ጉዳይ ገዳዩ ከዋናዎቹ ሰዎች ጋር ሊያገናኘው እዛው በስልክ ቀጠሮ ያስይዝለታል፡፡

ማታ ማታ ጋዝ ላይት ቪአይ ፒ ክፍል ውስጥ ከባለስልጣናቱ ጋር ይተዋወቃል፣ ይላመዳል፡፡ “. . . የ'ናንተው ነኝ፣ ከጠላት ጋራ ምንም ንኪኪ የለኝም፣ ጀርባዬ ይጠና” ብሎ ይምላል፡፡ ብሉ ሌብል  ያወርዳል፣ ሰበብ ፋልጎ “ሚጢጢ” ስጦታ ይለቃል፣ ይወዳጃል፡፡



በጉዳይ ገዳዩ ያላሰለሰ ጥረት በወሩ ፍልስጤምን የሚያክል የኢንቨስትመንት መሬትና ከሀረሪ ክልል አመታዊ ባጀት ጋር የሚስተካከል  ብድር ያመቻቻል፣ ይጨርሳል፡፡ 

ጉዳይ ገዳዩንም ተከፋፋይ ቻፓ  በቼክ ቻይና ወደሚገኘው ባንኩ ይለቅለታል፡፡

ሁለት በባንክ ሃራጅ የወጣ ህንጻ ይገዛል፡፡ አንድ ሆቴል ይገነባል (በቀረጥ ነጻው ቢዝነስ ይሸቅላል) ባለ አስራ ሁለት ህንጻ ፎቅ ይገነባል፤ ለባንክ ማናጀሮች ጉቦ ሰጥቶ ህንጻውን ለስድስት የግል ባንኮች ያከራየዋል፡፡ ኮንስራክሽን ቢዝነስ ውስጥ ይገባል፡፡ በባለጉዳይ ገዳዩ ሠውዬ አሳላጭነት  አምስት የመንገድ ጨረታዎችን ያሸንፋል፣ የፈረደበትን ጥቁር V8 መኪና ይገዛል . . . ማኪያቶ ሲጠጣ ከመኪናው አይወጣም፡፡

ከዛም ‘ኪራይ ሰብሳቢ’ ምናምን እንዳይባልና ዋናዎቹን Ex-Communists እንዳያሳጣ ሁለት ጢኒኒጥ ፋብሪካዎችን ከፍቶ ሁለት መቶ ጠውላጋ ድሀዎችን በጠውላጋ ደሞዝ ይቀጥርበታል፡፡ ኢቲቪም የምርቃቱ እለት ሙሉ ዘገባ ይሰራለታል፣ በእለቱ ለተገኙ የመንግስትና የግል ጋዜጠኞችም ለያንዳንዳቸው የሻይ የቡና አምስት አምስት ሺህ ብር ይበጨቅላቸዋል፣ጋዜጠኞቹም እጁን እንደ መስቀል ተሳልመው ይወጣሉ፡፡ 

የአዲስ ዘመን ጋዜጠኞች ደግሞ በደስታ ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ፡፡

ጉዳይ ገዳዩ የከተማውን ዋና አፈጮሌ ያስተዋውቀዋል፡፡ አፈጮሌው ፒምፕ ነው፡፡ እንደምርጫው እምቡጥ የመሳሰሉ ቺኮችን ያቀርብለታል፡-ከድንግል እስከ ፈት ቆንጆ አሮጊት፡፡ ቢልየነሩም አዲሳባ ብቻ ሳይሆን ዱባይ ድረስ እየወሰደ ይመቻቻቸዋል፡፡ የታዋቂ ሰው ሚስት የነበረች ቆንጆ ፈልጎ ይወሽማል፣ ትዳሩን ፈቶ ያገባታል፡፡  ከዛም ለክብሩ ወሬውን ያስነዛዋል፡፡
አደይ አበባ መቅጠፉን ግን አያቆምም፡፡ ለሊት ለሊት ላይ ካዛንቺስ እንትን አዝማሪ ቤትን ያዘጋና  በሀያ አምስት ቺኮች ተከቦ

ብላክ ሌብል እያወራረደ የባህላዊ ባንድ ያዘፍናል፣ ይሸልማል፡፡


*******

የሆነ ሰአት ላይ ሁሉም ነገር ይሰለቸዋል፤  የጽድቅና ነገር ትዝ ይለዋል፡፡ወገኑን መርዳት እንዳለበት እና ‘የድርሻውን መወጣት’ እንዳለበት ትዝ ይለዋል፡፡ አሁንም ጉዳይ ገዳዩን ሰውዬ ያማክረዋል፡፡

ቀላል ነው፡፡

ሜሪ ጆይ እና ሜቄዶንያ ይወስደውና አራት መቶ ሺ ብር ቦጭቆላቸው ዘጠኝ ግዜ የሚድያ ኢንተርቪው ይሠጣል፡፡ የእናት የአባቱ አገር ውስጥ ሁለት ቤተክርስቲያን ያሰራል፤ አንድ ታዋቂ ዘፋኝ ሲታመም ወስዶ ያሳክመዋል፤ ወሬውንም ኤፍ ኤሞች ሁለት ወር ሙሉ ያስጮሁታል፡፡ ምድረ ያዲሳባ መርቃኝም የወሩ አጀንዳው ያደርገዋል፡፡ 

(ካምስት አመት ቡሃላ)

ሁለተኛው ትዳሩ ይፈርሳል፣ ድል ባለ ድግስ ያገባት ሁለተኛዋ ቆንጆ ሚስቱ ደግሞ የሱን ማጋጣነት መታገስ ያቅታታል፡፡ ስለዚህም ባ’ካባቢዋ ያሉትን ሰዎች ማውጣት ትጀምራለች፡ እሱ ትዝም አትለውም፡፡ እልክ ይይዛትና ጓደኞቹን እና መሰሎቹን ማውጣት ትጀምራለች፡፡  ያኔ መብከንከን ይጀምራል፡፡ ማዲያት ያወጣል፣ ሲጠጣ መጣላት ይጀምራል፡፡ አብሾ ነገር ይጀማምረዋል፡፡

ወደ ውጪ መመላለስ ያበዛል፡፡ አሁን ግን ዱባይና ቻይና ሳይሆን ታይላንድ ነው፡፡ አይነ ጨንባሳው ታይላንዳዊ ሀኪምም፡ “ስኳር፣ ሪህ፣ ደም ብዛት፣ ኮሌስትሮል፣ ልብ ድካም፣. . .  አለብህ፡ ስለዚህ ምንም እንዳትበላ፣ እንዳትጠጣ!” ብሎ ይከለክለዋል፡፡
ከሰዎቹ ጋር የነበረው እፍፍ ይቀንሳል፣ ይሄኔ ጉዳይ ገዳዩ በብርሀን ፍጥነት ይሸሸዋል፣ አብሮት መታየትም ያቆማል፡፡ የሆነ ሰአት ላይ ሰዎቹ የቢጫ ካርድ ይመዙበታል፣ ሙስና የሚባል፡፡ ስድስት መቶ ሚልዮን ብር የዘረፈው  ሰውዬ “ስልሳ ሺህ ብር ሰርቋል፣ መኖሪያ ቤቱ ሲበረበር ደግሞ አስር ሺ ብር እና አራት አይፎን ተገኝቶበታል” ተብሎ ይታሠራል፡፡ . . . . አዳሜ “እግዚኦ! ስልሳ ሺ ብር ከተሰረቀማ አለቀልን ማለት ነው፡፡ ደግ አደረጉት!” ብላ የደናቁርት መግለጫ ታወጣለች፣ በየድራፍት ቤቱ፡፡

 ታሳሪው ጉዳይ ገዳዩን በእግር በፈረስ አፈላልጎ እስር ቤት ድረስ ያስመጣዋል፡ ይደራደራሉ፣ ይጨርሳሉ፡፡ ኋላም በጉዳይ ገዳዩ ያላሰለሰ ጥረት ይፈታል፡፡

ከዛም እስኪሞት ድረስ አንገቱን ደፍቶ ይኖራል. . . . ሲሞት ቅድስት ስላሴ መንበረ-ጸባኦት ቤተ-ክርስትያን ይቀበራል፡፡ ጳጳሱ አቡነ እንትና የቀብሩ ዲጄ ሆነው ይገኛሉ፡፡

ይረሳል!

*** 
                                                                        
. . . . ሌላ በጥባጭ ቢልየነር ደግሞ ይፈጠራል. . . .ጉዳይ ገዳዩን የተዋወቃል፡፡
sourcehttp://eyobaeyoba.blogspot.no/2013/12/i-wanna-be-billionaire.html

No comments:

Post a Comment