ሰኔ 5 2013
የሚሆን የማይመስለው ሆነ፤ ልቦች በአንድነት ዘመሩ፤ የደስታ እንባ ፈሰሰ፤ አእዋፍ በደስታ አብረው እስኪቀዝፉ ድረስ የነጻነት ድምጽ የነጻነት ጩኸት አየሩን ሞላው፤ የሕዝብ አሸናፊነት በግልጽ ገኖ ታየ፤ የታፈነው የድምጽ ማእበል ግድቡን ትሶ ወጣ፤ የምን እንደረግ ይሆን ጭንቀት እትትም ተደረመሰ፤ ምድር የጠበበች እስኪመስል ሽዎች በነጻነት ፈሰሱባት፤ በእውነት 1997ን በ2005 አየነው። ገዥዎቻችን የሕዝባችን የአልገዛም ባይነት ወኔ ባልተቋረጠው አፈናቸው ተዳፈነ እንጅ ፈጽሞ እንዳልሞተ በእርግጥ ባይኖቻቸው አዩ። ልዩነትን የሰበኩት ሲሳቀቁ ፀንቶ የነበረው የፍርሃት ግንብ ኢያሪኮ በሰላም በፍቅር በአንድነት መዝሙር ተደረመሰ እሁድ ግንቦት 25 2005 ዓ/ም።
በ1997 ዓ/ም ቅንጅት ካዘጋጀውና እስካሁንም ድረስ ትዝታው ከሕዝብ ህሊና ካልጠፋው ሰላማዊ ሰልፍ ወዲህ የመጀመሪያ የሆነው የግንቦት 25ቱ ሰልፍ መፈቀድን በተመለከተ አንዳንዶች ወያኔ ህዝብን ለመያዝ፣ ከሕዝብ ለመታረቅ ያደረገው ዘዴ ነው ይላሉ። ሲያስረዱም በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሶ የነበረውን የአማሮችን ከቤኒሻንጉል መፈናቀል ቀልብሶ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ መሞከሩ፣ ጥቂት ቢሆኑም በሙስና ተዘፍቀዋል በሚል የራሱን የወያኔን ባለስልጣናት ዘብጥያ ማውረዱን ይጠቅሱና አሁን ደግሞ በሰማያዊ ፓርቲ የተጠየቀውን የሰላማዊ ሰልፍ እናድርግ ጥያቄ መፍቀዱ ወያኔ አንድም በአባይ ግድብ ምክንያት በተለይ ከግብጽ ጋር የገባበት እሰጥ አገባ ስላሳሰበው ሕዝባችንን ባንድነት ለማቆም ከማሰብ የተደረገ ነው ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ በሰባዊ መብት ረገጣ አይሆኑ እየሆነ ያለው ወያኔ የእርዳታ ሰጭ ሀገሮችንና ድርጅቶችን ቀልብ ለመግዛትና የውጭውን ማሕበረሰብ አይን ለመሳብ ያደረገው ነው በማለት የተቻሉ። ተችዎች ይህን ይበሉ እንጅ ከሰልፉ ትቂት ቀናት ቀደም ብሎና ከሰልፉም በሗላ በወያኔ መንደር እየሆነ የነበረውና ያለው ግን ይህን አያረጋግጥም ነበር።
ጠቅለል ባለ መልኩ የሰሞኑን ሰልፍ በተመለከተ ወያኔ ውጥረት ውስጥ ገብቶ በዚህ የተነሳም ፈቅዶ ሊሆን ይችላል፤ ካለፉት ዓመታት ልምዳችን ስንነሳ ግን ወያኔ ሕዝብ የወደደውን አያደርግም። ሕዝብ የፈለገውንም አይሰጥም። እራሱ የመረጠውን በራሱ ጊዜና እቅድ መከወን ነው የሚያስደስተው። ከዚህ በፊት ብዙዎች ስለሕዝባችን ብዙ ነገር ብለው ጽፈውም ነበር የወያኔ ፍላጎትና ምርጫ ስላልነበረ ግን መጨረሻቸው ቃሊቲ ነው የሆነው። ከሰልፉ በሗላ ከወያኔ የተሰጠው መግለጫ አይሉት ማስጠንቀቂያም የሚያመለክተው እኛ ባልፈለግነው መልኩ የሚደረግ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ ”የሕዝብ ጥያቄም እንኳ ቢሆን” ዋጋ ያስከፍላል አይነት ነበር።
ወያኔ ሕወሃት የሚፈልገው በራሱ አፈ ቀላጤዎች አማካኝነት ሁሌ እንደሚነግረንም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሁና እንድትቀጥል፣ ሕዝባችንም በሀይማኖት፣ በቋንቋና በብሔረስብ ሳይከፋፈል እንዲኖር የኔ መኖርና መግዛት ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም፣ ያልኩትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈጸም አለበት ነው። አለበለዚያ ግን ኢትዮጵያ አትኖርም ሕዝቡም ይበጣበጣል ነው።
ይሁን እንጅ ወያኔ እንደሚያወራው ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም ባሳለፍናቸው ሶስትና አራት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ ያሳዩት ነገር ቢኖር ልክ እንደከዚህ ቀደሙ የተጠናከረ አንድነታቸውን ነበር። በሃይማኖት መቻቻልን መዋደድንና መፋቀርን የተለያዩ እምነት ተከታዮች ባንድ ጣራ ስር ከመኖር አንስቶ ባንድ ላይ በራሳቸው መንገድ መጸለይን፣ ላንደኛው ችግርና ዓላማ ተረዳድቶ አብሮ መቆምን በማሳየት መለያየትን መጠፋፋትን ሳይሆን አንድነትንና ወገንተኛነትን በጉልህ ለዓለም አሳይተዋል። ለወያኔ እኔ አውቅላችሗለሁ ደካማ ፖለቲካ አይበገሬነታቸውን በማሳየት የወያኔ አካሄድ ያንድነትና የጥንካሬ መንገድ ሳይሆን የመለያየትና የውድቀት መሆኑን በተግባር በደማቁ አስምረው አስመስክረዋል።
አንዳንዴ ታዲያ ከእንደዚህ ያለው አብሮ የመቆም፣ የመደጋገፍና የመረዳዳት ጠንካራ ባሕላችን በተጻራሪ የቆመው ወያኔ ከኔ መኖርና ይሁንታ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አገር ያጠፋሉ ለማለት ሲዳዳው ምን ማለቱ ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት እየተጠናከረ ከመጣ ለአገዛዜ ስለሚያሰጋኝና ከኔ ውጭም ሌላ እንዲገዛ ስለማልፈቅድ በራሴ መንገድ ሀገሪቱን እበታትናታለሁ ነው? ወይስ ጦርነትን መስራት እንችላለን ብለው እንደሚፎከሩት ሀገር ለመገጣጠምም ሆነ ለማፈራረስ አቅሙ አለን ለማለት ነው? የስነ አእምሮ ጠበብት ስቶክሆልም ሲንድረም ብለው እንደሚጠሩት ሕዝባችን በሙሉ ወያኔ ከሌለ እኛም ሀገራችንም አትኖርም ብሎ እንዲያስብ የሚደረግ ጫና ነው? ወይስ ሕወሃት ከምስረታው ጀምሮ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝለትን ሀገራችንን የመበታተን ተግባሩን በገደምዳሜ እየነገረን ነው?
ወያኔ ያሻውን ቢልም የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን አጠናክሮ ሕወሃትን ማርበድበዱን ቀጥሏል። ወያኔ የአንድነትን አስፈሪነትና ሃያልነት ከ1997 ዓ/ም ወዲህ እሁድ ግንቦት 25 ባደባባይ ባይኑ በብረቱ ተመልክቷል። እስከዛሬ ላሳለፋቸው የአገዛዝ ዘመኑም ከኔ ሙሉ ይሁንታ ውጭ የሚደረጉ መተባበሮች፣ ስብሰባዎች፣ ሰልፎች ሁሉ ለሀገር አንድነት አደገኞች ናቸው ፐሮፓጋንዳ በእርግጥም ፕሮፓጋንዳ ብቻ መሆኑን ሁላችንም በተግባር አይተናል።
ወያኔ እንዲያስታውሰው የሚያስፈልገው የቀድሞውን የወያኔ ቁንጮ ጨምሮ በዓለማችን የታወቁ ብዙ አምባገነን አገዛዞችና መሪዎች የተናገሩትንና ለማድረግ ያሰቡትን እኩይ ዓላማ ሳያደርጉና ሳያዩ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ወዲያኛው ማለፋቸውን ሲሆን፤ ሕዝቡ ግን ከፍርሃት ቆፈን ወጥቶ በበለጠ ተጠናክሮ ተፋቅሮና ተቻችሎ በአንድነት ጎዳና የነጻነት መዝሙር እየዘመረ መቀጠሉን አሰረግጦ እያሳየ መሆኑን ጭምር ነው።
No comments:
Post a Comment