No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Sunday, 2 February 2014

የድንጋይ ዉርወራ ፖለቲካ በዓዲግራት by Abraha Desta


ዓረና-መድረክ ለጥር 18, 2006 ዓም በዓዲግራት ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ መጥራቱ ይታወሳል። ዓዲግራት ከተማ ከመቐለ በስተሰሜን በኩል በ120 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። የስብሰባው ዓላማ ከዚህ ቀደም በዉቅሮ፣ ማይጨው፣ ዓብይ ዓዲና ሽረ ከተሞች እንዳደረግነው ሁሉ የዓረና ፓርቲ ዓላማዎችና ፖሊሲዎች ከህዝብ ጋር ለማስተዋወቅ እንዲሁም ህዝብን ፖለቲካ ማስተማርና ማደራጀት ነበር።

ስብሰባ ለማካሄድ ተፈቀደልን። የማዘጋጃቤት አዳራሽም ተሰጠን። ስብሰባ ለማድረግ ማስፈቀድና አዳራሽ ማግኘት በቂ አልነበረም። ህዝብ በስብሰባው እንዲሳተፍ የጥሪ ወረቀት መበተን ነበረብን። በማይክሮፎንም ማወጅ ነበረብን። ዓረና በዓዲግራት ከተማ ስብሰባ መጥራቱ ለማብሰር የዓረና ፓርቲ ልኡክ ወደ ዓዲግራት ከተማ ሐሙስ ጥር 15, 2006 ዓም ተላከ።

ዓርብ ጥር 16, 2006 ዓም ጧት የልኡካን ቡድኑ ለሁለት ተከፍለው ዓዲግራት አቅራቢያ በሚገኙ የዕዳጋ ሐሙስና የፋፂ ከተሞች የስብሰባው ቅስቀሳ አደረጉ። ወደ ፋፂ የተላከው ቡድን የተሳካ ቅስቀሳ አድርጎ በሰላም ወደ ዓዲግራት ሲመለስ በዕዳጋ ሐሙስ የነበረ ቡድን ግን “ሕጋዊ አይደላችሁም” በሚል ሰበብ የዓረና ፓርቲ የህዝብ ግንኙት ሐላፊ የሆነው አቶ ዓምዶም ገብረስላሴና መምህር ሃይለ ገብረፃዲቅ ታሰሩ። ከሰዓታት እስር በኋላ ተፈቱ። ወደ ዓዲግራትም ተመለሱ።


ዓርብ ከሰዓት በኋላ እኔና አቶ አስገደ ገብረስላሴ ዓዲግራት ከተማ ገባን። ሁላችን በዓዲግራት ተሰባሰብን። ለሁለት ተከፍለን ቅስቀሳ ለመጀመር አንድ ቡድን ከፒያሳ ወደ መነሃርያ አቅጣጫ ሲንቀሳቀስ ሌላው ደግሞ ወደ ስታዲዮም (እንዳ ምስዮን) አከባቢ ተንቀሳቀሰ። ወደ መነሃርያ አከባቢ የተንቀሳቀሰ ቡድን በዓዲግራት ህዝብ ብዙ ድጋፍ አገኘ። ህዝቡ የሚበላና የሚጠጣ ያቀርብልን ነበር። ወረቀት በመበተንም ይተባበረን ጀመር። ይህ ሁሉ ሲደረግ የከተማው ሰራተኞች፣ የደህንነት ሰዎች፣ የፖሊስ አባላት እየተከታተሉ ያዩ ነበረ።

ብዙ ሳይቆይ ህፃናት መረበሽ ጀመሩ። ለህዝብ የተበተነ ወረቀት እየነጠቁ መቅደድ ጀመሩ። ለዓረና አባላትም መሳደብ ጀመሩ። የዓረና አባላትም ቅስቀሳቸው ቀጠሉ። ልጆቹ በዓረና አባላት ላይ አክታ መትፋትና አፈር መበተን ተያያዙት። ልጆቹ የዓረና አባላትን ከበው የጥሪ ወረቀቱ ለህዝብ እንዳያደርሱ አደረጉ።

የዓዲግራት ወጣቶችም የሚረብሹ ወጣቶችን ለመበተን ሞከሩ። አልተሳካም። ምክንያቱም ልጆቹ በባለስልጣናቱ ይደገፉ ነበር። የቀበሌ ካድሬዎች አፈርና ድንጋይ ማቀበል ጀመሩ። የዓዲግራት ሰዎች ረብሻው የተቀነባበረ መሆኑ ሲረዱ የዓረና አባላት ለማዳን በባጃጅ ከአከባቢው ወጥተው ወደ ፖሊስ ጣብያ እንዲሄዱ ለማድረግ ጥረት ጀመሩ። ለረብሻው የተደራጁ ወጣቶች ደግሞ ባጃጆችን በመክበብ የዓረና አባላትን እንዳይወጡ አደረጉ። በዚህ ግዜ በዓዲግራት ወጣቶችና ለረብሻው በተደራጁ ሃይሎች መካከል ግጭት ተፈጠረ። የዓዲግራት ወጣቶች አሸነፉና ረባሺዎቹ ህፃናት ትንሽ ከፈቱና የዓረና አባላት ካከባቢው ወጥተው ወደ ፖሊስ ጣብያ አመሩ። አንድ የዓረና አባል ግን እዛው ቀረ። ህፃናቱ ሊደበድቡት ሲሉ የዓዲግራት ወጣቶች አዳኑት። እሱን አጅበው ሳይደበደብ ፖሊስ ጣብያ አደረሱት። ፖሊስ ጣብያ ሂደው ግን ሰሚ አላገኙም። በተጨማሪም እየተከታተሉ የነበሩ የከተማው ባለስልጣናት የዓረና አባላትን ይተባበሩ የነበሩ የዓዲግራት ወጣቶችን ያስፈራሩ ነበር።

መነሃርያ አከባቢ የነበሩ የዓረና አባላት በባጃጆች ካከባቢው ሲርቁ የረብሻ ቡድኑ ወደ ሌላኛው የዓረና ቡድን መጣ። እንዳሚስዮን አከባቢ የጥሪ ወረቀት እያደልን ነበር። ህፃናቱ የጥሪ ወረቀቱ ለህዝብ እንዳናድል ከበቡን። መሳደብ፣ አክታ መትፋትና አፈር መበተን ጀመሩ። ስራችን አቁመን ሁኔታውን ስንገነዘብ ህፃናቱ በጣም ብዙ ናቸው። ብዙዎቹም ሁኔታው ለማየት የተቀላቀሉ ይመስላሉ። በድራማው ግራ የተጋቡ ናቸው።

በህፃናት ተከበናል። ህፃናቱ ከ12-16 ዓመት ይሆናሉ። ከህፃናቱ በኋላ የቀበሌ ካድሬዎች አሉ። ከቀበሌ ሰራተኞቹ ጎን ሲቪል የለበሱ ፖሊሶች ነበሩ። ከፖሊሶቹ ጎን ብዙ ወጣቶች ነበሩ። ወጣቶቹ የህወሓት የደህንነት ተጠሪዎች መሆናቸው በኋላ ተነግሮናል። ከደህንነት ሐላፊዎቹ ጎን የከተማውና የምስራቃዊ ዞን አስተዳዳሪዎች ነበሩ። የከተማና የዞን አስተዳዳሪዎች መሆናቸው ያወቅኩት ማታ ቢሮአቸው ገብተን ሲንነጋገር ነበር።

ብዙ ሳንቆይ ልጆቹ ከመሳደብ፣ ከመትፋትና አፈር ከመበተን ወረቀቶቻችን፣ ሞባይሎቻችን፣ ማይክሮፎኖቻችንና ጠቅላላ ንብረታችን ወደ መንጠቅ ተሸጋገሩ። የተደራጁ ወጣቶች (ከ25-30 ዓመት ዕድሜ የሚገመቱ) ከህፃናቱ ጋር በመሆን ልብሶቻችን መቅደድ፣ የያዝነው ሞባይልና ማይክሮፎን መስበር እንዲሁም ፊታችን ላይ አክታ መትፋት ጀመሩ። ከደብዳቢዎች መሐል አንድ ደንብ የለበሰ ፖሊስ አለ። ስርዓት እንዲያስይዝልን ተማፀነው። ሊያናግረን ፍቃደኛ አልነበረም። ግን ዝም ብሎ ይከተለናል። ከደብዳቢዎቹ ጋር አብሮ ይንቀሳቀሳል። ልጆቹን ያበረታታል።

ፖሊስ ስርዓት እንዲያስይዝልን ጠይቀን ፍቃደኛ ሳይሆን ሲቀር የተመለከቱ ህፃናት እኛን በድንጋይ መውገር ጀመሩ። የቀበሌ ሰራተኞች (ሴቶች ናቸው) ለህፃናቱ ድንጋይና አፈር ያቀብሉ ነበር። የከተማው ሰራተኞች (ከንቲባው ጨምሮ) ከህፃናቱ ጋር ይገናኛሉ። ባለስልጣናቱ ለህፃናቱ ትእዛዝ የሚሰጡ ይመስላሉ። ህፃናቱም በድንጋይ የመደብደብ ተግባራቸው አጠናክረው ቀጠሉ። እነ አቶ ከንቲባም በመኪና ዉስጥ ተቀምጠው ትእይንቱ በካሜራ ይቀርፁ ነበር። ግብረ መልስ አልሰጠንም። ዝም ብለን ተደበደብን።

ወጣቶቹ ደብዳቢዎች ከድንጋይ ወደ ቦክስ (ቡጢ) ተሸጋገሩ። መጀመርያ በቦክስ የተመታው አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ ነበር። አራት የዓዲግራት ኗሪዎች በግጭቱ ገብተው አቶ ዓምዶምን ከደብዳቢዎች አዳኑት። አቶ አስገደ ገብረስላሴ የህፃናቱ የድንጋይ መጫወቻ ሆነ። ብዙ የዓዲግራት ወጣቶች እኛን ለማዳን ጣልቃ ገቡ። ሁኔታው ትንሽ ተረጋጋ። እዛው የነበረ ፖሊስ ሊተባበረን ስላቻለ ወደ ፖሊስ ጣብያ መሄድ እንዳለብን ገባን። ግን እንዴት እንሂድ?!

አንድ በሁኔታው የተገረመ ባለባጃጅ መጣ። “ና ግባ” አለኝ። ወደ ፖሊስ ጣብያ እንዲወስደኝ ነገርኩት። ወደ ባጃጁ ስጠጋ እኔን ለመደብደብ አምስት ወጣቶች መጡ። ሦስቱ ለመምታት አስበው አልተሳካም። ሦስቱን ስከላከል ሁለቱ ግን መቱኝ። ትንሽ ወደ መራቅ አሉና ክፍተት ሳገኝ ወደ ባጃጁ ገባሁ። እስክገባ ድረስ ባለባጃጁ ከህፃናቱ ድብደባ ይከላከልልኝ ነበር። ባጃጅ ዉስጥ ከገባሁ በኋላ ባለባጃጁም እኔን ለመውሰድ ሲገባ ህፃናቱ አፈር ይዘው በዓይኔና ጀሮዬ ይበትኑ ነበር። በሌላኛው የባጃጇ በር ደግሞ ትላልቆቹ ወጣቶች እኔን ለመደብደብ ሞከሩ። ግን የግራ በሩ አይከፈትም ነበር። መስተዋቱ ሰበሩት። እኔን ለመምታት ሲሉ ባጃጇ ተሰባበሯት። ትንሽ ከደበደቡኝ በኋላ የዓዲግራት ወጣቶች መጥተው ደብዳቢዎቹን ያዙዋቸው።

ባለ ባጃጁ ተነሳ። ወደ ፖሊስ ጣብያ ወሰደኝ። የከተማው የፖሊስ አዛዥ አግኝቼ “ሰው እየተደበደበ ነው፤ እርዱን!” አልኩት። ይሳለቅብኝ ጀመር። እያወራሁት እያለሁ እኔን ትቶ ከሌሎች የደህንነት ሰዎች ጋር ያወራል። “አንተንኮ ነው እያናገርኩ ያለሁት” አልኩት በንዴት። “ወደኛ ምን ልታደርጉ መጣቹ” አለኝ። ወደ ሌላ ፖሊስ ሄድኩና “ኧረ ሰው እየሞተ ነው። አድኑን በኋላኮ ትጠየቃላቹ!” እያልኩ ብዙ አወራሁ። ፖሊሱ ዝም ብሎ ያዳምጠኛል። መልስ ግን አይሰጠኝም። በግምት ሃያ ደቂቃ ለሚሆን ግዜ መልስ ሳይሰጠኝ ቆየ (አስቡት በዚህ ግዜ አቶ አስገደ፣ አቶ ዓምዶምና መምህር ሃይለ በዱርየዎቹ እየተደበደቡ ነው)። ከተወሰነ ግዜ በኋላ ለአንድ ፖሊስ ጠርቶ “ና ከሱ ጋር ሂድ” አለው። የታዘዘው ፖሊስም “መሳርያ የለኝም” አለ። “ዝም ብለህ ሂድ!” “ዝም ብዬማ አልሄድም መሳርያ ያስፈልገኛል…” ወዘተ እየተመላለሱ ተነታረኩ። መጨረሻ ሁሉም ነገር ትተውት ወደ ቢሮአቸው ገቡ።

እኔ ከፖሊሶች ጋር ስነታረክ እነ አስገደና ዓምዶም በድንጋይ እየተደበደቡ ከእንዳሚስዮን ፒያሳ ቴሌ ገቡ። ፒያሳ አከባቢ ሲደርሱ ድብደባው እየከበደ ሲመጣ ብዙ የዓዲግራት ኗሪዎች በጉዳዩ ገብተው ለማዳን ሞከሩ። ደብዳቢዎቹን አባረሩልን። አጋጣሚው ተጠቅመን ወደ ምስራቃዊ ዞን አስተዳደር ቢሮ ቅጥር ግቢ ገባን። ህዝቡ ተመለሰ። ደብዳቢዎቹ ግን እኛን ተከትለው ገቡ። በቅጥር ግቢው የዞኑ የህወሓት አስተዳዳሪዎች ነበሩ። ዱርየዎቹ ድንጋይ መወርወር ሲጀምሩ ባለስልጣናቱ ወደ ቢሮአቸው በመግባት ከፎቅ መስኮት ከፍተው ድብደባውን ይከታተሉ ነበር። እኛ ስንደበደብ እነሱ ይስቁ ነበር። የደቡብ አፍሪካውያኑ የአፓርታይድ ገዢዎችን የጭቆና ስልት አስታወሱኝ።የአስተዳዳሪዎቹ ሁኔታ ገረመንና ለመቅረፅ ሞከርን።

ከተወሰነ ግዜ በኋላ ሁኔታው ተረጋጋ። የዞኑ ባለስልጣናት በአቶ ማሞ (የምስራቃዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ) ቢሮ ሰበሰቡን። “እያያቹ አስደበደባችሁን” አልናቸው። የዞን አስተዳዳሪዎች ደግሞ “ህፃናት ልጆች ደብድባችኋል፤ ትከሰሳላቹ” አሉን። የዞኑ የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ገብረሂወት ሐጎስ ደግሞ ቅስቀሳ እንደምታደርጉ ለኛ አላሳወቃችሁም። ለዚህም ነው ጥበቃ ያላደረግንላቹ” አለ። እኛም ለከተማው ከንቲባ ፅሕፈትቤት ማሳወቃችንና እንደተፈቀደልን ነገርነው። አቶ ደሳለይ ተፈሪ የተባለ የዞኑ የህወሓት የፕሮፓጋንዳ ሐላፊ ህፃናቱ የፈለጉትን የማድረግ መብት እንዳላቸውና ማንም ሊያስቁማቸው እንደማይችል አስፈራራ። አልማዝ ነጋ የተባለች የዞኑ የህዝብ ግንኙነት ሐላፊም “ልጆቹ የረበሿቹ ያለፍላጎታቸው ስለቀረፅዋቻቸው ነው” ስትል አከለች።

ብዙ ከተጨቃጨቅን በኋላ አቶ ማሞ የዞኑ አስተዳዳሪዎች ባሉበት ስንደበደብ በካሜራ መቅረፃችን ለማስረጃ እንዳንጠቀምበት በመስጋት “ያለ ፍቃዳችን ስለቀረፁን እዚህ ያሉ ሁሉም ተይዘው የቀረፁትን ቪድዮና ያነሱትን ፎቶ እንዲሰረዝ …!” በማለት ለፖሊስ አዛዡ ትእዛዝ አስተላለፈ። ሞባይሎቻችንና ካሜራዎቻችን በፖሊስ ተይዘው እኛም በእሱር ወደ ፖሊስ ጣብያ ተወሰድን። ሞባይሎቻችንና ካሜራዎቻችን በአንድ የህወሓት ካድሬ የሆነው (የህወሓት የወጣቶች ጉዳይ ኤክስፐርት) ያለፍቃዳችን ተፈተሹ። የሚፈተሽ ፈትሸው፣ የሚሰረዝ ሰርዘው ንብረታችንን መለስሉን። የድብደባው ማስረጃዎች አጠፉብን።

ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት አከባቢ ከፖሊስ ጣብያ ወጣን። አቶ አስገደና አቶ ዓምዶም ሆስፒታል ተወስደው ስለነበር ጠበቅናቸው። ለግዜው ሙሉ የሕክምና አገልግሎት እንደማያገኙ ስለተነገራቸው ለቅዳሜ ጧት ተቀጥረው ተመለሱ። ወደያዝነው አልጋ ገብተን ስናርፍ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አልጋችን በ አነፍናፊ ዉሻ ተፈተሸ።

ቅዳሜ ጧት አስገደና ዓምዶም ህክምና ለማግኘት ሆስፒታል ሄዱ። ሌሎቻችን ቅስቀሳ ጀመርን። ቅስቀሳ ስንጀምር ለፖሊስ ማሳወቅ አለብኝ ብዬ ፖሊስ ጣብያ ጎራ አልኩኝ። ፖሊስ ጣብያው ስገባ ግን አንድ የሚገርም ነገር አየሁ። ዓርብ ከሰዓት ከደበደቡኝ ዱርየዎች አንዱ ፖሊስ ሁኖ የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሶ ፖሊስ ጣብያው ዉስጥ አገኘሁት። ዝም ብዬ ወደ ጓደኞቼ ተመለስኩ። በሰላም ቀሰቀስን። የዓዲግራት ወጣቶች ወረቀት መበተኑ እያገዙን በተወሰነ ግዜ ብዙ ቦታዎች ለማዳረስ ሞከረን።

ቅዳሜ ከቀኑ ስድስት ሰዓት አከባቢ ሲሆን ልጆቹ እንደገና መረበሽ ጀመሩ። ባለ ባጃጅ የዓዲግራት ወጣቶች ለህፃናቱ እየደበደቡ በተኗቸው። ፖሊሶችም ለባለባጃጆች ማስፈራራትና ማስጠንቀቅ ጀመሩ። ሁኔታው ስላላማረን ለምሳ ብለን ቅስቀሳው አቆምን። ለምሳ ስንገባ ድርየዎቹ ተደራጅተው መጥተው ስንበትነው የነበረው ወረቀት ነጠቁን። ሦስት የዓዲግራት ከተማ ወጣቶች ተናደው ከዱርየዎቹ ጋር ተጣሉ።

ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ቅስቀሳው ለማካሄድ ስንንቀሳቀስ ገና ሳንጀምር የተደራጁ ወጣት ደብዳቢዎች የድንጋይ ናዳ አወረዱብን። አቶ አስገደ ገብረስላሴና አቶ ስልጣኑ ሕሸ በድንጋይ ተመቱ። የዓዲግራት ወጣቶች አዳኑን። ዱርየዎቹ እኛን ሲደበድቡ የዓዲግራት ወጣቶች ደግሞ እነሱን መደብደብ ጀመሩ። ዱርየዎቹ ሩጦው አመለጡ። አስገደ ወደ ፖሊስ ጣብያ ደወለ። ሁኔታው ካስረዳቸው በኋላ ስልኩ ተዘጋ። ደግመን ብንደውል ስልኩ ዝግ ሆነ።

ወደ ፒያሳ ተመለስን። ዱርየዎቹ ተከተሉን። የዓዲግራት ህዝብ ተሰብስቦ እያየ ዱርየዎቹ እኛን መደብደብ ጀመሩ። ባለስልጣናቱም እየተከታተሉ ይቀርፃሉ። ሲጨንቀን ወደ ዞን ፖሊስ ፅሕፈትቤት ቅጥር ግቢ ለመግባት ሞከርን። እኛ ለመግባት ስንሞከር የምስራቃዊ ዞን የህዝብ ግንኙነት ሐላፊዋ ወይዘሮ አልማዝ ነጋ አገኘናት። ለጥበቃው “እንዳታስገባቸው!” አለችው። ከዱርየዎቹ ድብደባ ለማምለጥ ወደ ዞን ፖሊስ ፅሕፈትቤት ለመግባት ስንጥር የፅሕፈትቤቱ ጥበቃ ወደ ህንፃው እንዳንገባ ከለከለን፣ እሱም በዱላ ደበደበን። የዞኑ ፖሊስ አዛዦች ከፎቅ እያዩን ነበር።

ዝም ብለን ተደበደብን። ቪድዮ ይቀርፁ የነበሩ ተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ። ለካ የነሱ ዓላማ እኛ ስንደበደብ ግብረመልስ እንድንሰጥና ህፃናቱን ስንደበድብ ለመቅረፅና ከህፃናት ጋር እንደተጣላን በማስመሰል ለማቅረብ ነበር። ሳይሳካላቸው ሲቀር አንዲት ሰለማዊት ገብሩ የተባለች የቀበሌ ካድሬ “የእህቴ ልጅ በዓረናዎች ተደበደበ” በሚል ሰበብ ወደ ፖሊስ ጣብያ ለመውሰድ ፈለገች። እኛ ግን ወደ ፖሊስ ጣብያ የሚወስደን አጥተን ነበር የምንደበደበው። ፖሊሶች ወደ ፖሊስ ጣብያ ለመውሰድ ፍቃደኛ አልነበረም፤ ልጆች እየመታን እስክንቀረፅ ድረስ።

ሲጨንቃቸው አንድ የዓዲግራት ኗሪ ወደ ፖሊስ ጣብያ ሊወስዱን ፈለጉ። ሁኔታውም አረጋጉ። ወደ ፖሊስ ጣብያ ገባን፤ እኛንም ደብዳቢዎቻችንም። ፖሊሶቹ “ተደበደብን” ስንላቸው “ህፃናትን ደብድባችኋል” አሉን። አቶ አስገደ ገብረስላሴ “ህፃን ደብድበሃል” ተብሎ ክስ ተመሰረተበት። ተበዳይ ነኝ ያለ ልጅ (ከደብዳቢዎቹ አንዱ ነው) “ወረቀት እንካ ለናትህ ስጣት አሉኝ። እምቢ ብዬ ‘ሕድሪ መለስ አይነዕብርን’ የሚል ፅሑፍ ያለው መፈክር ሳሳያቸው በጥፊ መቱኝ” አለ። አቶ አስገደ ግን እንኳን ልጅ ሊመታ ወረቀትም አያድልም ነበር። እኛን ነበር የሚያስተባብረው።አብዛኞቹ ህፃናትና ሁኔታውን የሚከታተሉ ወጣቶች ተበተኑ። ዋነኞቹ እኛን ለመደብደብ የተደራጁና የተከፈላቸው ወጣቶች ብቻ በፖሊስ ጣብያው ቅጥር ግቢ ቀሩ።

ወጣቶቹ በፖሊስ ጣብያው ቅጥር ግቢ ዉስጥ እኔ በትክክል የማላውቀው ነገር ያጨሱ ነበር። ሲጋራ እንዳልሆነ ግን እርግጠኛ ነኝ። አንድ የዓዲግራት ኗሪ የሆነ የዓረና አባል እንደነገረኝ ከሆነ ግን ልጆቹ ያጨሱት የነበረውን “አሺሽ” (ሐሺሽ) ነው። አክሎም ልጆቹ የታወቁ የ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች መሆናቸውና ከሌላ ቦታ ወደ ዓዲግራት እንደመጡም ነገረኝ። አውርተን ሳንጨረስ አቶ አስገደ ወደ መርማሪ ፖሊስ ቢሮ ስለተጠራ አብረን ገባን። ከዱርየዎቹ አንዱ ሲያጨሰው የነበረውን ነገር ጨርሶ ወደ መርማሪ ፖሊስ ቢሮ ገባና በእጁ መታኝ። እኔም “ስርዓት አስይዝልን እንጂ ይህ’ኮ የሕግ ቦታ እየመታኝ እያየኸው እንዴት ዝም ትለዋለህ?” ብዬ መርማሪ ፖሊሱን ጠየኩት። መርማሪ ፖሊሱ ልጁ ሲመታኝ እያየ ነበረ። “ከፈለክ ክሰሰው አሁን ግን አትረብሸኝ ስራ ላይ ነኝ” አለ።

አስገደ ገብረስላሴ ታሰረ። ከተወስኑ ሰዓታት በኋላ ተለቀቀ። አልጋ ወደያዝንበት ሆቴል አመራን። አንድ የህወሓት አባል ስለ ሁኔታው ይነግረኝ ነበር። ማን እንዳቀናበረው፣ የታቀደው ነገር፤ ለእሁድ ምን ለማድረግ እንደታሰበ ወዘተ … ። ሁሉም ነገር አጫውቶኝ ሳይጨርስ ካድሬዎች ይከታተሉን ነበርና ሳያዩት ጥሎኝ ሄደ። ፖሊሶች ተከትለው መጡ። ለአስገደ እንደሚያስሩት ነገሩን። እንደገና ዋስ አምጣ አሉት። ቅዳሜ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አከባቢ ነው። ዋስ አስፈረመ። ፖሊሶቹ አልጋ የያዝንበት ሆቴል በተደጋጋሚ ይፈትሹት ገቡ። ወደ ሆቴሉ የሚገባና የሚወጣም ይቆጣጠራሉ።

እንደገና የከተማው የፖሊስ አዛዥ ጨምሮ ሦስት ፖሊሶች መጥተው ለእሁድ ስብሰባው ጥበቃ እንደማያደርጉልን ነገሩን። ያቀረቡት ምክንያትም የሳይክል ዉድድር ስላለ ፖሊሶች ወደዛው ስለሚሄዱ በስብሰባው የሚገኙ በቂ የፖሊስ ሃይል ስለሌለ ነው አሉን።

እኛም አልጋችን ዉስጥ ሁነን ተነጋገርን። ፖሊስ ጥበቃ አያደርግልንም፣ ለስብሰባ የሚመጣ ሰው የፀጥታ ችግር ሊደርስበት ይችላል፣ በኛ ላይም የተቀነባበረ አዲስ የድብደባ ስልት መዘጋጀቱ ሰምተናል፣ አባሎቻችን ክስ ተመስርቶባቸዋል፣ ታስረው በዋስ የተለቀቁም አሉ። ከባድ ድብደባም ደርሶብናል። ከፍተኛ የሆነ ድካም ይሰማናል። ስለዚህ ስብሰባው ሊያካሂድ የሚችል የሰው ሃይል ስለሌለንና ፀጥታ የሚያስከብር አካል ስለሌለ ስብሰባው ሰረዝነው። ስለዚህ ስብሰባው የተሰረዘው መንግስት ፀጥታ የማስከበር ሐላፊነቱ በ አግባቡ ስላልተወጣ ነበር።

እሁድ ጧት (ጥር 18, 2006 ዓም) ወደ መቀሌ ተመለስን። ደብዳቢዎቹ ግን የዓዲግራት ተወላጆች ወደ ሆኑ የዓረና አባላት ቤት እየሄዱ ድንጋይ መወርወር ተያያዙት። ህዝብም ያባብርራቸው እንደነበር ሰምተናል። እሁድ ማምሻው በሁኔታችን የተናደዱ ካድሬዎች ተሰባስበው መምህር ፍፁም ግርሙ ወደሚኖርበት አከባቢ በመሄድ አሳሰሩት። መምህር ፍፁም ግርሙ የዓዲግራት ከተማ ተወላጅና ኗሪ ሲሆን የዓረና ፓርቲ የማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የህዝብ ግንኙነት ምክትል ሐላፊ ነው። እንዲሁም የምስራቃዊ ዞን የዓረና አባላት አስተባባሪ ነው።

ከእሁድ በኋላ በደረሰን መረጃ መሰረት የድንጋይ ውርወራ ፖለቲካው የተቀነባበረው በህወሓት ፅሕፈት ቤት ሁኖ ደብዳቢዎቹም የዓዲግራት ተወላጆች ያልሆኑና ከሌላ አከባቢ ተቀጥረው፣ ተከፍሏቸው የተደራጁ፣ የተሰለፉ ናቸው። አብዛኞቹ ደብዳቢዎች ኤርትራውያን ስደተኞች ነበሩ። ህወሓት ኤርትራውያን ስደተኞችን የተቃዋሚ ፓርቲ ስብሰባዎችን ለመረበሽ ማቀዱም ሰምተናል።

ይኸው ህወሓት ወደ ድንጋይ ውርወራ ፖለቲካ አወረድናት። ድሮም ህወሓቶች ድንጋይ መወርወር እንጂ ሐሳብ መወርወር መቼ ይችሉበታል። ድንጋይ መወርወር የፍርሐት ምልክት ነው። ፈሪዎች ይሸነፋሉ።

It is so!!!

1 comment:

  1. WELCOME TO CONSUMER LOAN FIRM .......... Are you a businessman or a woman? Are you in any financial mess or do you need funds to start your own business? Do you need a loan to start a small-scale pleasant and medium business? Do you have a low credit score and are you finding it difficult to obtain equity loan from local banks and other financial institutes? Our loans are well insured for maximum security is our priority, Our main goal is to help you get the services you deserve, Our program is the fastest way to get what you need in a snap. Reduce your payments to ease the pressure on your monthly expenses. Gain flexibility with which you can use for any purpose - holiday, education, for exclusive purchases We offer a wide range of financial services, which includes: Business Planning, Commercial and Financial Development, Properties and Mortgages, Debt Consolidation Loans , Private Loans, Home Refinancing Loans with low interest rate at 2% per annul for individuals, companies. WE OFFER ALL TYPE OF LOANS, APPLY TODAY FOR AVAILABLE LOANS. Please contact us via email for more information: (consumerloanfirm@gmail.com)

    ReplyDelete