No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Friday, 22 March 2013

! …… የትግራይ ህዝብና ህወሓት ………….!


እውነት ነው። የህወሓት መሪዎች የትጥቅ ትግሉ ጀመሩት። ደርግ ዓማፅያኑ ለማጥፋትና ትግራይን ለመቆጣጠር የሃይል እርምጃ መውሰድ ጀመረ። ትግራይ የጦርነት ኣውድማ ሆነች። የትግራይ ገበሬዎች በሰላም የእርሻ ስራቸው ማከናወን ኣቃታቸው። የደርግ ወታደሮች ገበሬዎቹን ማስፈራራት፣ ሴቶችን መድፈር፣ ወጣቶችን በግደል (በጥርጣሬ) ተያያዙት።

በደርግ ኣሰራር የተማረረው የትግራይ ገበሬ ጫካ ገባ። እዛው ጫካ ከህወሓቶች ጋር ተቀላቀለ። ኣብዛኛው ታጋይ (ገበሬ ወይ ኣርሶ ኣደር) ደርግን ለመታገል ጠመንጃ ያነሳው በደርግ ስርዓት በነበረ ጥሩ ያልሆነ የሰለማዊ ሰዎች ኣያያዝ እንጂ እንደሚነገረን እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ። በዚ ምክንያት በትግራይ ከኣንድ ቤተሰብ ቢያንስ ኣንድ ታጋይ (የተሰዋም በህይወት ያለም) ነበር (ኣለ)።

ነገር ግን ሁሉም የትግራይ ተወላጅ የህወሓት ደጋፊ ኣይደለም። ምሳሌዎችን ልጥቀስ።

ምሳሌ ኣንድ

የትግራይ ኣርሶ ኣደር የታገለበት ዓላማና የመሪዎቹ ለየቅል ነበር። በ1983 ዓም የህወሓት መሪዎች ኣራት ኪሎ ቤተ መንግስት ከገቡ በኋላ የመሪዎቹ ዓላማ ለታጋይ ገበሬዎቹ ግልፅ ሆነ። በታጋዮቹና መሪዎች የዓላማ ልዩነት ግልፅ ሆነ። ታጋይ ገበሬዎቹ ጥያቄ ኣስነሱ። ጥያቂያቸው ምን ነበር??? ስድስት ጥያቄዎች:


(1) የኤርትራ ረፈረንደም (ነፃነት ወይ ባርነት የሚል ኣማራጭ) ስሕተት ነው፤ ለሀገር ኣንድነት መስራት ሲጠበቅብን ምንሊክ የሰራው ስሕተት እየደገምን ነው (ኃይለስላሴ እንኳ ለማስተካከል ሞክሮ ነበር)።

(2) የባህር በር (ወደብ) ያስፈልገናል። ሁሉም ነገር ለሻዕቢያ መስጠትና ኣገልጋይ መሆን በታሪክ ተጠያቂዎች ያደርገናል።

(3) የተታገልንበት ዓላማ መንገዱ እየሳተ ነው። ዓላማችን ስልጣን መያዝ ብቻ ኣልነበረም፤ ዲሞክራሲ ማስፈን ነው።

(4) ሙስና እየተስፋፋ ነው፣ ትግላችንና መስዋእትነቻን በኣሉታዊ መልኩ ይጎደዋል።

(5) የደርግ መሪዎች እንጂ ሁሉም የደርግ ወታደሮች ጠላቶቻችን ኣይደሉም፤ በመከላከያ ሰራዊታችን ይጠቃለሉ፣ ብዙ የሰለጠኑና የሀገር ሃብት ፈሰስ የተደረገባቸው ናቸው።

(6) ሻዕቢያ ሊወረን እየተዘጋጀ ነው፤ ወታደራዊ ዓቅሙ እየገነባ ነው። እኛ ደግሞ ሀገራዊ መከላከያ ሰራዊት ይኑረን።

የሚሉ ጥያቄዎች ተነሱ። ነገር ግን ጥያቄዎቹ ወድያው ሻዕቢያ ጀሮ ደረሱ። የሻዕቢያ መሪ ኢሳያስ ኣፈዎርቂ ከመለስ ዜናዊ ጋር ተነጋገሩበት። እንደዉጤቱም በ1985 ዓም ከ32, 000 በላይ የሚሆኑ የህወሓት ታጋዮች (ጥያቄ ያነሱ) እንዲባረሩ ተደረገ።

እንኳን የትግራይ ህዝብ በሙሉ፣ ህወሓት የታጋዮቹ ድጋፍ የለውም። መረጃ ስለሌለን ግን ሁሉም የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ ኣድርገን እናስባለን።

ምሳሌ ሁለት

ሑመራ ኣከባቢ ነው፣ ልዩ ስሙ ማይካድራ። ኣንድ የድሮ ታጋይ ሴት ሦስት ልጆች ብቻዋ ታሳድጋለች። የማይካድራ ህዝብ (እንደሌላው ሁሉ) በመለስ ሞት ምክንያት የሓዘን ሰልፍ እንዲያደርግ በካድሬዎች ታዘዋል። ሴትየዋ በሓዘን ሰልፉ ኣልተገኘችም። በፖሊስ ተይዛ እንድትታሰር ተደረገ (የታሰሩ ብዙ ናቸው ግን ይቺ ሴት መረጥኩኝ)። በፖሊስ ለምን እንዳልተገኘች ተጠየቀች።

ሴትየው: ስራ ስለበዛብኝ ነው ያልመጣሁት

ፖሊስ: ስራ ቢበዛብሽስ??? ስራ ከመለስ ይበልጣል?

ሴትየው: እኔ ኮ ብቻየን ሦስት ልጆች ኣሳድጋለሁ።
ፖሊስ: እና?

ሴትየው: እናማ ስራ ይበልጥብኛል። ደሞኮ ሞት ብርቅ ኣይደለም። መስዋእትነት ኮ እናውቀዋለን። ባሌን ታውቀዋለህ። ታጋይ ነበር። ድሮ ተሰውተዋል። ልጆቹ ማሳደግ ኣይችልም። የኔና የተሰዋው ባለቤቴ ሓላፊነት ተሸክሜ ልጆቻችን ለማሳደግ ሌት ተቀን መስራት ኣለብኝ። መለስ ከሞተ እናንተ ቅበሩት።

ፖሊስ: ኣንቺ ራስሽ ታጋይ ነበርሽ። ባልሽም ተሰውተዋል። መለስ ደግሞ የሰማእታት ኣርኣያ ነው። ስለዚ ልታዝኚለት ይገባል።

ሴትየው: መለስ ከምወደው ባሌ ኣይበልጥብኝም። ኣሳዛኝ መስዋእት ኮ ጫካ ዉስጥ ተሰውተው ያለቀባሪ ተጥለው የቀሩ፣ ሬሳቸው የጅብና ኣሞራ ሲሳይ የሆነ፣ (ኣብ ፈቀዶ ጎቦታትን ሽንጥሮታትን ዝተረፉ) እንጂ ……. መለስ ኮ ብዙ ነገር ኣይተዋል። ኣሁን ደግሞ በክብር፣ በስርዓት እያረፈ ነው። ባሌኮ የቀብር ስነስርዓት ኣልተደረገለትም። ምን ታካብዳላቹ?! በመለስ ሞት ግን ባሌና የትግል ጓደኞቼ (ስውኣት ብፆተይ) ኣስታውሼ ኣዝኛለሁ።

ሴትዮዋ ተፈታች። እኛ ግን የትግራይ ህዝብ በስርዓቱ ደስተኛ ይመስለናል። ዉስጡ እየነደደ ነው።

ምሳሌ ሦስት

በትግራይ ሓውዜን ኣከባቢ ነው። ኣንድ ኣብሮ ኣደጌ (ጓደኛየ) ኣስታወስኩ። ኣብረን እንማር ነበር (እስከ ስድስተኛ ክፍል)። ከስድስተኛ ክፍል በላይ ትምህርቱ መቀጠል ኣልቻለም። የልጁ ኣባት የህወሓት ታጋይ ነበር፤ ተሰውተዋል። ከኣያቶቹ ጋር ይኖራል። ኣያቶቹ ሦስት ልጆች ነበሯቸው። ሁሉም ተሰውተዋል። የቀራቸው የልጅ ልጃቸው (እሱ ብቻ) ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት ልጁ ከመንግስት የወሰደውን ብድር መመለስ ስላልቻለ ወደ ሑመራ ኣከባቢ ይጠፋል። ኣያቶቹ ይታሰራሉ። መታሰራቸው ሰምቶ መጣ። ብዙ ነገር ደረሰበት። የጣብያ (ቀበሌ) ካድሬዎቹ ተቃወማቸው። ካድሬዎቹ ኣስተዳዳሪዎችም ኣባቱ የተሰዋበት ዓላማ ተቃወመ ብለው የኣከባቢው ሰዎች ከነሱ ቤተሰብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳያደርጉ ተነገራቸው። (ያ ሦስት ልጆች የተሰውበት ቤተሰብ እንዲገለል ተደረገ)። በኣሁኑ ሰዓት ግን ይሄን የማግለል ስትራተጂ እየተውት ይገኛሉ።

ምሳሌ ኣራት

በትግራይ ኣስተማሪዎች በገዢው ፓርቲ የሚደርሳቸው ኣስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ በደል በመቃወም የተለያዩ እርምጃዎች የሚወስዱበት ኣጋጣሚ ኣለ። ተደጋጋሚ የስራ ማቆም ኣድማ ይደረጋል። ኣንዳንዴም የመምህርነት ስራው ጠቅልሎ የመተው ነገር ኣለ። ለምሳሌ ትግራይ ምስራቃዊ ዞን የመማር ማስተማር ሂደቱ ተስተጓጉሏል። ነጋሽ ኣከባቢ በሚገኝ ኣንድ ትምህርትቤት ሁሉንም ኣስተማሪዎች (ዳይሬክተሩ ጨምሮ) ትምህርትቤቱ ዘግተው ጠፍተዋል። ግን የሚዘግበው ሰው የለም።

ምሳሌ ኣምስት

በኣንዳንድ ኢትዮዽያውያን የትግራይ ተወላጆች የኢህኣዴግ መንግስት በመደገፍ ኢትዮዽያውያንን ይበድላሉ ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ብዙዎች ይህንን እንደሚቃወሙ እንዴት ልንገራቹ?

ዓረና ትግራይ ፓርቲ በሺዎች የሚቆጠሩ ኣባላት እንዳሉት ሰምቻለሁ። እነዚህ ታድያ ህወሓት የሚቃወሙ ኣይደሉምን? ዴምህት የተባለ ኣማፂ ቡድን 60 ሺ ወታደሮች እንዳሉት ይነገራል። 60 ሺው ትክክል ላይሆን ይችላል። ግን ከ 20-25 ሺ ወታደር እንደሚኖረው ግን ይገመታል። እንዚህ ሁሉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው።

በ1997/98 ዓም ከሻዕቢያ ሬድዮ በሰማሁት መረጃ መሰረት (ቃለ መጠይቅ ሲደረግባቸው) ብዙዎቹ የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ኣባላት ነበሩ። ወደ ኤርትራ የገቡበት ምክንያት ሲያስረዱ በ1997 ና98 በነበረ የህዝብ ዓመፅ የተወሰደ እርምጃ በመቃወም ነበር። ስለዚ ሁሉም የትግራይ ህዝብ ገዢው ስርዓት ይደግፋል ብሎ ማሰብ ስሕተት ነው።

በሌላ በኩል ስናየው ደግሞ ስራ ነው። ኣንድ ሰው ስራ ፈልጎ ወደ ፖሊስነት ወይ ውትድርና ሊገባ ይችላል። የእንጀራ ጉዳይ ነው። ከገባ ታድያ (ደመወዙን ለማግኘት) የታዘዘውን መስራት ኣለበት። ካልሰራ ይባረራል፤ ከተባረረ መኖር ኣይችልም (ሌላ ስራ እስካላገኘ ድረስ)። ስለዚ ጠንክሮ ቢሰራ ኣይደንቀኝም።

ባጠቃላይ የትግራይ ህዝብ በሙሉ የህወሓት ደጋፊ ነው ማለት ኣይቻልም። ብዙ የሚቃወም ኣለ። ብዙ የሚጨቆን ኣለ። በትግራይ የሌለው ጭቆናን የሚያጋልጥ ነው። በሌሎች ኣከባቢዎች (ከትግራይ ውጭ) ሰው ሲታሰር ወይ ሲገደል የሚናገርለት ወይ የሚጮህለት ወገን ኣለው። በትግራይ ግን የለም። ኣንዱ ሲታፈን ሌላው ኣብሮ ዝም ይላል። ይሄ ነው ልዩነቱ እንጂ በትግራይ ጭቆና ስለሌለ ኣይደለም።

በመጨረሻም

እንደው ሁሉንም ትተን፣ የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ቢደግፍ (ከህወሓት ጎን ቢቆም) ችግሩ ምንድነው? ኣንድ ህዝብ የፈለገውን የመደገፍ ወይ የመቃወም መብቱ የተጠበቀ ነው። የትግራይ ህዝብ ህወሓትን (በፍላጎቱ ኣይደግፍም እንጂ) ቢደገፍ ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱ ‘ለምን ህወሓትን ትደግፋለህ?’ ሊባል ኣይገባም። ሌሎች ህዝቦች ህወሓትን የመቃወም መብት ያላቸው ያህል የትግራይ ህዝብም የመደገፍ መብት ኣለው።

ስለዚ (1) ሁሉንም የትግራይ ህዝብ (ብዙዎች እንደሚያስቡት) የህወሓት ደጋፊ ኣለመሆኑ እንዲታወቅ። (2) የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ይደግፋል ብሎ መውቀስም ተገቢ ኣይደለም።

It is so!!!
sorce. Abraha Desa fb .
 

No comments:

Post a Comment