ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም
ከጥቂት ቀናት በፊት አንዳንድ ሰዎች በዓባይ ጉዳይ ቀረርቶና ሽለላ ማሰማት ሲጀምሩ ከባድ የሆነ የመረጃ እጥረት
መኖሩን ስለተገነዘብሁ ስለግብጽ የኃይል ሚዛን ደረቅ መረጃ የጦርነትን መጥፎ መልክ ከሚገልጽ አስተያየት ጋር
አቀረብሁ፤ የወያኔ ሎሌዎች ወዲያው በእኔ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ከፈቱ፤ ድንቁርናው ከዚህ ይጀምራል፤ ማሪዮ ፊልሞና
ብሩኖ ‹‹በአፍራሽ አስተሳሰባቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዛሬም የግብጽን ጦር ገና ከሩቁ
እንድንገብርለት ጉትጎታ ይዘዋል፡፡›› በማለት ውርጅብኙን ይጀምራል፤ አንድም ቦታ እኔ ያቀረብሁትን መረጃም ሆነ
አስተያየት አንሥቶ ጉድለትን አላሳየም፤ ዓላማው መረጃው ወይም አስተያየቱ አይደለም፤ ለረጅም ጽሑፉ ዓላማው እኔ
ነኝ፤ የአሉላ ሰሎሞን ጆቫኒ የግጥም ዓይነት መልክ ከመያዙ በቀር ያው ነው፡፡
ለእነዚህ ሰዎች መልስ
የሚያስፈልጋቸው በእኔ ላይ የሰነዘሩትን ለማረም አይደለም፤ አንዳንድ ሰዎች መልስ አይገባቸውም ይሉኛል፤ እውነት
ነው፤ እኔ በሥራዬ እቆማለሁ፤ ወይም በሥራዬ እወድቃለሁ፤ ነገር ግን ንጹሐን ወጣቶችን አዋቂዎች መስለው እንዳይበክሉ
መከላከል ግዴታ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ድንቁርና እንደተላላፊ በሽታ ነው፤ ይጋባል፡፡