No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Friday, 20 December 2013

'ኢትዮዽያዊነት' ምንድነው? by Abraha Desta


የህወሓት በስልጣን የመቆየት ስትራተጂ መከፋፈል ነው። ለመከፋፈል ወዳጆችና ጠላቶች መለየት ነው። ህወሓት ከትግራይ ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት "ሸዋ አማራ" ጠላቱ እንደሆነ ይሰብካል ('ዓረና ከጠላቶቻችን ጋር እያበረ ነው' የሚል ፕሮፓጋንዳ መሰረት እናድርግ)።
...

እንዴት ነው አንድ ህዝብ ለሌላ ህዝብ ጠላት የሚሆነው? የህዝብ ጠላት ሊሆን የሚችለው ገዢ መደብ ነው። ህዝብን የሚጨቁን ገዢ የህዝብ ጠላት ነው። ስለዚህ መወገድ ይኖርበታል። ህዝብ ግን የሌላ ህዝብ ጠላት ሊሆን አይችልም።

'የሸዋ አማራ' የትግራይ ጠላት መሆኑ የሚነግሩን ደርግ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀመውን ግፍ በማጣቀስ ነው። ደርግ ጨካኝ የነበረው ለትግራይ ህዝብ ብቻ አይደለም፤ አማራውም፣ ኦሮሞውም ሌላውም ተጨቁኗል። የአማራ ህዝብም "ደርግ አማራ ነው፣ የኛ ነው" ብሎ ከሌሎች ህዝቦች የተለየ ድጋፍ ለደርግ አልሰጠም። ደርግም "ለአማራ ህዝብ የቆምኩ ነኝ" አላለም። ደርግ "ለኢትዮዽያ የቆምኩ ነኝ" እያለ ሁሉም ኢትዮዽያውያንን በደለ።

ህወሓት ከስልጣን የሚወርድ ከሆነ ትግራይ ኢትዮዽያ እንዲሆን የሚፈልግ አይመስልም። ህወሓትና የትግራይ ህዝብ በተመሳሳይ ዕድሜ መመዘን ግን ስህተት ነው። ምክንያቱም የህወሓት የስልጣን ዕድሜ አጭር ነው። የትግራይ ህዝብ ግን ለዘላለም ይኖራል። በሌላ ስርዓት ሌላ ታሪክ ያስመዘግባል። ህወሓት ግን በምርጫ ወይ በጠመንጃ በቅርብ ግዜ መውደቁ አይቀርም፤ የተፈጥሮ ሕግ ነውና።

"ኢትዮዽያዊ ነኝ" ካልክ "የሸዋ ልሂቃን ደጋፊ ነህ" ይሉሃል። ኢትዮዽያ የሸዋ ፖለቲከኞች ብቻ የግል ንብረት ነች እንዴ? ኢትዮዽያኮ የሁላችን ነች። የትግራዮች፣ የአማራዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ሶማሌዎች፣ ቤኑሻንጉሎች፣ ጋምቤላዎች፣ ዓፋሮች፣ ደቡቦች ... የሁሉም ናት።

ኢትዮዽያዊ ማንነት ለተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከሰጠነው ተሳስተናል። የፖለቲካ ተፎካካሪዎቻችን "ኢትዮዽያውያን ነን" ስላሉ እነሱን ለመቃወም "ኢትዮዽያውያን አይደለንም" ካልን ችግሩ የኛ ነው። ምክንያቱም ኢትዮዽያዊነታችን በራሳችን ፍቃድ ለሌሎች አሳልፈን ሰጥተናል ማለት ነው። ኢትዮዽያዊነት ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ማን ሰጠው? ኢትዮዽያውነት'ኮ የጋራ
ማንነታችን ነው።

እያንዳንዱ ሰው የራሱ (የግሉ) የሆነ ማንነት አለው። በወረዳ፣ ዞን፣ ብሄር ወዘተም ቡድናዊ የግል ማንነት አለው። በኢትዮዽያ ደረጃ ደግሞ የሁላችን የጋራ የሆነ ኢትዮዽያዊ ማንነት አለን።

ፖለቲከኞች "እነዚህ ሰዎች ኢትዮዽያዊ ስሜት የላቸውም፣ በዘር ያስባሉ፣ ትክክለኛ ኢትዮዽያውያን እኛ ነን ወዘተ ..." ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል። ምክንያቱም ኢትዮዽያ የየተወሰኑ ግለሰቦች አይደለችም። ኢትዮዽያ የሁሉም ነች። ኢትዮዽያዊነት የተወሰነ ብሄር ወይ ክልል ወይ አውራጃ የሚወክል አይደለም። ሁሉም የኢትዮዽያ ህዝቦች የሚወክል ነው።

የኢትዮዽያ ህዝቦች እንደ አንድ ሰው አንድ ዓይነት ሃይማኖት፣ ባህልና ማንነት ሊኖራቸው አይችልም። በአንድ ሀገር የተለያዩ ሰዎች እስካሉ ድረስ የተለያየ ማንነት አለ (በብሄር፣ ወረዳ ወዘተም የተለያየ ማንነት ነው ያለው)። ስለዚህ ኢትዮዽያዊነት የአንድ ሰው ማንነት ሳይሆን የብዙ ሰዎች ማንነት ድምር ዉጤት ነው።

ስለዚህ ኢትዮዽያዊነት የጋራ ማንነት ነው። ኢትዮዽያዊነት አብሮነት ነው። እናም አንድ ግለሰብ ወይ የፖለቲካ ድርጅት "እኔ ነኝ ትክክለኛ ኢትዮድያዊ" ካለ ኢትዮዽያዊነት ወደ አንድ አከባቢ (ብሄር ወይ ክልል ወይ መንደር) አውርዷታል ማለት ነው። ይህም ስህተት ነው።

ኢትዮዽያዊ መሆን ከደበረን ችግር አለ ማለት ነው። ችግሩ ጭቆና ሊሆን ይችላል። ጭቆና (ለምሳሌ የብሄር ጭቆና) ካለ ጭቆናውን ለማስወገድ ሁሉም ኢትዮዽያውን ህዝቦች ተባብረው መፍታት ይኖርባቸዋል። ሁላችን ከተባበርን ችግሮችን (ብሄራዊ ጭቆናን) ማስወገድ እንችላለን።

ጭቆና ስለበዛብን ከኢትዮዽያ መገንጠል (አብሮነትን መቃወም) መፍትሔ ሊሆን አይችልም። እንበልና በትግራይ ህዝብ ወይ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ብሄራዊ ጭቆና ተፈፅሟል። አሁን መታገል ያለብን በነዚህ ህዝቦች ላይ የነበረውን ብሄራዊ ጭቆና በማስወገድ ነፃነትና እኩልነት ማረጋገጥ ነው። ለዚህ ጉዳይ ሁሉም ዜጎች መተባበር ይኖርባቸዋል።

"ብሄራዊ ጭቆና ስለነበረ (ስላለ) መገንጠል እንፈልጋለን" የሚለው ሐሳብ አይመቸኝም። ምክንያቱም ጭቆናው ከነበረ አሁንስ ቢሆን እንዴት በመለየት መቅረፍ ይቻላል? ትግራዮችና ኦሮሞዎች ጭቆና የደረሰባቸው ባለፉ ስርዓቶች ከሆነ ላለፈው በደል አሁን በመገንጠል እንዴት መቅረፍ ይቻላል? ብሄራዊ ጭቆናው ያለው አሁን ድረስ ከሆነም ለመለየት ከመምረጥ አብሮ ታግሎ ጨቋኝ ስርዓቱ በመጣል እኩልነትን ማስፈን እየተቻለ ለመገንጠል ማሰብ ምን አመጣው?

ጨቋኝ ስርዓቱ ለማስወገድ አቅሙ ከሌለን ለመገንጠልም አቅሙ አይኖረንም። ምክንያቱም ከመገንጠል ስርዓቱን መቀየር ይቀላል። ምክንያቱም ለመገንጠል ብቻህን ነው የምትታገለው፤ ስርዓት ለመቀየር ግን ከኢትዮዽያውያን ወገኖችህ ጋር ነው የምትታገለው። ደግሞ በመገንጠል ጭቆና አይወገድም። ለእኩልነት ጠንክረው በመታገል እንጂ በመገንጠል ጭቆናን ያስወገዱ ህዝቦች የሉም።

ኢትዮዽያዊነቴ ለማንም አሳልፌ አልሰጥም። ኢትዮዽያዊነት ለ"ሸዋ አማራ" ብቻ የተሰጠ ማንነት አይደለም። ኢትዮዽያዊነት የሁላችን ነው።

It is so!!!

No comments:

Post a Comment