No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Monday 5 November 2012

መብት ጠያቂዎችን በአሸባሪነት መፈረጅ የሕግ የበላይነትን ይንዳል!


ድምፃችን ይሰማ
በዴሞክራሲያዊ ስርአት ውስጥ ዜጎች መሪያቸውን ከመምረጥ ባለፈ በአመራሩ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን የመከታተልና የማሳወቅ፣ ለመብቶቻቸውም የመታገል ሉአላዊ መብት አላቸው፡፡ የሚደርሱባቸውን አስተዳደራዊ በደሎች በሰላማዊ መንገድ መቃወምና እንዲስተካከልላቸውም አጥብቆ መጠየቅ አሌ ከማይባሉ መሰረታዊ መብቶቻቸው አንዱ ነው፡፡ ይህንን መርህ ህገ መንግስታችን በግልጽ ያጸደቀው መሆኑም ያለጥርጥር ይታወቃል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ከሀምሌ 2003 ጀምሮ በመንግስትና በመጅሊስ ጥምረት በግድ እየተጫነበት የነበረውን አዲስ አህባሽ የተባለ አንጃ ‹‹አልቀበልም›› በማለት የችግሩ ምንጭ የሆነውን መንግጅሊስን (የመንግሰትና የመጅሊስ ይፋዊ ጥምረት) በመቃወም ያደረገው ትግል ከዚህ የዜጎች ሉአላዊ መብት የመነጨ ነበር፡፡ ይህንንም ከየካቲት 26 በፊት በነበረው ወቅት የመንግስት ባለስልጣናት በግልጽ እውቅና ሲሰጡት ታይተዋል፡፡

ጥያቄው የሚሊዮኖች እንደመሆኑ ሁሉም መንግስትን ሄዶ ማናገር ስለማይችል ከመካከሉ አንደበተ ርቱእና ለህዝቡ አሳቢ የሆኑ ግለሰቦችን በፔቲሽን የወከለው ህዝበ ሙስሊም ‹‹ጥያቄያችንን መመለስ ወደሚችለው መንግስት አድርሱልን!›› ከሚል ተማጽኖ ጋር ሶስት ጥያቄዎችን አስይዞ ወደመንግስት ላካቸው – ዛሬ በሽብርተኝነት የተከሰሱትን ብርቅዬ መሪዎቻችንን!ተወዳጅ ኮሚቴዎቻችን ዛሬ እንደወንጀል ከመቆጠሩ በፊት ይህንን ከህዝብ የተወከሉበትን የመብት ጥያቄ ይዘው ከከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ተቀምጠዋል፡፡ የጥያቄዎቹ አቀራረብ ሰላማዊነትም በባለስልጣናቱ አፍ እንዲወደሱ አስችሎ ነበር፡፡
በየካቲት 26 አክብሮ ያወያያቸውን ሰዎች ከየካቲት 26 በኋላ ‹‹ጸረ ሰላም፣ ሁከት ፈጣሪ፣ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው›› እያለ መፈረጅ የጀመረው መንግስት ግን ይህንን የሚያደርገው በምን አመክንዮ ላይ ተመስርቶ እንደሆነና ትናንት ‹‹ለሰላማዊነታችሁ እናመሰግናለን›› የተባሉ ሰዎች ከምኔው ወደ ‹‹ሁከት ፈጣሪነት›› እንደለተለወጡ ለህዝብ ግልጽ አልነበረም፡፡ መሪዎቻችን በ 26 የካቲት/2003 የተሰጣቸውን ድፍንፍን ያለ መልስ እንዲሁ ተቀብለው ቢያቆሙ ኖሮ ይህ ሁሉ በሽብርተኝነት መፈረጅ ባልገጠማቸው ነበር፡፡ ‹‹ጥያቄያችን በተገቢው መንገድ አልተመለሰም፤ አሁንም በደንብ መወያየት አለብን›› በማለታቸው ብቻ ጽንፈኛ ከመባል ጀምሮ በጸረ ሰላምነት እስከመፈረጅ፣ እስከመከሰስም ደርሰዋል – ዴሞክራሲ አለ በሚባልባት አገር!
ውድ ኮሚቴዎቻችን በመብት ጥየቃው ሂደት ሁሉ ከጅማሮው አንስቶ ሰላማዊነትን እና ከሁከት መቆጠብን ብቸኛ አማራጭ አድርገው ነው የያዙት፡፡ ለሁከት ምንም አይነት ክፍተት አልሰጡም፡፡ በስራቸው ሚሊዮኖን ሙስሊሞች ዓላማ አንግበው እየታገሉ የነበረ ቢሆንም እነሱ ግን ወደሃይል ተጠቃሚነት እርምጃ ፈጽመው አልገቡም፡፡ የህዝብ ድጋፍ፣ ስሜትም ሆነ ጥንካሬ ከሰላም አንድ ስንዝር አላራቃቸውም፡፡ ከሃይል ይልቅ መንግስትን መማጸንን፣ ነጭ ባንዲራ ማውለብለብን፣ የድምጽ ተቃውሞ ሲገፋ የዝምታ ተቃውሞን ነው የመረጡት፡፡ ሺዎች ተንበርክከው እያለቀሱ፣ ‹‹እጆቻችን ታስረዋል›› የሚል ምልክት እያሳዩ፣ የሰላም ምልክት የሆነውን እራፊ ነጭ ጨርቅ እያውለበለቡ፣ አንዳንዴም ተደብድበው ማንንም ሳይደበድቡ ቤታቸው በሰላም እየገቡ የሚታዩበትን ተቃውሞ ‹‹ሽብር›› ሲሉ መፈረጅ የክፍለ ዘመኑ ስህተት አይደለምን? ይህ አይነቱ ተቃውሞ ‹‹ሽብር›› ተሰኝቶ መሪዎቹን ዘብጥያ ካስወረደ ያ ሁሉ ሁልቆ መሳፍርት ህዝብ ድንጋይ ወርውሮ፣ ንብረት አውድሞ ቢሆን ምን ስያሜ ይሰጠው ነበር? ‹‹ሽብርተኛ›› ስለሰላም መስበክ የጀመረው መቼ ነው? ‹‹ሰላም ሰባኪ ሽብርተኛ›› በእውኑ አለም እንዴት ሊኖር ይችላል? አገር የምትመሩ ሰዎች ስለምን ይሆን ከመቃብር በላይ የሚውል ታሪካችሁን ክፉኛ የምታበላሹት?
መብት ጠያቂዎችን በአሸባሪነት መፈረጅ የሕግ የበላይነትን ይንዳል!ውድ ኮሚቴዎቻችን ላይ ‹‹እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም ዶልታችኋል›› የሚል የሀሰት ክስ መቅረቡም ሌላው ተአምር ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ እምነቱን የመምረጥ መሰረታዊ መብቱን እንኳን ተገፎ ‹‹በግድ ያመጣንልህን ሃይማኖት ተቀበል፤ አህባሽ ሁን›› እየተባለ ባለበት፣ በየትምህርት ተቋማቱ ‹‹ወይ ከትምህርት ወይ ከእስልምና አንዱን ምረጥ›› እየተባለ ባለበት ተጨባጭ ‹‹እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም እየሰራ ነው›› ብሎ ማሰብ እንዴት ከአንድ ጤነኛ አእምሮ ይፈልቃል? ‹‹ኧረ ህገ መንግስታዊ መብቴን አክብሩልኝ!›› እያለ አመት ሙሉ አደባባይ የዋለ ህዝብ ጥያቄው በሸሪአዊ መንግስት ማቋቋም የሚተረጎመው በምን አይነት ሀሰተኛ ጆሮዎች ተሰምቶ ነው?ዘመኑ እኮ የዲጂታል ዘመን ነው! መሪዎቻችን ያደረጓቸው ህዝባዊ ንግግሮች እና የሰጧቸው መግለጫዎች በሺዎች ሞባይሎች እና መቅረጸ ድምጾች ውስጥ አሉ – ልባችን ውስጥ ከመታተማቸው ሌላ! በተጨማሪም እንቅስቃሴውን ክርስትያን ወንድሞቻችን እና ሌሎችም ያውቁታል፤ ደግፈውታልም፡፡ የእምነት ተቋማትና የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች የድጋፍ መግለጫ ሰጥተዋል፤ እየተፈጸመ ያለው ግፍ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡ የዚህን አለምአቀፍ ክብር ያገኘ ታሪካዊ እንቅስቃሴ መሪዎች በሽብርተኝነት መክሰስ በምንም አይነት መልኩ ተቀባይነት አያገኝም፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ካላመነበት፣ ህዝበ ክርስትያኑም ካላመነበት፣ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችም ካላመኑበት… ፕሮፓጋንዳው የሚሰራው ለማን ነው?
መንግስታችን የመብት ጥያቄ በቀረበለት ቁጥር በሽብር መፈረጁ በራሱ ‹‹ሽብር›› የሚባለው ነገር እንደስጋት መቆጠሩን እያጠፋው ነው ያለው፡፡ ‹‹ሽብር›› አደጋ መሆኑ ቀርቶ የመቀላለጃ ስም መሆን ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ጓደኛሞች ‹‹እሺ አሸባሪው!›› ሲባባሉና ሲቀላለዱ መስማት ያልተለመደ አይደለም፡፡ እንደውም በአገራችን ተጨባጭ ‹‹አሸባሪ›› እያለ ከሚፈርጀው አካል ይልቅ ‹‹ሽብርተኛ›› የተባሉት በህዝብ ዘንድ የተሻለ የሚታመኑበት ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ይህ የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ ውጤት ነው፡፡ ሊስተካከልም ይገባዋል፡፡
እንደ እስከዛሬው ሁሉ ዛሬም መፈክራችን አልተለወጠም፡- ‹‹መሪዎቻችን የሰላም አምባሳደሮች እንጂ ሽብርተኞች አይደሉም! የሀሰት ክስ አይገዛንም! መንግስት ፍረጃውን ትቶ ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎቻችንን ይመልስ! ድምጻችን ይሰማ! ኮቴዎቻችን እና መምህራኖቻችን፣ አርቲስቶቻችን እና ጋዜጠኞቻችን ይፈቱ!›› እንላለን፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊም!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment