ድምፃችን ይሰማ
በዴሞክራሲያዊ ስርአት ውስጥ ዜጎች መሪያቸውን ከመምረጥ ባለፈ በአመራሩ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን የመከታተልና የማሳወቅ፣ ለመብቶቻቸውም የመታገል ሉአላዊ መብት አላቸው፡፡ የሚደርሱባቸውን አስተዳደራዊ በደሎች በሰላማዊ መንገድ መቃወምና እንዲስተካከልላቸውም አጥብቆ መጠየቅ አሌ ከማይባሉ መሰረታዊ መብቶቻቸው አንዱ ነው፡፡ ይህንን መርህ ህገ መንግስታችን በግልጽ ያጸደቀው መሆኑም ያለጥርጥር ይታወቃል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ከሀምሌ 2003 ጀምሮ በመንግስትና በመጅሊስ ጥምረት በግድ እየተጫነበት የነበረውን አዲስ አህባሽ የተባለ አንጃ ‹‹አልቀበልም›› በማለት የችግሩ ምንጭ የሆነውን መንግጅሊስን (የመንግሰትና የመጅሊስ ይፋዊ ጥምረት) በመቃወም ያደረገው ትግል ከዚህ የዜጎች ሉአላዊ መብት የመነጨ ነበር፡፡ ይህንንም ከየካቲት 26 በፊት በነበረው ወቅት የመንግስት ባለስልጣናት በግልጽ እውቅና ሲሰጡት ታይተዋል፡፡
