No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Friday, 14 December 2012

አንድነት ስየን ሊሰርዝ ወይም ሊያስጠነቅቅ ይችላል የተሃድሶው ጅማሬ ይሆን?

በነባር አመራሮች ሲንከባለል የኖረው “የቅንጅት ወራሽ” አንድነት ፓርቲ ኃላፊነቱንና አመራሩን ለተተኪ ሳያስረክብ መቆየቱ በአብዛኛው ትችት ሲያሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በተለይም አቶ ስየ አብርሃ ፓርቲውን በተቀላቀሉ ማግስት በከፍተኛ ኃላፊነት መሰየማቸው አልተወደደለትም ነበር፡፡ በአንድነት ፓርቲ ውስጥም እስከመከፋፈል የዘለቀ ልዩነት መፍጠሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
አሁን የረገበ የሚመስለው የፓርቲው የውስጥ ልዩነት፤ በወቅቱ “ዝም አንልም፤ መርህ ይከበር” የሚሉት ኃይሎች የወሰዷቸውን ጽንፈኛ አቋሞች ብዙዎች የሚደግፉት ባይሆኑም ያነሱትን ጥያቄ አግባብነት ግን ይቀበላሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ይሁን በሌላ የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊመንበር የነበሩት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም “እኛ የማማከር አገልግሎት መስጠት አለብን፤ አመራሩን መያዝ ያለበት አዲሱ ትውልድ ነው” በማለት ራሳቸውን በቅሬታ ከፓርቲው ማግለላቸው ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ የሚገኙት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳም ከፓርቲው ጋር ያላቸው ግንኙነት በይፋ በሚታወቅ ደረጃ ላይ አይገኝም፡፡ እርሳቸውን ተከትለው ወደ አሜሪካ የመጡት አቶ ስየም በተየያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በፓርቲው ስም ንግግር ሲያደርጉና የራሳቸው እምነት ሲያንጸባርቁ የሚታዩትን ያህል ወ/ት ብርቱካን ከአንድነት ጋር በተቆራኘ ጉዳይ መድረክ ላይ አለመታየታቸው ከፓርቲው ጋር ያላቸውን ግኑኘነት ግልጽ እንዳልሆነ አመላካች ነው፡፡ ወ/ት ብርቱካን ወደ አሜሪካ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በአጠቃላይ ከትግሉ ጎራ እንዳልራቁ ቢናገሩም ሲመሩ የነበሩትን ፓርቲ በተመለከተ ዝምታን መምረጣቸው የዳያስፖራውን የፖለቲካ ትግል ይመራሉ ብሎ ተስፋ በጣለባቸው ደጋፊያቸው ዘንድ ይፋ ያልወጣ ግን በብዛት ያነጋገረ ጉዳይ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ በፓርቲው ላይ ዙሪያ በሚነሱበት ወቅት ፓርቲው ራሱን ለሹምሽር ማዘጋጀቱ በሚደረገው ሹምሽርም አቶ ስየን ጨምሮ ከም/ቤት የሚባረሩ እንዳሉ ዘወትር ረቡዕ ከአዲስአበባ የሚታተመው ሰንደቅ ጋዜጣ አዲስ ወሬ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡
ወ/ት ብርቱካን ሊ/መንበር ሆነው መመረጣቸውን በግልጽ የተቃወሙትና ለበርካታ ጊዜያት ራሳቸውን ከፓርቲው አግልለው ቆይተው የተመለሱትና ከፓርቲው “በክብር ተሰናብተው” የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው እንደገና ወደ አመራር እንደሚመጡ ሰንደቅ በዘገባው ፍንጭ ሰጥቷል፡፡
በፓርቲው እውቅና ለአንድ ዓመት ለትምህርት ወደ አሜሪካ የሄዱት አቶ ስየ ትምህርታቸውን ባለፈው ግንቦት አካባቢ ቢያጠናቅቁም እስካሁን ወደ አገር ቤት አልተመለሱም፡፡ ሆኖም በቅርቡ የመድረክ አመራሮች በአሜሪካ ባካሄዱት ስብሰባዎች ላይ አቶ ስየ በአጋርነት ሲሳተፉ ቢቆዩም በአንድነት ፓርቲ ም/ቤት ስብሰባ ላይ በተደጋጋሚ አለመገኘታቸው በርካታዎችን ከማሳሰብ አልፎ ቅሬታንም እንደፈጠረ ሰንደቅ ዘግቧል፡፡ በመሆኑም ሁኔታው ሕገ-ደንብ የመጣስ ሆኖ በመገኘቱ ከም/ቤት አባልነት እንደሚያሰርዝ ሰንደቅ የቅርብ ምንጮቹን ጠቅሶ አስታውቋል፡፡ ሆኖም የመጨረሻው ውሳኔ እሁድ የሚታወቅ ሲሆን ይህም ሰብሳቢው በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ የሚንተራስ እንደሆነ ጨምሮ ዘግቧል፡፡
ሁኔታው የሕገ-ደንብ ሳይሆን በፓርቲው ውስጥ ገና ከጅምሩ ያልተቋጨ የሥልጣን ሽኩቻና ያለመተማመን ነጸብራቅ ነው የሚሉ ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጪዎች የእሁዱ ውሳኔ በፓርቲው ላይ መጠነኛና ጊዜያዊ መልክን የመቀየር ለውጥን እንጂ ተፈላጊውን ተሃድሶ እንደማያመጣ ይናገራሉ፡፡ በተለይ በቅርቡ ሊ/መንበሩ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “የግል እምነቴ ነው” በማለት ለውይይት መነሻ ባቀረቡት ጽሁፍ ተሃድሶ የማድረግን አስፈላጊነት በማጉላትና እስካሁንም ይህ አለመደረጉ ተፈላጊውን ለውጥ በአገራችን ላይ ሊያመጣ እንዳላስቻለ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ሆኖም ተሃድሶው እንዴትና ከየት እንደሚጀመር አልተናገሩም፡፡ በካቢኔ ሹምሽርነት የተጠራው የእሁዱ ስብሰባም የዚህ ተሃድሶ መጀመሪያ ይሁን እስካሁን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡
በቅርቡ ቀድሞ የቅንጅት እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊ በሆኑ የተቋቋመው ሰማያዊ ፓርቲ ወደፊት ምን ያህል እንደሚዘልቅና የት ድረስ እንደሚራመድ ባይታወቅም እያካሄደ ያለው ያልተለመደ የፖለቲካ አሠራር የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ የመጣ ሆኗል፡፡ የቀድሞ የፖለቲካ አመራሮችን “በአማካሪነት” በማቀፍ በተለይ ፓርቲው በወጣት አመራሮች የተቋቋመና እየተመራ ያለ መሆኑ በአገር ውስጥ ያሉት ነባር ፓርቲዎች ያላስመዘገቡትን ውጤትና ያላመጡትን ተሃድሶ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ እየተገበረና እየሄደ ያለው መንገድ በሌሎች ዘንድ የተሃድሶን አስፈላጊነት እንዲያስቡ ያስገደደ ነው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

No comments:

Post a Comment