No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Friday, 29 March 2013

! …….. ወይ የመናገር ነፃነ …..ት! …….!

እንዲህም ተነስተዋል፣ “ኣብርሃ መቀሌ ዉስጥ ሁኖ የፈለገውን እየተናገረ፡ ‘ ኢትዮዽያ ዉስጥ የመናገር መብት የለም’ ይላል።”

ጥሩ የሚባል ኣስተያየት ነው። ነገር ግን የመናገር መብት ወይ ነፃነት በኣግባቡ ካለመገንዘብ የመነጨ ይመስለኛል።

(1) የመናገር መብት በፌስቡክ ብቻ መፃፍ መቻል ማለት ነው? ስለ መናገር መብት ስናገር፣ መናገር የምችልባቸው መድረኮች እንዲኖሩ እየጠየቅኩ ነው። ለምሳሌ እኔ በነፃ ሚድያ (የግል ቲቪ፣ ሬድዮ፣ ጋዜጣ፣ መፅሄት፣ ጦማርና የተለያዩ ዌብሳይቶች እንደፈለኩ መናገርና መፃፍ እችላለሁ??? እነዚህ ሁሉ የተዘጉ ኣይደሉምን??? በነፃነት እንዳንናገር ኣልታፈንም??? የግል ሚድያ ሲታፈን የመናገር መብትም ኣብሮ እየታፈነ ነው።

ስለዚ በፌስቡክ መፃፍ ስለቻልኩ የመናገር መብቴ ተከብሮልኛል ማለት ኣይቻልም። ፌስቡክ የኢትዮዽያ መንግስት የግል ስጦታ ኣይደለምና።

(2) እንበልና እኔ (በፌስቡክም በሌላም) የፈለኩትን ነገር እንድናገር ተፈቅዶልኛል። እኔ የመናገር መብት ኣለኝ ማለት ሁሉም የኔ ኣምሳያ የመናገር መብት ኣለው ማለት እንችላለን? ብዙ ዜጎች (እንኳን የመናገር መብታቸው ሊጠቀሙና) ለህይወታቸውም ፈርተው ይኖራሉ። ብዙ ጓደኞቼ ህወሓትን ባለመደገፋቸው ከስራ ተባረዋል። የፈለጉትን የተናገሩ ከገዢው ፓርቲ ማስፈራርያ ይደርሳቸዋል።


ባጭሩ የእኔ መብት ተከበረ ማለት የሌሎች ሰዎች (የሁሉም ሰው) መብት ተከበረ ማለት ኣይደለም። ወይስ የራሴ መብት ካስከበርኩ ስለሌሎች ሰዎች መብት መናገር የለብኝም ነው ነገሩ???

(3) “እንደፈለክ እየተናገርክ የመናገር መብት የለም ትላለህ” ተብሏል። እና የመናገር መብቱ ስላለኝ፡ ዝም ብዬ ዝም ልበል? ምን እያላችሁኝ ነው??? እዚጋ የመከራከርያ ሓሳባቹ ማወቅ እፈልጋለሁኝ። ኣማራጭ ልስጣቹ (እኔን ለምትቃወሙ የስርዓቱ ደጋፊዎች)፡ እኔ መናገር ስለቻልኩ:

(ሀ) ‘ገዢው ፓርቲ ዴሞክራሲ (የመናገር ነፃነት) ኣስከብሯል/ ኣስፍነዋልና፤ ፓርቲውን መውቀስ፣ መቃወም የለብህም’ እያላችሁኝ ነው? ፓርቲያቹ የመናገር (ሓሳብ የመግለፅ) መብት ከፈቀደ፣ እኔ በፌስቡክ ስፅፍም ይህንን ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቴ እየተጠቀምኩ ነው። ስለዚ መብቴን መጠቀም እንጂ ዝም እንድል ኣይጠበቅም። መብቱ ስለተሰጠህ (ተስጥቶኝ ከሆነ) ዝም ማለት ኣለብህ ሊባል ኣይችልም፤ ከተባለ ግን መብትን መስጠት ሳይሆን መከልከል ነው የሚባለው።

(ለ) ‘በኢትዮዽያ ዴሞክራሲ የለም (የመናገር ነፃነት ታፍነዋል)ና ኣንተን (እኔን) ገዢው ፓርቲ የመንቀፍ ወይ የመቃወም መብት የለህም’ እያላቹ ነው??? ሓሳባቹ እንዲህ ከሆነ ታድያ የኔ በፌስቡክ መፃፍ ሰዎች ሓሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲኖራቸው ለምናደርገው ሰላማዊ ትግል ኣንድ ኣካል መሆኑ ነው። ስለዚ የምፅፍበት ምክንያት ግልፅ ነው። እኛ ኢትዮዽያውያን የመናገር ነፃነታችንን የሚያከብርልን ዲሞክራሲያዊ መንግስት ያስፈልገናል። ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ መታገል ያስፈልጋል። ስለዚ መፃፌ ትክክል ነው።

(ሐ) ‘በኢትዮዽያ ዴሞክራሲ ኣለ፣ ነገር ግን ዴሞክራሲ የራሱ የሆነ ገደብ (ሕግና ስርዓት) ኣለው። ኣንተ በምትፅፋቸው ነገሮች ስርዓት ሊኖርህ ይገባል’ እያላቹ ከሆነ እኔ የምፅፈው ሕገ መንግስት መሰረት ያደረገ መሆኑ ላረጋግጥላቹ እወዳለሁ። በኢትዮዽያ ሕገ መንግስት የሚጣሰው በተራ ዜጎች ሳይሆን በገዢው ፓርቲ ነው። ሕግ የጣሰ በሕግ ይጠየቃል። ነፃነት ገደብ ኣለው። ያ ገደብ ግን በተግባር በሚሰራበት ሕገ መንግስት ውስጥ የተደነገገ የጋራ የስምምነት ነጥብ እንጂ የገዢዎችን የግል ጥቅም መሰረት ያደረገ ኣይደለም።

በዚ መሰረትም: ሓሳብ የመግለፅ ነፃነት እስከመሳሳት ድረስ ይሄዳል። ሰው የመሳሳት መብት ኣለው። መሳሳት በራሱ ስሕተት ኣይደለም። ኣንድ ተግባር ስሕተት የሚሆነው የሌላውን ሰው መብት በኣሉታዊ መልኩ መጉዳት ሲጀምር ብቻ ነው። ለዚህ መፍትሔም ጉዳዩ ወደ ሕግ (ፍርድቤት) ማቅረብ ነው። (ይቅርታ ነፃና ገለልተኛ የፍትሕ ኣካላት ሲቋቋሙ ማለቴ ነው)።

(4) የመናገር መብት (ሓሳብን በነፃነት መግለፅ) ሲባል ስትጮህ ወይ ስትፅፍ ኣለመታሰር ወይ ኣለመከልከል ማለት ብቻ ኣይደለም። የመናገር መብት የመደመጥ መብትም ይጨምራል። ዜጎች የመናገር መብት ኣላቸው ስንል ለሚናገሩትን ነገር፣ ለሚጠይቁትን ጉዳይ መንግስት በሚገባ ኣዳምጦ መፍትሔ የመስጠት ሕገ መንግስታዊ ግዴታ ኣለበት። ዜጎች ተሰሚነት ሊኖራቸው ይገባል።

የመናገር መብት መጮህ (ወይ መፃፍ) ብቻ ኣይደለም። ለምሳሌ የኢትዮዽያ ሙስሊሞች ለኣንድ ዓመት ያህል በሰለማዊ ሰልፍ መልክ ጥያቂያቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ጥያቂያቸው ግን እስከኣሁን ድረስ መልስ ኣላገኝም። ሰልፍ መውጣት ስላልተከለከሉ ታድያ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብታቸው ተከብሮላቸዋል ማለት ኣይቻልም። የሚመለከተውን ኣካል ጀሮ ማግኘት ኣለባቸው። መፍትሔ እስካላገኙ መብታቸው ኣልተከበረም። ስለዚ መናገር ብቻ ኣይደለም የምንፈልገው፤ መደመጥም እንፈልጋለን።

(5) የመናገር መብት ‘የመናገር መብት የለም’ ብሎ የመናገር መብትም ያጠቃልላል። ስለዚ ‘የመናገር መብት የለም’ ብዬ የመናገር መብት ኣለኝ።

We have to struggle to replace the ‘rule of man’ with the ‘rule of law’.

It is so!!!
sorce. Abraha Desta

No comments:

Post a Comment