No one is born hating another person because of the colour of his sikn, or his background or his religion.
People must learn to hate, and if they can learn to hate, they can
be tought to love, for love comes more naturally to the human heart than its opposite. Nelson Mandela.

Tuesday, 26 February 2013

«አሰብ የማን ናት ? » ዶር ያእቆብ ኃ/ማሪያም


«አሰብ የማን ናት ? » ዶር ያእቆብ ኃ/ማሪያም
‹‹ … የዘይላን በር ነገር በሚቻልዎ ነገር ሁሉ ተጣጥረው በእኔ ዕጅ ቢሆን እንኳን በሐረርጌ፣ በአሩሲ፣ በከንባታ፣ በጅማ፣ በከፋ ያለን ነገር ሁሉ በዘይላ አደርገው ነበር። ይህም ማለቴ ለእርስዎ እንዳይቸ…ግርዎ ባውቀው የኢትዮጵያ ልጆች በንጉሥ ኡምቤርቶ ብርታት የዘይላ በር እጃችን ተመልሶ ገባ እንዲሉ ሥምዎ በነገሥታት ታሪካችን ይተከላል። … ››
ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ፣ እ.አ.አ በ1876 ዓ.ም ለንጉሥ ኡምቤርቶ ከላኩት ደብዳቤ የተወሰደ። የ3ሺህ ዓመታት ጥንታዊ ታሪክ እንዳላት የተመሰከረላት ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በአንድ ወቅት በዓለም የሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ በግንባር ቀደምትነታቸው ተጠቃሽ እንደነበረች የሚዘከርላት ኢትዮጵያ፣ ሰፊ የባህር ክልልና ወደቦች እንደነበሯት የአደባባይ ምስጢር ነው።

በቀይ ባህር ክልል ወሰነ-ሰፊ ይዞታ የነበራት ኢትዮጵያ፣ በየዘመናቱ ህዝቦቿ በከፈሉት መሪር መስዋዕትነት ነፃነቷንና ክብሯን ጠብቃ የኖረች ሀገርም ነች። አዶሊስ፣ ገምበዛን፣ ዘይላ እና ምፅዋ ወደቦችም በኢትዮጵያ ግዛት ሥር እንደነበሩ በርካታ የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጣሉ። ይሁን እንጂ ኦቶማን ቱርኮች፣ ግብጾችና
ጣሊያን ወዘተ በተለያየ ወቅት የሰሜኑን የሀገሪቱን ግዛት በመቆጣጠር ኢትዮጵያን ለተወሰነ ጊዜ ከቀይ ባህር አካባቢ እንድትገለል በማድረግ ተገዳድረዋት ነበር።
በዚህ ጽሑፍ መንደርደሪያ ላይ ያነበባችኋቸው የኢትዮጵያ ነገሥታት ደብዳቤዎች፣ ሀገሪቷ ከቀይ ባህር አካባቢ እንድትገለል በተደረገችባቸው ወቅቶች ከተፃፃፏቸው መልዕክቶች ውስጥ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ደብዳቤዎቹ ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ የባህር በር ባለቤትነታቸውን ለማስከበር ከከፈሏቸው መራር መስዋዕትነት ባሻገር ዲፕሎማሲያዊ ትግላቸውንም በመጠኑ የሚያመላክቱ ናቸው።
ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም በመስከረም ወር 2004 ዓ.ም ‹‹አሰብ የማን ናት?›› በሚል ርዕስ ለህትመት ያበቁት መጽሐፍ፣ እነዚህን መሰል ታሪካዊ ሰነዶችን፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ምሁራንና ተመራማሪዎች ያሳተሟቸው መጽሓፍትን፣ የጥናት ወረቀቶችን፣ ዘገባዎችን፣ ቃለ-ምልልሶችን ወዘተ በአስረጅነት የያዘ ነው። በመጽሐፉ ገጾች ህዳግ የሰፈሩት ማስታወሻዎች እንደሚያሳዩት፣ ደራሲው በአጠቃላይ 216 ማጣቀሻዎችን ተጠቅመዋል።
ዶ/ር ያዕቆብ በ13 ምዕራፎች ከፋፍለው ለአንባቢያን ያበረከቱት ይህ መጽሐፍ፣ ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ የነበራትን የባህር በር ባለቤትነት መነሻ ያደረገ ነው። ኢትዮጵያውያን በባህር በር ባለቤትነታቸው ላይ የገጠማቸውን ተግዳሮትና ያደረጉትን መራር ትግል ይዘክራሉ – በመጽሐፉ።
እንዲሁም፣ የባህር በር መኖርና አለመኖር በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚያስከትለውን ጥቅምና ጉዳት፤ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ያለውን ሚናና ሌሎች ሁኔታዎች በዶ/ር ያዕቆብ የተዳሰሱ ናቸው። በእነዚህና በመሰል ጉዳዮች ላይ ያነጣጠሩት ዶ/ር ያዕቆብ፣ የኤርትራ መገንጠልን ተከትሎ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር የመሆኗ ጉዳይ ላይ ያተኩራሉ። ይህም ብቻ አይደለም፤ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት እና የአልጀርሱን የድንበር አከላለል ሥምምነትን … ወዘተ በጥልቀት በመመርመር፣ የአሰብ ወደብ ጉዳይ ላይ በተለየ መልኩ አፅንኦት ይሰጣሉ።
ደራሲው ዶ/ር ያዕቆብ በመጽሐፋቸው መግቢያ ባሰፈሩት ረዥም ሀተታ እ.አ.አ በታህሳስ 2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሀከል በአልጀርስ የተፈረመው የወሰን መካለል ሥምምነት ሀገራችን አሰብን የራሷ ግዛት የማድረግ እድል እደነበረና በኢትዮጵያ ድክመት ዕድሉ እንዳመለጠ ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ ‹‹የኢትዮጵያን የባህር በር [አሰብን] ማስመለስ የሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ ብሔራዊ ግዴታ ነው፤ ይህም እንዲሆን እያንዳንዱ ዜጋ አቅሙ የሚፈቅደውንና የሚችለውን እንዲያደርግ›› ይማፀናሉ። (ገፅ 9)።
በእርግጥም የባህር በር ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑ አይካድም። ለዚህ አባባል አስረጅ ይሆን ዘንድ ፕ/ር ሹመት ሲሻኝ በወርሀ ጥር 2003 ዓ.ም ለጦቢያ መጽሔት የሰጡትንና ዶ/ር ያዕቆብ በመጽሐፋቸው የተጠቀሙበትን አስተያየት መጥቀስ ይበቃል።
‹‹ … ኢትዮጵያ በታሪኳ ያለፈቻቸው መነሳትና መውደቅ ከባህር ጋር ከነበራት ቅርበትና ርቀት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው። የባህር በሮቿ በእጇ በነበሩበት ዘመን የጎለበተችና የበለፀገች ኢትዮጵያን መመስረት ተችሏል። በአንፃሩ የባህር በሯን በተነጠቀችባቸው ዘመኖች ኢኮኖሚዋ የኮሰሰ፣ ባህሏ የደበዘዘ፣ ፖለቲካዋ የተናጋ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ አይተናል። በኢትዮጵያ እጅግ አንፀባራቂ የነበረው የአክሱም ሥልጣኔ እንዲያ መግነኑ በሌላ አጋጣሚ ሳይሆን፣ አክሱም በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ በገነባችው የበላይነት ምክንያት ነበር። አዶሊስን ዋና በር በማድረግ በወቅቱ በነበረው ዓለማቀፋዊ ንግድ በግንባር ቀደምትነት በመሳተፏ አክሱም እስካሁን የሚያስደንቀውን ብሩህ ሥልጣኔ መገንባት ቻለች። … ›› (ከገፅ 25-26)
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንደነበረች ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው፣ ከ100 እስከ 150 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተፃፈ በሚገመተው “ፔሪፕለስ ኦፍ ዘ ኤሪትሪያን ሲ” (“Periplus of the Eritrean Sea”) በተሰኘው መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የአክሱም መጠነ-ሰፊ ንግድ በአዶሊስ ወደብ በኩል ይተላለፍ እንደነበርም ይተርካል ይላሉ፡- ዶ/ር ያዕቆብ። ኮስሞስ(Cosmos) የተባለ ጸሐፊ “ክርስቲያን ፎቶግራፊ”(“Christian Photography”) በሚል መፅሐፍ ውስጥ አዶሊስ ወደብን እንደጎበኘም አትቷል ይሏሉ። ኮስሞስ አዶሊስን በጎበኘበት ወቅት የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት አፄ ካሌብ እጅግ የዳበረ ባህር ኃይል እንደነበረው፣ ቀይ ባህርን ተሻግሮ የመንንና ደቡብ አረቢያን ይቆጣጠር እንደነበር ፅፎአል ሲሉ አስረጅ ይጠቅሳሉ። ኢትዮጵያ በረዥም ታሪኳ ሁሉ የባህር በር ባለቤት እንደነበረች፣ነገር ግን በውጭ ኃይሎች ወረራ የተነሳ በተለያየ ወቅት ተግዳሮት እንደገጠማት ይተርካሉ።‹‹ … ኢትዮጵያ የሰሜን ግዛቶቿና የባህር ጠረፎቿ በ1885 ዓ.ም በቱርኮች፣ በግብፆች፣ በጣልያኖች እና በፈረንሳዮች ሴራ ከተያዙባት ጊዜ ጀምሮ፣ በየጊዜው የተፈራረቁት ነገሥታት ሁለገብ ትግል ከማድረግ የቦዘኑበት ጊዜ የለም። ከኢህአዴግ መንግሥት በስተቀር … ሁሉም የባህር በርን ማስመለስ ከውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው ግዙፉና ቀዳሚውን ቦታ አስይዘውት ነበር። … ›› (ገፅ 31)
ለባህር በር ቅርቧና ትልቋ ሀገር ሻዕቢያ አሥመራን ከተቆጣጠረ በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገነጠለች። ሻዕቢያ ከምፅዋ በተጨማሪ አሰብ ወደብንም በሕገ-ወጥ መንገድ ጠቀለለ። ‹‹በኢህአዴግ ቡራኬ ኤርትራ አሰብን የራሷ አካል በማድረጓ ኢትዮጵያ የባህር በሮቿን ተነጠቀች። በዓለም በህዝብ ቁጥር ትልቋ ወደብ አልባ ሀገርም ሆነች። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ድንበርና በባህሩ መሀከል ያለው 60 ኪሎ ሜትር፣ በዓለም በአንድ አገርና በባህር መሀከል ያለው እርቀት አጭሩ ለመሆን በቃ›› ሲሉ ዶ/ር ያዕቆብ አስረጅ ያቀርባሉ። (ገፅ 46)
ወደብ አልባ ከሆኑ የዓለም አርባ (40) ሀገራት መሀከል በህዝብ ብዛት ኢትዮጵያ (በ82,824,732 የሕዝብ ቁጥር) የመጀመሪያ ደረጃ የያዘች ሲሆን፣ ዩጋንዳ በ32,709,865 የህዝብ ቁጥር ትከተላለች። ኔፓል በ29,330,505 ትሰልሳለች። አንዶራ 7,638 የህዝብ ቁጥር ብቻ ያላት የመጨረሻዋ ሀገር መሆኗን የፌብርዋሪ 20/2011 እ.አ.አ መረጃ ያመለክታል።
ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም በህዝብ ብዛት ቁጥር ግዝፈቷና ለባህር ባላት ቅርበት የመጀመሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አገር መሆን እንደማይገባት ነው በመጽሐፋቸው በብርቱ የሚሟገቱት። የሙግታቸው ዋንኛ ትኩረትና ማነጣጠሪያቸው አሰብ ወደብ ነው። የአልጀርሱ ሥምምነት፣ የአሰብ ወደብ ባለቤትነት መብቷን የምታስከብርበት መልካም አጋጣሚ ነበር ባይ ናቸው።
ኢህአዴግ፣ በአልጀርሱ ሥምምነት ወቅት በተገቢው መልኩ ታሪካዊና ሕጋዊ መብቷን ለማስከበር አልጣረም ባይ ናቸው። ምክንያቱም፣ በአልጀርሱ የድንበር ሥምምነት የኢትዮጵያ በ1900፣ በ1902 እና በ1908 ዓ.ም ከጣሊያን ጋር በተዋዋለቻቸው ውሎች ነው። የቅኝ ግዛት ውሎች ደግሞ ተቀባይነት የላቸውም። የድንበር መካለልን በተመለከተ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ሕጎች (ድንጋጌዎች) በሚገባ ተግባራዊ አልሆኑም ሲሉ በርካታ ሁነቶችን አንስተው ይተነትናሉ።
በአልጀርስ ስምምነት መሠረት የተቋቋመው ኮሚሽን አመሰራረትና ውሳኔውንም ይገመግማሉ። የተደራዳሪዎቹን ማንነት፣ የድርድሩን የጊዜ ሰሌዳ፣ አደራዳሪውን፣ የድንበር ኮሚሽኑ ዳኞችን ማንነት፣ የተደረገውን ክርክር ይዘት ወዘተ ደረጃ በደረጃ ይፈትሻሉ። ይህም ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ እንዴት መደምደም እንደለበት፣ ጥያቄውን ተፈፃሚ ማድረግ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦችና ጥቆማዎችንም ያቀርባሉ። በመጨረሻም፣ ‹‹አንድ ሕዝብ በአንድነት፣ በእውነተኛና ፍትሃዊ በሆነ ዓላማ አምኖ፣ በዓላማውን ስኬታማነት በፅናት ከታገለ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ምንም አይሳነውም። የኢትዮጵያ የባህር በር መብት ደግሞ ዓለም የተስማማበት ፍትሃዊ ጥያቄ ነው። ጉዳዩን ጊዜ እስኪፈታው ረግቶ እንዳይቀር ማንቀሳቀስ የሁሉም ኢትዮጵያ ተግባር ነው። … ›› ሲሉ አፅንኦት ይሰጣሉ።
እኛም የዶ/ር ያዕቆብን ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ የምንቋጨው የኢህአዴግ አባልና የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሜ/ጄ/ል አበባ ተ/ኃይማኖት፣ ለዩኒቨርስቲ መመረቂያ ከፃፉት ጽሑፍ የሚከተለውን በመንቀስ ነው፡-
‹‹እ.አ.አ እስከ 1994 ዓ.ም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና ከፍተኛው የመከላከያ አዛዦች አንዱ እንደመሆኔ የመንግሥትን አቋም አውቅ ነበር። የባህር በር ጥያቄ የሚያነሱ (ኢትዮጵያውያን) ሕገመንግስቱን፣ በተለይ የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠልን የሚደነግገው አንቀጽ 39 የማይቀበሉ፣ የፊውዳል ሥርዓትና ወታደራዊውን አገዛዝ የሚናፍቁ፣ የኤርትራን ነፃነት የማይቀበሉ ጦርነት ናፋቂዎች አድርጌ እቆጥራቸው ነበር። አሰብ ወደብ ውስጥ ብቻ የነበረው የኢትዮጵያ ኃብት ዝርፊያ የባህር በር ጥያቄ እንዳነሳ ቀሰቀሰኝ። ለምን (ህወኃት/ኢህአዴግ) ይህንን አቋም እንደወሰደ ታሪክ እስኪያጣራ ምስጢር ሆኖ ይቆያል። ሆኖም ለእኔ ምክንያቱ ድንቁርናና አጉል ትዕቢት ነው።›› (ገፅ 5)
ለማንኛውም የዶ/ር ያዕቆብ ‹‹አሰብ የማን ናት?›› መጽሐፍ ሙሉ ይዘት በተመለከተ፣ ቀሪውን አስተያየት ለአንባቢያን ትተን በዚሁ ብንሰነባበትስ?
posted by Gheremew Araghaw

No comments:

Post a Comment