የአብዮቱ የምፅአት ቀን ምልክቶች! (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)September 3, 2013
‹‹በአፍሪካ ትልቁ አምባገነን›› የሚል ተቀፅላ የተሰጣቸው የሊቢያው ኮሎኔል መሀመድ ጋዳፊ እና የግብፁ ሆስኒ ሙባረክ በህዝባዊው እምቢተኝነት ከስልጣን መነሳታቸው በመሰል አገዛዞች ስር ያደሩ ሕዝቦችን ለለውጥ ማነቃቃቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ በተለይም ከራሳቸው መንግስት ተኳርፈው አስተማማኝ የዲሞክራሲ ተቋማትን በገነቡ የምዕራብ ሀገራት በብዛት የሚኖሩ ዜጎች ላሏት ኢትዮጵያ ንቅናቄው የፈጠረው ተመሳሳይ መነሳሳት ቀላል ባለመሆኑ ኢህአዴግን ሊወጣው ከማይችለው ቅርቃር ውስጥ ከቶታል፡፡ የዚህ ተጠየቅም ቀድሞ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ድርጅቱ ‹እሳት ማጥፊያ› ያደርጋቸው የነበሩ አጀንዳዎቹ ያለፈባቸው (Expired) መሆናቸውን ማሳየት ነው፡፡
ሰባቱ ‹‹ቀኖና››ዎች
ሰባቱ ‹‹ቀኖና››ዎች
ስርዓቱ ከሃያ ሁለት ዓመታት በላይ በስልጣን የመቆየቱ ምስጢር ከሁለት ምንጭ የሚቀዳ ነው፡፡ አንዱ የታዘዘውን ሁሉ ያለ ምንም ማንገራገር የሚፈፅመው ጠመንጃ አንጋቹ (መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና የደህንነት መዋቅሩ) ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ከፖለቲካው ፍልስፍና የሚወረሱ አጀንዳዎቹ ናቸው፤ ይሁንና ለጊዜው የታጠቀውን ኃይል ወደ ጎን ብለን ስርዓቱ ‹‹የፖለቲካዬ መገለጫዎች›› ብሎ እንደ ቀኖና ይዟቸው የነበሩትን ሰባት ጉዳዮች በደምሳሳው ብንቃኝ የመቃብር አፋፍ ላይ የቆመ ስርዓት ስለመሆኑ የማመላከት አቅም አላቸው ብዬ አስባለሁ፡፡
